ኢትዮጵያና ሩሲያ ወታደራዊ ትብብራቸውን ለማጠናከር ተስማሙ

-  ልዩ ኢኮኖሚያዊ ትብብሮችን ለማድረግም አቅደዋል
ኢትዮጵያና ሩሲያ ለዓመታት የቆየ ትብብራቸውን በተለይም ወታደራዊ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ከመግባባት ላይ ደረሱ፡፡
ሁለቱ አገሮች የመግባባት ስምምነት ላይ የደረሱት የሩሲያው የረዥም ጊዜ ዲፕሎማትና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሰርጌይ ላቭሮቭ ባለፈው ሐሙስ ለአንድ ቀን የሥራ ጉበኝት አዲስ አበባ በመጡበት ወቅት ነው፡፡
ሰርጌይ ላቭሮቭ በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በደረሱበት ወቅት የተቀበሏቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ናቸው፡፡ በመቀጠልም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በሁለቱ አገሮች የጋራ ጉዳይ ላይ ከሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር መክረዋል፡፡
ከሁለቱ አገሮች ባለሥልጣናት ምክክር በኋላ ለጋዜጠኞች የተካሄደው ውይይት የገለጹት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሰርጌይ ላቭሮቭ፣ በተለያዩ የሁለቱ አገሮች የጋራ ትብብሮች ላይ መምከራቸውን፣ ከእነዚህም መካከል በወታደራዊ ትብብርና በልዩ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶች ለመተባበር መግባባታቸውን ገልጸዋል፡፡
ባለፈው ሐምሌ ወር የሁለቱ አገሮች ከፍተኛ ባለሥልጣኖች በጋራ ኮሚሽን ስብሰባ ላይ ተገናኝተው በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በኢነርጂ፣ ተደራራቢ ግብርን ለማስቀረትና የኢንቨስትመንት ጥበቃ ለማድረግ መስማማታቸውን የገለጹት ሰርጌይ ላቭሮቭ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ጋር ተግናኝተው በተነጋገሩብት ወቅት የተጠቀሱት የትብብር መስኮች በፍጥነት እንዲተገበሩ ለማድረግ መስማማታቸውን አስረድተዋል፡፡
ይህ ሲባል ሌሎች ጉዳዮች የሉም ማለት እንዳልሆነ የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ በተለይ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት መገለጫ ባህሪ የሆነው ወታደራዊ ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል መስማማታቸውን አስታውቀዋል፡፡
ዶ/ር ቴድሮስ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የሩሲያን ባለሀብቶች እንደምታበረታታ ለሚኒስትሩ መገለጹን በተለይ በኃይል አቅርቦትና በባቡር መስመር ዝርጋታ የተጀመረውን ትብብር ኢትዮጵያ እንደምታደንቅና ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንደምትፈልግ መገለጹን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከላይ ከተገለጸው በተጨማሪ የአበባና የሥጋ ምርት መዳረሻን ወደ ሩሲያ ማስፋት እንደምትፈልግና ለዚህም ይረዳ ዘንድ የሁለቱ አገሮችን በአየር ትራንስፖርት ማገናኘት ተገቢ መሆኑ እንደታመነበት፣ ይህንንም በፍጥነት ለመጨረስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሰርጌይ ላቭሮቭ ቃል መግባታቸውን ዶ/ር ቴድሮስ አክለዋል፡፡
ከዚህ ውጪ ሁለቱ አገሮች ኢትዮጵያ በምትገኝበት ቀጣና ስላለው ፖለቲካዊ ሁኔታ የተነጋገሩ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በሰላም ማስከበርና በማደራደር ረገድ እያደረገች ላለው እንቅስቃሴ ሩሲያ ከፍተኛ አድናቆት እንዳላት ተናግረዋል፡፡
‹‹በዓለም አቀፍ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመንቀሳቀስ የደረስንበትን መግባባት በድጋሚ አድሰናል፡፡ በተጨማሪም ግጭቶችን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት በተለይም የተናጠል የኃይል ዕምርጃ ላለመውሰድ ተግባብተናል፤›› ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያና የሩሲያ ግንኙነት በ17ኛው ክፍል ዘመን እንደተጀመረ ይነገራል፡፡ ከዚህ በኋላ በአፄ ምንሊክ ዘመን የሁለቱ አገሮች ግንኙነት የበለጠ እየተጠናከረ መሄዱን፣ ኢትዮጵያ በዓድዋ ጦርነት በጣሊያን በተወረረችበት ወቅት የሩሲያ ቀይ መስቀል ማኅበር የቆሰሉ አርበኞችን ለመርዳት እ.ኤ.አ. በ1896 ኢትዮጵያ መግባቱን  የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
የመንግሥታት መለዋወጥ ያልፈተነው የሁለቱ አገሮች ግንኙነት አሁንም መቀጠሉን የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይገልጻል፡፡
Source: http://www.ethiopianreporter.com/index.php/news/item/7343-%E1%8A%A2%E1%89%B5%E1%8B%AE%E1%8C%B5%E1%8B%AB%E1%8A%93-%E1%88%A9%E1%88%B2%E1%8B%AB-%E1%8B%88%E1%89%B3%E1%8B%B0%E1%88%AB%E1%8B%8A-%E1%89%B5%E1%89%A5%E1%89%A5%E1%88%AB%E1%89%B8%E1%8B%8D%E1%8A%95-%E1%88%88%E1%88%9B%E1%8C%A0%E1%8A%93%E1%8A%A8%E1%88%AD-%E1%89%B0%E1%88%B5%E1%88%9B%E1%88%99

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር