በርካታ የሲዳማ ባላሃብቶችን በሽርክና የያዘው ደቡብ ግሎባል ባንክ ኣዲስ ፕሬዚዳንት ልሾምለት ነው

የአቢሲኒያ ባንክ ፕሬዚዳንት ቀጣይ ማረፊያ ደቡብ ግሎባል ባንክ እንደሆነ ተጠቆመ

-ባንኩ ገንዘብና ወርቅ ሸልሞ ሸኛቸው   -   የደቡብ ግሎባል ባንክ ፕሬዚዳንት ከኃላፊነታቸው ለቀቁ
በዳዊት ታዬ 
ከአቢሲኒያ ባንክ ፕሬዚዳንትነታቸው በፈቃዳቸው መልቀቃቸውን ያሳወቁት አቶ አዲሱ ሃባ፣ ቀጣይ ማረፊያቸው ደቡብ ግሎባል ባንክ እንደሆነ ተጠቆመ፡፡ የደቡብ ግሎባል ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ወርቁ ለማ ደግሞ ኃላፊነታቸውን ለቀዋል፡
አቢሲኒያ ባንክ ለአምስት ዓመት የመሩት አቶ አዲሱ፣ በባንኩ ታሪክ የመጀመሪያ ነው በተባለው የሽኝት ፕሮግራም ላይ፣ በባንኩ ቦርድ ውሳኔ መሠረት የግማሽ ሚሊዮን ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡ 
ከገንዘብ ሽልማቱ በተጨማሪ ለእርሳቸውና ለባለቤታቸው በነፍስ ወከፍ ሃያ ግራም ወርቅ የተበረከተላቸው ሲሆን፣ በቆይታቸው ለባንኩ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደነበር የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ መሐሪ ዓለማየሁ በሽኝት ፕሮግራሙ ላይ ተናግረዋል፡፡ 
ቅዳሜ ነሐሴ 24 ቀን 2006 ዓ.ም. በሒልተን ሆቴል በተደረገው የሽኝት ፕሮግራም ላይ አቶ መሐሪ የአቶ አዲሱ መልቀቅ ድንገተኛና ያልተጠበቀ መሆኑን የገለጹት፣ ‹‹አቶ አዲሱ በራሳቸው ምክንያት ባንካችንን ለመልቀቅ ስለጠየቁ ቦርዱም ጥያቄው ድንገተኛ ሆኖ ደስተኛ ባይሆንም ጥያቄውን ተቀብሎታል፤›› በሚል ነው፡፡ አያይዘውም ከአቶ አዲሱ ጋር ወደፊትም መልካም ግንኙነቱ እንደሚቀጥል ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል፡፡ አቶ አዲሱ በአምስት ዓመት ቆይታቸው አበርክተዋል ያሉዋቸውን ዋና ዋና ተግባራት ያስታወሱት የቦርድ ሊቀመንበሩ፣ ‹‹አቶ አዲሱ ለአቢሲኒያ ባንክ የተቻላቸውን ሁሉ አድርገዋል ብዬ አምናለሁ፤›› ብለዋል፡፡
የደቡብ ግሎባል ባንክ ፕሬዚዳንትነታቸውን ያስረከቡት አቶ ወርቁ ለማ

አቶ አዲሱ በበኩላቸው፣ ወደ አቢሲኒያ ባንክ ሲመጡ ብዙዎች ባንኩ አስቸጋሪ ነው ብለዋቸው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ሆኖም በጋራ መሥራት ውጤታማ እንደሚያደርግ ስለሚያምኑ በዚህ እምነት በጋራ በመሥራት ውጤት ሊመጣ መቻሉን ገልጸዋል፡፡ አቶ አዲሱ ጨምረው እንደገለጹት፣ እርሳቸው ሰባተኛ የባንኩ ፕሬዚዳንት መሆናቸውና ከዚህ ቀደም ባንኩን ካገለገሉ ፕሬዚዳንቶች በተለየ መንገድ በምሥጋናና በሽልማት መሸኘታቸው አስደስቷቸዋል፡፡
ከተሰጣቸው ገንዘብና ሽልማት በላይ ለተደረገላቸው የክብር አሸኛኘት ምሥጋና አቅርበዋል፡፡ እንደተባለውም የአቶ አዲሱ የሽኝት ፕሮግራም ከዚህ ቀደም በባንኩ ያልተከናወነ እንደነበር ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ 
ሆኖም አቶ አዲሱ ውጤታማ ሆነውበታል ከተባለው የአቢሲኒያ ባንክ ፕሬዚዳንትነታቸው ለምን ለቀቁ? የሚለው ጥያቄ የእርሳቸው መልቀቂያ ደብዳቤ ከቀረበበት ዕለት ጀምሮ ሲያነጋግር ነበር፡፡ 
ለመልቀቃቸው የተለያዩ ምክንያቶች ቢሰጡም፣ አቶ አዲሱ በፈቃዳቸው ያደረጉት መሆኑን በሽኝት ፕሮግራሙ ላይ ተናግረዋል፡፡ የባንኩ ቦርድም ይህንን አጠናክሯል፡፡
አቶ አዲሱ ቀጣይ ማረፊያቸው የት እንደሚሆኑ በዕለቱ ፕሮግራም ላይ በግልጽ ማስመጥ ባይፈልጉም፣ ታማኝ ምንጮች ግን የአቶ አዲሱ ቀጣይ ማረፊያ ደቡብ ግሎባል ባንክ እንደሆነ ይጠቁማሉ፡፡ ከአቢሲኒያ ባንክ በተመሳሳይ የኃላፊነት ቦታ ወደ ደቡብ ግሎባል ባንክ ለማቅናት ያስችላቸው ዘንድም፣ ደቡብ ግሎባል ባንክ አቶ አዲሱ ለባንካችን ፕሬዚዳንት ይሁኑልኝ ብሎ በማጨት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጥያቄ ማቅረቡን ለማወቅ ተችሏል፡፡ 
የአቶ አዲሱን ከኃላፊነት መልቀቅ ተከትሎ የአቢሲኒያ ባንክ ቦርድ አቶ ሙሉጌታ አስማረን የባንኩ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት አድርጐ ሰይሟል፡፡ 
ይህ በእንዲህ እንዳለ ላለፉት ሁለት ዓመታት የደቡብ ግሎባል ባንክ ፕሬዚዳንት በመሆን ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ወርቁ ለማ ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ታውቋል፡፡ አቶ ወርቁ ከኃላፊነት የመልቀቃቸው ምክንያት ግልጽ ባይሆንም፣ እሳቸው ግን ከነሐሴ 23 ቀን 2006 ዓ.ም. ጀምሮ በገዛ ፈቃዳቸው ከኃላፊነታቸው መልቀቃቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ዝርዝር ጉዳዮችን ከመግለጽ የተቆጠቡት አቶ ወርቁ የሥራ መልቀቂያቸውን ቦርዱ አፅድቆልኛል ብለዋል፡፡
የአገሪቱን የፋይናንስ ኢንዱስትሪ የሚቆጣጠረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አቶ አዲሱ የደቡብ ግሎባል ባንክ ፕሬዚዳንት እንደሆኑ የቀረበለትን ጥያቄ እያየው ሲሆን፣ ለጥያቄው አዎንታዊ መልስ ከሰጠ አቶ አዲሱ አቶ ወርቁን ተክተው የደቡብ ግሎባል ባንክ ፕሬዚዳንት ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ 
በዚህ ጉዳይ ላይ ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ አዲሱ ተጨማሪ ማብራሪያ ባይሰጡም፣ ኢንዱስትሪው ውስጥ እንደሚቆዩ አረጋግጠዋል፡፡ በሽኝት ፕሮግራሙ ላይም ከአቢሲኒያ ባንክ እንደማይርቁ፣ የአቢሲኒያ ባንክ ባለአክሲዮን ጭምር ስለሆኑ ግንኙነታቸው ጠንካራ እንደሚሆን ያመለከቱት አቶ አዲሱ፣ ‹‹በሌላ ቦታ ፕሬዚዳንትም ብሆን አቢሲኒያ ባንክን አልርቅም፤›› የሚል አነጋገር መጠቀማቸው፣ ‹‹ቀጣይ ጉዞዋቸው ደቡብ ግሎባል ባንክ ነው›› የሚለውን እምነት አጠናክሯል፡፡
ብሔራዊ ባንክ በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ለመሰማራት የሚያስፈልገውን ካፒታል ከ100 ሚሊዮን ብር ወደ 500 ሚሊዮን ብር እንዲያድግ ከመወሰኑ ቀደም ብሎ፣ በ100 ሚሊዮን ብር ካፒታል ከተቋቋሙ የመጨረሻዎቹ ሁለት የግል ባንኮች መካከል አንዱ ደቡብ ግሎባል ባንክ ነው፡፡ 
በወቅቱ ባንኩ ወደ ሥራ ሲገባ 138.9 ሚሊዮን ብር ካፒታል ይዞ በ5,481 ባለአክሲዮኖች የተመሠረተ ሲሆን፣ በመጀመሪያው የሥራ ዘመን አትራፊ ሳይሆን መቅረቱ ይታወሳል፡፡ ሆኖም በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ተኩል ግን ትርፍ ማስመዝገብ የጀመረ ባንክ ነው፡፡ 
_____________________________________________________
We welcome comments that advance the story through relevant opinion and data. If you see a comment that you believe is irrelevant or inappropriate, please! inform us. The views expressed in the comments do not represent those of Bloggers. 

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር