አንድነት ፓርቲ አቅዶት የነበረው ሠልፍ ላልተወሰነ ጊዜ ተራዘመ

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (በአንድነት) መስከረም 25 ቀን 2007 ዓ.ም. ሊያደርገው አቅዶት የነበረው ሰላማዊ ሰልፍ ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙን፣ የፓርቲው ፕሬዚዳንት አቶ ግዛቸው ሽፈራው (ኢንጂነር) ለሪፖርተር አስታወቁ፡፡
ፕሬዚዳንቱ ሠልፉን ለሌላ ጊዜ ማስተላለፍ ያስፈለገበትን ዋነኛ ምክንያት ሲያስረዱ፣ ‹‹እኛ ብቻችንን ከምናደርገው ሠልፉ የሕግ የበላይነትና የህሊና እስረኞችን የሚመለከት በመሆኑ፣ ሌሎች የሚመለከታቸው ፓርቲዎችም አብረን እናደርገዋለን ስላሉ በጋራ እየሠራን በመሆኑ ነው፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ለማድረግ አቅደውት የነበረውን ስብሰባ በተመለከተ፣ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰላማዊ ሠልፍና ስብሰባ ማሳወቂያ ቢሮ አስገብተውት የነበረውን ደብዳቤ ከምን እንደደረሰ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹ጥያቄው ምንም መልስ አላገኘም፡፡ እኛም ጉዳዩን አልተከታተልነውም፤›› ብለዋል፡፡
ለዚህም እንደ ምክንያት ያቀረቡት የአቅጣጫ ለውጥ ማድረጋቸውን ሲሆን፣ በዚህም የተነሳ ጉዳዩን በቅርበት አለመከታተላቸውን ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡
ፓርቲው መስከረም 25 ቀን 2007 ዓ.ም. ሊያደርገው አቅዶት የነበረው ሠልፍ ‹‹የአንድነት ንቅናቄ ለሕግ የበላይነትና የህሊና እስረኞችን ለማሰብ›› የሚል መሪ ቃል የነበረው ሲሆን፣ ከዚህም ጋር በተያያዘ የፕሬስ መታፈን፣ የጋዜጠኞችን ስደትና ተያያዥ ጉዳዮችንም እንደሚያነሳ ተገልጾ ነበር፡፡
እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ አሁን ግን፣ ፓርቲው የአቅጣጫ ለውጥ በማድረጉ ሠልፉ መቼ እንደሚካሄድ አልተወሰነም፡፡ ‹‹የሠልፉን ቀን አሁን መገመት ያስቸግራል፤›› ብለው፣ በዚሁ ሠልፍ ላይ ከአንድነት ፓርቲ ጋር ምን ያህል ሌሎች ፓርቲዎች እንደሚሳተፉም ገና አለመታወቁን አስረድተዋል፡፡ ‹‹የትኞቹ ፓርቲዎች እንደሚሳተፉ ወደፊት ብንጠቅሰው ይሻላል፤›› በማለት የሠልፉን ጊዜና ፓርቲዎችን ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር