ከዋሳ (ቆጮ) የሚገኘውን ስታርች ለውጭ ገበያ ማቅረብ የሚያስችል ምርምር በመካሄድ ላይ ነው

Photo from http://letsdrivethere.wordpress.com/2013/04/18/enset-the-false-banana/
አዲስ አበባ መስከረም 3/2007 የእንሰት /ቆጮ/ ምርት ጥራትን በመጠበቅ ከውስጡ የሚገኘውን ስታርች ለተለያዩ አገልግሎቶች ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችል ምርምር እየተካሄደ መሆኑን ተመራማሪዎች ገለጹ።
ተመራማሪዎቹ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት የእንሰት ምርቷማነትን በማስፋት ቆጮን ከባህላዊ ምግብነት በተጨማሪ ለተለያዩ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ለኢንዱስትሪ ግብአት ሊውል ይችላል።
ቆጮ ከፍተኛ ስታርች ስላለው በሳይንሳዊ ዘዴ ቢመረት አገሪቱ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ከምታደርገው ሽግግር አንጻር በተለይ ለምግብ ኢንዱስትሪው ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው የሚሉት በኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሥነ-ምግብ ተመራማሪ የሆኑት አቶ ተመስገን አወቀ ናቸው።
በአገሪቱ የተለያዩ የምግብና የመድኃኒት ፋብሪካዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፉ በመምጣታቸው የእንሰትን ምርት አቅርቦትና ጥራት በማሳደግ ከምርቱ የሚገኘውን ስታርች ለኢንዱስትሪዎች በግብአትነት በማቅረብ ከፍተኛ ገቢ ማግኘት እንደሚቻል አስታውቀዋል።
በዚህም ለተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ከውጭ የሚገባውን የስታርች አቅርቦት ለመተካት እንሰትን በሳይንሳዊ ዘዴ ማምረት ያስፈልጋል ያሉት ተመራማሪው ከምግብነት በተጨማሪ ለመድኃኒት ፋብሪካዎችና ለሌሎችም ኢንደስትሪዎች ግብአትነት መጠቀም  እንደሚቻል አብራርተዋል።
በኢንስቲትዩቱ የተደረገ ጥናት እንደሚያመለክተው የእንሰት ምርት ለኢንዱስትሪ ግብአትነት ካለው ጠቀሜታ አንጻር ተፈላጊነቱ እጅግ ከፍተኛ ነው።
ለወደፊት የምርቱን አቅርቦት ከአገር ፍጆታ በተጨማሪ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችል ሥራ መከናወን እንዳለበት ጠቁመው የቆጮ ስታርች እንደ ቡና፣ ቆዳና ሌጦ ለአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ እንደሚያስገኝ አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትትዩት የግብርናና ሥነ-ምግብ ምርምር ቤተ-ሙከራዎች ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን አባተ በበኩላቸው ድርቅን መቋቋም የሚችለውና ከፍተኛ የምግብነት ይዘት ያለው እንሰት ስታርቹ ለኢንዱስትሪ ግብዓትነት እንደሚውል አስረድተዋል።
ከእንሰት ቆጮ፣ አሚቾና ቡላን በማዘጋጀት በተለያዩ ዝግጅቶች በአማራጭ ምግብነት በስፋት እየቀረበ በመምጣቱ በርካቶች እየለመዱት ነው።
እንሰት በጣም በትንሽ ውኃ በርካታ ምርት ሊሰጥ የሚችል ሰብል መሆኑን ጠቁመው ውኃ እንኳን ባይኖር ከሦስት እስከ ሰባት ዓመት የማይጠፋና ከሌሎች  የእርሻ ውጤቶች ጋር ሲነጻጸር በርካታ ምርት መሰጥ የሚችል ሰብል መሆኑን በጥናት ጭምር መረጋገጡን ተናገረዋል።
የምርምር ተቋሙ በሽታን የሚቋቋምና የተሻለ ምርት የሚሰጥ የእንሰት ዝርያ እያጠና መሆኑን ገልጸው ምርታማነትን በአማራጭ ቴክኖሎጂዎች ለማሳደግ ተቋሙ በትኩረት እየሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።
በመሆኑም በደቡብ ክልል ብቻ በስፋት የሚመረተውን የእንሰት ሰብል በሁሉም የአገሪቷ ክፍሎች እንዲስፋፋና ሁሉም ዜጎች  እንዲጠቀሙብት  ኢንስቲትዩቱ ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።�
ኢንስቲትዩቱ ጥራት ያለው የእንሰት ዝርያን በአገሪቱ ለማስፋፋት ከተለያዩ ትምህርትና ምርምር ተቋማት እንዲሁም መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በጋራ እየሰራ ይገኛል።
የዲላ ዩኒቨርስቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በቅርቡ የቆጮን ምርት በቀላል ዘዴ ጥቅም ላይ ማዋል የሚያሰችል አዲስ ቴክኖሎጂን ለአርሶ አደሩ እያስተዋወቀ መሆኑን ገልጿል።
ቆጮን በምግብነት ከሚጠቀሙ አገራት መካከል ኢትዮጵያን ጨምሮ ኬንያ፣ ዚምባብዌና ደቡብ አፍሪካ ይጠቀሳሉ።
Source: ENA

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር