የዩኒቨርሲቲ ሰልጣኝ ተማሪዎች ስልጠናው ግጭትን የሚያስነሳ በመሆኑ እንዲቆም ጠየቁ

 *ሰልጣኞቹ ፌስ ቡክ እንዳይጠቀሙ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል
ከነሀሴ 9 ጀምሮ በደብረማርቆስ ከተማ በደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ፣ ተክለኃይማኖት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ ቤተ መንግስት፣ መምህራን ኮሎጅና የደብረ ማረቆስ መሰናዶ ትምህርት ቤት ተከፋፍለው በአራት የሥልጠና ቦታዎች እንዲሁም 45 የውይይት ቡድኖች ስልጠና እየወሰዱ የሚገኙት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ስልጠናው ከፋፋይና ለትውልዱ ጎጅ በመሆኑ ሊቆም እንደሚገባ ማሳሰባቸውን ሰልጣኞቹ ለነገረ ኢትዮጵያ ገለጹ፡፡
ተማሪዎቹ በተለይም ‹‹የኢትዮጵያ ህዝቦች ትግልና የአገራችን ህዳሴ›› በሚል ህዝብን ከህዝብ ያጋጫል ያሉትን ያሉት ሰነድ ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ እንዳሰሙ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ተማሪዎች ‹‹እስር በእስር ለማናከስ የተዘጋጀ ሰነድ ነው፡፡ በመሆኑም ሰነዱ ሊቃጠል ይገባዋል፡፡ በቀጣይ ወደ ዩኒቨርሲቲ ስንገባ የሚያጋጨን ስለሆነ ስልጠናው በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል፡፡ የኦሮሚያ ተማሪዎችን አመጽ የቀሰቀሰው በዚህ የኢህአዴግ ከፋፍለህ ግዛ ሴራ ነው፡፡ ሰነዱ እንደሚለው ኢትዮጵያ ከታናሽንት ወደ ታላቅነት ሳይሆን ከታላቅነት ወደታናሽነት ነው የወረደችው፡፡ ለዚህ ከፋፋይ ሰነድ በርካታ ወጭ ወጥቶ እርስ በእርሳችን ለማናከስ ከሚጣር በገንዘቡ በየጎዳናው የወደቁ ኢትዮጵያውያንን ከርሃብ መታደግ ይችል ነበር፡፡›› በሚል ጠንካራ ተቃውሞ ማሰማታቸውን ገልጸውልናል፡፡
ተማሪዎቹ አክለውም ‹‹አጼ ምኒልክ በጊዜያቸው መልካም ስራ ሰርተዋል፡፡ ስህተት ሰሩ እንኳ ቢባል የዘመኑ ወጣቶች ያ ስህተት ላይ ተሳታፊዎች ባለመሆናችን የእኛም ስህተት ተደርጎ ከሌሎቹ ጋር ለማናከሻነት መዋል የለበትም፡፡ በዚህ ዘመን ህወሓት፣ ብአዴንና ሌሎቹ የኢህአዴግ አባላት እንጅ ህዝብ ነፍጠኛ ሊባል አይገባም፡፡ ብአዴን አማርኛ ተናጋሪውን አይወክልም፡፡›› ማለታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በተለይ ኢህአዴግ ስኬታማ እንደሆነ በሚገልጸው የሰነዱ ክፍል ላይ ካድሬዎች በየ እምነት ተቋማት ጣልቃ እየገቡ በመሆኑ የእምነት ነጻነት እንደሌለ፣ ጋዜጠኞች እየሰደዱ መሆንንና ሚዲያዎች በመዘጋታቸው ሀሳብን በነጻነት መግለጽ እንዳልተቻለ፣ የመድብ ፓርቲ እንደሌለና የኢህአዴግ አፋኝ መሆኑን በመግለጽ ሰነዱ ላይ የተጠቀሱት ስኬቶች በተግባር እንደሌሉ ተከራክረዋል፡፡
ትምህርትን በተመለከተ ሰነዱም ሆነ ኢህአዴግ በየጊዜው ያብጠለጥላቸዋል ያሏቸውን አጼ ምኒልክ ‹‹እኔ ቤት እንጀራ የለም፡፡ እንጀራ ያለው ትምህርት ቤት ነው
፡፡›› ብለው እንደነበር በማውሳት ከመቶ አመት በፊት ከነበረው ስርዓትም ያነሰ መሆኑን የተከራከሩ መኖራቸውን ምንጮቻችን ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም የትምህርት ስርዓት ከመቼውም ጊዜ በባሰ መውደቁ፣ ተማሪዎች ተመርቀው በተማሩት ዘርፍ ሳይሆን ኮብልስቶንን ጨምሮ ያልተማሩትን እንዲሰሩ መገደዳቸውንና ስራ አጥ መሆናቸውን በመግለጽ የትምህርት ስርዓቱን ውድቀት አስረድተዋል ተብሏል፡፡
በስልጠናው ወቅት ከኢህአዴግ ስኬት በስተጀርባ ዋናው ተዋናኝ ሆነው የቀረቡት አቶ መለስ ዋነኛ የመወያያ ርዕስ እንደነበሩና ተማሪዎችም ‹‹አማርኛ ተናጋሪውን አቶ መለስ አከርካሪውን መትተነዋል ብለዋል፡፡ አከርካሪውን ከተመታ አሁን ሌላ ከፋፍለህ ግዛን የሚያሰፍን ስልጠና ለምን አስፈለገ? የመለስን ራዕይ አሳካለሁ የሚለው ብአዴን አማርኛ ተናጋሪውን አይወክልም፣ ህዝቡን የሚሳደቡ ባለስልጣናት ምንም አይነት እርምጃ የማይወሰድባቸው ስርዓት ለህዝብ ንቀት ስላለው ነው፣ ኢህአዴግ ራሱ ዘረኛ ነው፡፡›› በሚል ተቃውሟቸውን ገልጸዋል፡፡ ስልጠናው ወጣቱ ኢህአዴግ የያዘውን የተሳሳተ መስመር ለማስያዝ የሚጥርና የማይጠቅም በመሆኑ ሊቆም እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ በውይይቱ ወቅት ዝምታን የመረጡ ተማሪዎችም እንደ ወጣት ማንም አውቅልሃለሁ ሳይላቸውና ሳይፈሩ ስህተቱን እንዲቃወሙ ማሳሰባቸው ታውቋል፡፡
በስልጠናው ወቅት አሰልጣኞች ተማሪዎች ፌስ ቡክ ውሸት በመሆኑ እንዳይጠቀሙ፣ ይህ ሳይሆን ቀርቶ ፌስ ቡክን በመጠቀማቸውና በፌስ ቡክ አማካኝነት በሚነሳ ብጥብጥና ሌሎች ችግሮች ምክንያት መንግስት በሚወስደው እርምጃ ተጎጅ እንደሚሆኑ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲዎች አባላት ናቸው ተብለው የተጠረጠሩ ተማሪዎች በስልጠናው እንዳይሳተፉ ጥረት ተደርጓል ያሉት ሰልጣኞቹ ‹‹አክራሪና አሸባሪ የሚባሉ አካላት መሳሪያ እንዳትሆኑ፣ ለእነዚህ አካላት መሳሪያ በመሆናችሁ የእርምጃው ሰለባ ትሆናላችሁ፡፡ መንግስት ተጠያቂ አይሆንም፡፡›› የሚል ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው ገልጸዋል፡፡ በስልጠናው ወቅትም ተቃዋሚዎች፣ ጋዜጠኞች፣ ፌስ ቡከኞች፣ መንግስት በእምነታቸው እንዳይገባ ኢትዮጵያውያን በአጥፊነት መፈረጃቸውንና ተማሪዎች ከእነዚህ አካላት መራቅ እንዳለባቸው ማስጠንቀቂያ አዘል መልዕክት መተላላፉን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ተማሪዎች በበኩላቸው ‹‹በአሁኑ ወቅት ኢህአዴግ ሚዲያውን እያፈነ ነው፣ ተቃዋሚዎችን እያሰረ ነው፣ በእምነት ጉዳይ ጣልቃ እየገባ ነው፣ የሚቀጥለውን ምርጫ ወቅት የእነዚህ ሁሉ ጭቆና ወደ አመጽ ቢያመራ ተጠያቂው ማን ነው? ለምን እንደ ሻዕቢያ በግልጽ አምባገነን መሆናችሁን አታውጁም? ህዝቦችን በየ አካባቢው እያፈናቀላችሁ ለምን ምኒልክን ትከሳላችሁ? ብሄራዊ እርቅን ለምን ትፈራላችሁ? የስልጠናው በጀት ይነገረን? ትራንስፎርሜሽኑ አልተሳካም፣ አባይ ግድብ የኢህአዴግ ፕሮጀክት ነው እና ሌሎችንም ጥያቄዎችና አስተያየቶች ማንሳታቸውን ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡
በደብረማርቆስ ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በአሰልጣኝነት ከተመደቡት መካከል አብዛኛዎቹ የገዥው ፓርቲ የካቢኔ አባላት እንደሆኑና በተለይ ታሪክ ላይ ያተኮረው የስልጠናው አካል በብአዴን አባላት ጭምር ቅሬታ እንዳስነሳ የነገረ ኢትዮጵያ ምንጮች ገልጸዋል፡፡
ነሃሴ 9 የጀመረው ስልጠና በሁለት ዙር ለ15 ቀናት የሚሰጥ ሲሆን በዋናነት የኢትዮጵያ ህዝቦች ትግልና የአገራችን ህዳሴ፣ የታድሶ መስመርና የኢትዮጵያ ህዳሴ፣ ልማታዊ ዴሞክራሲ ስርዓትና ፈተናው እንዲሁም ህገ መገንስታዊ መርህና የሰላማዉ ትግል ስልት የተሰኙ አራት ጥራዞችን ያካተተ እንደሆነ ታውቋል፡፡
በቀጣይ ቀናት ከሰልጣኞቹ የተላኩትን የስልጠኛ ሰነዶችና መረጃዎች እየተከታተልን ለአንባቢያን የምናደርስ መሆኑን እንገልጻለን፡፡
ምንጭ፡- ነገረ ኢትዮጵያ  እና ዘ ሐበሻ 
___________________________________________________
We welcome comments that advance the story through relevant opinion and data. If you see a comment that you believe is irrelevant or inappropriate, please! inform us. The views expressed in the comments do not represent those of Bloggers. 

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር