ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት አንድ ቅርሷን በዩኔስኮ ልታስመዘግብ ነው፤ የፊቼ ጫምባላላስ ጉዳይ ከምን ደረሰ?

አዲስ አበባ መስከረም 15/2007 ኢትዮጵያ ካሏት ቅርሶች መካከል በተያዘው ዓመት አንዱን በመንግሥታቱ ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባልህ ድርጅት (ዩኔስኮ) በቅርስነት እንደምታስመዘግብ የቅርሥ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን አስታወቀ።
የባለሥልጣኑ የባህላዊ ቅርስ ጥናትና ምርምር ዳይሬክተር አቶ ደሳለኝ አበባው ለኢዜአ እንዳስታወቁት አገሪቷ በድርጅቱ በጊዚያዊነት ካስመዘገበቻቸው አራት ቅርሶች መካከል አንዱን በዚህ ዓመት በቋሚነት ለማስመዝገብ እየተንቀሳቀሰች ነው።
ዩኔስኮ በጊዚያዊነት ከመዘገባቸው መካከል የመልካ ቁንጡሬና የባጭልት የቅሪት አካል አካባቢዎች፣ የጌዲኦ ባህላዊና ተፈጥሯዊ መልከአ ምድር እንዲሁም የሶፍ ዑመር ዋሻና የድሬ ሼክ ሁሴን መንፈሳዊ፣ ባህላዊና ታሪካዊ ቅርሶች እንደሚገኙበት ገልጸዋል።
ድርጅቱ ከየአገራቱ በየዓመቱ አንዳንድ ቅርሶች እንዲመዘገቡ በሚፈቅደው መሰረት ኢትዮጵያ ከእነዚህ አራት በጊዚያዊነት ከተመዘገቡት ቅርሶች አንዱን በተያዘው ዓመት ታስመዘግባለች ብለዋል።
በቅርስነት ይመዘገባሉ ከሚጠበቁት ቅርሶች አንዱ የሆነው በላይኛው የአዋሽ ሸለቆ የሚገኘው የመልካ ቁንጡሬ ከግማኝ ክፍለ ዘመን በላይ የቅሪተ አካል ምርምርና ጥናት የተካሄደበት አካባቢ ነው።
በአካባቢው ከ80 በላይ የቅሪተ አካል ንብርብሮች የተገኙ ሲሆን 30 ያህሉም በቁፋሮ መውጣት የቻሉ እንደሆነ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
በአካባቢው የሆሞ ኢሬክተስን ጨምሮ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ የድንጋይ ቁሳቁሶች፣ የሰውና የእንስሳት ቅሪት አካላት በቁፋሮ የተገኙበት እንደሆነም ተናግረዋል።
ከእነዚህ ቅርሶች በተጨማሪ ሦስት የማይዳሰሱ ቅርሶች በዩኔስኮ ጊዜያዊ መዝገብ ላይ በቅርስነት እንዲሰፈሩ ውሳኔ ይተላለፋል ተብሎ እንደሚጠበቅ አቶ ደሳለኝ አመልክተዋል።
በማይዳሰስ ቅርስነት እንዲመዘገቡ የሚጠበቁት የሐረር ሕዝቦች የአሹራ በዓል አከባበር፣ የሲዳማ የዘመን መለወጫና የጨምበላላ በዓል እንዲሁም የኦሮሞ የገዳ ሥርዓት ይገኙበታል።
የቅርሶቹን ምዝገባ አስመልክቶ ድርጅቱ ውሳኔውን በመጪው ኅዳር ወር አጋማሽ ለኢትዮጵያ እንደሚያሳውቅ ይጠበቃል ሲሉ ዳይሬክተሩ ተናገረዋል። 
ከዚህ ጎን ለጎን የአገሪቷ ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊና መንፈሳዊ ቅርሶች ምዝገባና ጥበቃ በስፋት እየተከናወነ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የባለሥልጣኑ የቋሚ ቅርሶች ልማት ዳይሬክተር ወይዘሮ ፀሀይ እሸቱ ናቸው።   
በአክሱም፣ በፋሲል ግቢ፣ በላሊበላ፣ በጥያ፣ በሐረር ጀጎልና በኮንሶ ታሪካዊ መስህቦች ላይ የቅርስ አስተዳደር ዕቅድና የድንበር ማካለል ሥራዎች መስራታቸውን በመግለጽ ጭምር።
እንደ ዳይሬክተሯ ገለፃ ኢትዮጵያ በቅርስ ጥበቃ ረገድ አፍሪካ አገራት ጋር ስትነፃጸር የተሻለ አፈፃጸም አላት።
እንዲያም ሆኖ በመስኩ መድረስ የሚጠበቅባትን ደረጃ ለመስራት ጠንካራ ሥራ መሥራት እንዳለባት ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1977 የዓለም የተፈጥሯዊና ባህላዊ እንዲሁም ተፈጥሯዊና ባህላዊ ጥምር ቅርሶች ስምምነትን ተቀብላ አጽድቃለች።
ስምምነቱን ተቀብላ ካፀደቀች ከአንድ ዓመት በኋላ የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክና የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በዩኔስኮ በቅርስነት መመዝገብ ችለዋል።
ባላፈው ዓመትም በኢትዮጵያ የኦርቶዶክስ ዕምነት ተከታዮች የሚከበረው የመስቀል በዓል በዩኔስኮ በቅርስነት መመዝገቡ የሚታወስ ነው።
ምንጭ፦ ኢዜኣ


Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር