17ኛው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ምን ይዞ ቀርቧል? የደቡብ ዋንጫን ማንሳት የቻለውና በአሰጣኝ ዘላለም ሽፈራው የሚሰለጥነው ሲዳማ ቡና ደግሞ ሙገር ሲሚንቶን በሜዳው አስተናግዶ አንድ ለባዶ አሸንፎ ሸኝቶታል

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በአዲስ መልክ መካሄድ ከጀመረ የዘንድሮው 17ኛ ዓመቱ ነው። በእነዚህ 17 ዓመታት 11 ጊዜ ቅዱስ ጊዮርጊስን፣ ሁለት ጊዜ መብራት ኃይልንና ሀዋሳ ከነማን እንዲሁም ኢትዮጵያ ቡናን እና ደደቢትን አንድ አንድ ጊዜ ሻምፒዮን ማድረግ ችሏል። ዮርዳኖስ አባይ 24 ግቦችን በአንድ የውድድር ዓመት በማስቆጠር ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ ያጠናቀቀበት ሪከርድ በፕሪሚየር ሊጉ ታሪክ ያልተደፈረ ሪከርድ ነው።

ያለፈውን የውድድር ዓመት ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ የዋንጫ ባለቤት በመሆን ሲያጠናቅቅ ጀርመናዊው የክለቡ አሰልጣኝ   ኮከብ አሰልጣኝ፣ ሩዋንዳዊው ግብ ጠባቂው ሮበርት ኦዶንካራ ኮከብ ግብ ጠባቂ እንዲሁም አጥቂው ኡመድ ኡክሪ ኮከብ ተጫዋችና ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ በማጠናቀቃቸው ፈረሰኞቹ ያለፈውን የውድድር ዓመት የድርብርቦሽ ድል ባለቤት ሆነው ነበር። ዘንድሮስ?

ፕሪሚየር ሊጉ ባለፈው ቅዳሜ አንድ ለእናቱ በሆነው የአዲስ አበባ ስታዲየም ሲጀመር የአዲስ አበባ ዋንጫን ያነሳው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኢትዮጵያ ቡናን  በጨዋታ ብልጫ  ሁለት ለባዶ በማሸነፍ ተጀምሯል። በዚያ ጨዋታ የአሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማሪያም ልጆች በጥላሁን መንገሻ አቻዎቻቸው ላይ  የበላይ ሆነው ያመሹ ሲሆን፤ በአንጻሩ የኢትዮጵያ ቡና አጥቂዎች የተጋጣሚዎቻቸውን የግብ መስመር ማግኘት ተስኗቸው ደጋፊዎቻቸውን ሲያሳዝኑ አምሽተዋል። በተለይ ከቶጎ የተገዛው አጥቂው ኤዶም ከአንድ ፕሮፌሽናል ተጫዋች የማይጠበቅ በእጅጉ የወረደ አቋም ያሳየ ተጫዋች ሆኗል።

ትናንት በአዲስ አበባና በተለያዩ የክልል ከተሞች ስድስት ጨዋታዎች ተካሂደው ነበር። ክልል ላይ ከተካሄዱት ጨዋታዎች መካከል የፕሪሚየር ሊጉ ሻምፒዮን ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ አዳማ ተጉዞ ከብሔራዊ ሊጉ ሻምፒዮን አዳማ ከነማ ጋር ያካሄደው ጨዋታ ይገኝበታል። “የሻምፒዮናዎች ደርቢ” የተባለው ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች የተጋጣሚዎቻቸውን መረብ ለመድፈር ሳይነሳሱ ተከባብረው በመውጣት ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል። 

ሀዋሳ ላይ የተካሄደው የደቡብ ደርቢው የሃዋሳ ከነማና አርባ ምንጭ ከነማ ጨዋታ ደግሞ መሳ ለመሳ ተለያይተዋል። ባለሜዳዎቹ ታፈሰ ተስፋዬ ባስቆጠረላቸው ግብ ለረጅም ሰዓት መምራት ቢችሉም በጨዋታው መጠናቀቂያ አርባ ምንጭ ከነማዎች አቻ የሚያደርጋቸውን ግብ አስቆጥረው አንድ ነጥብ ይዘው ተመልሰዋል። 

የደቡብ ዋንጫን ማንሳት የቻለውና በአሰጣኝ ዘላለም ሽፈራው የሚሰለጥነው ሲዳማ ቡና ደግሞ ሙገር ሲሚንቶን በሜዳው አስተናግዶ አንድ ለባዶ አሸንፎ ሸኝቶታል። ሌላው የደቡብ ክልል ክለብ የሆነው ወላይታ ድቻ ደግሞ በሜዳው ለዳሽን ቢራ እጅ ሰጥቷል። ሁለቱ ክለቦች ወደ ፕሪሚየር ሊግ ያደጉት በተመሳሳይ ዓመት ማለትም በ2006 ዓ.ም ሲሆን በአንድ ዓመት የፕሪሚየር ሊግ ቆይታቸው በተገናኙባቸው ሁለት ጨዋታዎች ሳይሸናነፉ ነበር የተለያዩት። ትናንት ግን ጎንደሬዎቹ ቦዲቲ ላይ መዳኔ ታደሰ ባስቆጠረላቸው ብቸኛ ግን ሙሉ ሶስት ነጥብ ይዘው መመለስ ችለዋል። 

አዲስ አበባ ስታዲየም ደግሞ ትናንት ሁለት ጨዋታዎችን ማስተናገድ ችሏል። በመጀመሪያ ያስተናገደው የጥሎ ማለፍ አሸናፊውን ደደቢትን ከወልድያ ጋር ነበር። ጨዋታው ሲጀመር 22 ሆነው የገቡት ሁለቱ ቡድኖች ጨዋታው ከተጀመረ 30 ደቂቃ በኋላ ግን የወልድያው አብይ በየነ በቀይ ካርድ ከሜዳ እንዲሰናበት በመደረጉ 21 ተጫዋቾች ብቻ ናቸው ጨዋታውን የጨረሱት። ለፕሪሚየር ሊጉም ሆነ ለአዲስ አበባ ስታዲየም አዲስ የሆኑት ወልድያዎች አብይ በየነ ባስቆጠራት ግብ መምራት ችለው የነበረ ቢሆንም ብዙም ሳይቆዩ የደደቢቱ ታደለ መንገሻ ባለሜዳዎቹን አቻ ማድረግ ቻለ። ታደለ ግብ ከማስቆጠሩም በላይ በእለቱ ያሳየው እንቅስቃሴ በተመልካች አድናቆት ያተረፈለት ነበር። ሽመክት ጉግሳ ደግሞ ደደቢት መሪ የሆነበትን ግብ አስቆጠረ። 

ለወልድያ ብቸኛዋን ግብ ያስቆጠረው አብይ በየነ ሁለት ተከታታይ ቢጫ ካርዶችን በማየቱ በቀይ ሲባረር የአንድ ሰው ብልጫ ያገኙት የንጉሴ ደስታ ልጆች በወልድያ ኣቻዎቻቸው የግብ ክልል ላይ እንደ ልባቸው ሲመላለሱበት አመሹ። ናይጄሪያዊው የቀድሞው የመብራት ኃይልና ቅዱስ ጊዮርጊስ አጥቂ ሳሙኤል ሳኖሜ ሁለት ግቦችን አከታትሎ በማስቆጠር የግብ ልዩነቱን ወደ አራት አሳድገው ለረፍት ተለያዩ። ከእረፍት መልስም ዳዊት ፈቃዱ ሁለት ግቦችን በማስቆጠሩ በአጠቃላይ ድምር ደደቢት ስድስት ለአንድ በማሸነፍ የፕሪሚየር ሊጉ መሪ የሚያደርገውን ሙሉ ሶስት ነጥብና ንጹህ አምስት ግቦችን እንዲያገኝ አድርጎታል።

  ወልድያ ትናንት ያሳየውን የወረደ አቋም በጊዜ ማስተካከል ካልቻለ ወደፊት የሚያሳጋው ይሆናል። አሸናፊው ደደቢትም ቢሆን ከተጋጣሚው ከባድ ፉክክር ስላልገጠመው እንጅ በቀላሉ መረቡን ለማስደፈር የተዘጋጀ ክለብ ነበር። በተለይ ወልድያዎች ጨዋታውን በሙሉ 11 ተጫዋች መጨረስ ቢችሉ ኖሮ ውጤቱ ለደደቢት የከፋ ሊሆን ይችል ነበር ማለት ይቻላል። የክለቡ የቀኝ መስመር ለተጋጣሚ ተጫዋቾች የተመቸ መንገድ ሆኖ ታይቷል።  

ከዚህ ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ የተገናኙት መከላከያና መብራት ኃይል ሲሆኑ ሁለቱም ቡድኖች ተመጣጣኝ ፉክክር አድርገዋል። ምንም እንኳ ሁለቱም ቡድኖች ተመጣጣኝ ፉክክር ያደረጉ ቢሆንም አንዳቸውም የተጋጣሚያቸውን መረብ መድፈር አልቻሉም ነበር። በተለይ የመብራት ሀይሎቹ አጥቂዎች ራምኬሎ   እና ፍቅረየሱስ    ያደረጓቸውን ተደጋጋሚ ሙከራዎች አዲሱ የመከላከያ ግብ ጠባቂ ጀማል ጣሰው በብቃት ማዳን በመቻሉ ክለቡን መታደግ ችሏል። መከላከያዎችም ቢሆኑ በምንይሉ ወንድሙና ሙሉዓለም ጥላሁን ያደረጓቸውን የግብ ማግባት ሙከራዎች የመብራት ሀይሉ ግብ ጠባቂ አክሊሉ አሰግድ  ግብ ከመሆን አግዷቸዋል።

17ኛው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በመጀመሪያ ቀን ውሎው 13 ግቦችን ያስተናገደ ሲሆን ከተቆጠሩት 13 ግቦች መካከል ሰባቱ የተቆጠሩት በአንድ ጨዋታ ደደቢት ከወልድያ ነው። መከላከያ ከመብራት ኃይል እና አዳማ ከነማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ያለምንም ግብ የተጠናቀቁ ጨዋታዎች ሲሆኑ ወላይታ ድቻ፣ ሙገር ሲሚንቶና ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ ግብ ሳያስቆጥሩ የተሸነፉ ክለቦች ናቸው። ውድድሩ ወደፊትስ ምን ይዞ ይቀርባል? አዲስ የፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ ያሳየናል? በዮርዳኖስ አባይ ተይዞ የቆየው የከፍተኛ ግብ አግቢነት ክብረወሰንስ በዚህ ዓመት ይሰበራል? ተደጋጋሚ የዳኞች ስህተትና የተጫዋቾች አመለ ብልሹነት ተስተካክሎ ይቀርባል? ወደፊት የምናየው ይሆናል።

ምንጭ፦ www.ethiofootball.com

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር