በሐዋሳ ከተማ ባለሀብቱ የተከራካሪያቸውን ጠበቃ መግደላቸው ተሰማ

-ከጠበቃው ጋር የተመቱት ረዳት ጠበቃ ተርፈዋል
-ተጠርጣሪው ባለሀብት አለመያዛቸውን ፖሊስ ገልጿል
በደቡብ ክልል ሐዋሳ ከተማ መስከረም 27 ቀን 2007 ዓ.ም. የብሉ ናይል ሆቴል ባለቤት ናቸው የተባሉ ባለሀብት፣ በፍትሐ ብሔር ክስ ይሟገቷቸው የነበሩ ጠበቃ በሽጉጥ መትተው መግደላቸውንና ረዳታቸውን ማቁሰላቸውን ምንጮች ለሪፖርተር ገለጹ፡፡
የሆቴሉ ባለቤት የተከሰሱበት የፍትሐ ብሔር ጉዳይ ለጊዜው ባይታወቅም፣ እሳቸውን ወክለው ከሚከራከሩት ጠበቃ በተቃራኒ ሆነው ሲከራከሩ የነበሩት ጠበቃ ዳንኤል ዋለልኝ፣ በጥይት ተመትተው እንደወደቁ ወደ ሆስፒታል ቢወሰዱም ሊተርፉ አለመቻላቸውን ምንጮች አስረድተዋል፡፡
አንገታቸው አካባቢ ተመትተው የነበሩትና የአቶ ዳንኤል ረዳት መሆናቸው የተገለጸው አቶ ዳግማዊ አሰፋ፣ አዲስ አበባ ኮሪያ ሆስፒታል መስከረም 27 ቀን 2007 ዓ.ም. ማምሻውን ገብተው በተደረገላቸው የቀዶ ሕክምና መትረፋቸውንም ምንጮች አክለዋል፡፡
ባለሀብቱ በሟቹ ጠበቃ በሌላም ክርክር መሸነፋቸውንና አሁንም በመከራከር ላይ ባሉት የፍትሐ ብሔር ክርክር በመሸነፍ ላይ በመሆናቸው ምክንያት ዕርምጃውን ሳይወስዱ እንዳልቀሩ የሚናገሩት ምንጮች፣ ጠበቃ ዳንኤልንና ረዳታቸውን በጥይት የመቷቸው በቢሮአቸው በሥራ ላይ እንዳሉ ከጠዋቱ አራት ሰዓት አካባቢ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ 
የደቡብ ክልል ፖሊስ ስለ ጉዳዩ ከሪፖርተር ለቀረበለት ጥያቄ በሰጠው ምላሽ፣ ድርጊቱ እውነት መሆኑ አረጋግጦ ተጠርጣሪው ግን አለመያዛቸውን አስታውቋል፡፡ ፖሊስ በክትትል ላይ መሆኑና ተጠርጣሪው ከአገር እንዳልወጡም አክሏል፡፡ 
የሟች ጠበቃ ዳንኤል ዋለልኝ አሰፋ የቀብር ሥነ ሥርዓት በሐዋሳ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን መስከረም 29 ቀን 2007 ዓ.ም. መፈጸሙንም አስታውቋል፡፡ 
የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሕግ ከሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ማግኘታቸውንና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በሰብዓዊ መብት አያያዝ ከዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሳውዝ አፍሪካ በዚህ ወር ያገኙ እንደነበር የቅርብ ጓደኞቻቸው ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የአቶ ዳንኤልን ቤተሰቦችም ሆነ የተጠርጣሪውን ቤተሰቦች ለማግኘት የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር