ያለሐኪም ትዕዛዝ የፀረ ተህዋስያን መድኃኒቶችን መጠቀምና ጠንቆቹ


መድኃኒት ማለት በሽታን ለመመርመር፣ ለመከላከል፣ ለማከምና ለመፈወስ የምንጠቀምበት ኬሚካል ነው፡፡ መድኃኒት ለበሽተኛ በሐኪም ትዕዛዝም ሆነ ያለሐኪም ትዕዛዝ ሊሰጥ ይችላል፡፡
ያለሐኪም ትዕዛዝ የሚሰጡ መድኃኒቶች በሽተኛው ላይ ብዙ የጎንዮሽ ጉዳቶች የሌሏቸውና በሽተኛው በሚፈልግበት ጊዜ በመድኃኒት ባለሙያው ድጋፍ፣ ምክርና መረጃ በመመርኮዝ የሚወስዳቸው ናቸው፡፡ 
በአገራችን ባለው የምግብ የመድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን መመርያ መሠረት ለራስ ምታት፣ ለጉንፋን፣ ለሆድ ቁርጠትና ለመሳሰሉት ቀላል ሕመሞች የሚወሰዱ መድኃኒቶች ያለሐኪም ትዕዛዝ ሊሸጡ የሚችሉ ናቸው፡፡ 
በሐኪም ትዕዛዝ (በማዘዣ ወረቀት) የሚሰጡ መድኃኒቶች፤ በባለሙያው ከፍተኛ ጥንቃቄ ተወስዶባቸው ካልታዘዙ በስተቀር በበሽተኛው ላይም ሆነ በማኅበረሰቡ ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትሉ ናቸው፡፡ በአግባቡ ካልተወሰዱም በሽታ አምጭው ተህዋስ መድኃኒቱን እንዲላመድ ያደርጋሉ፡፡ 
በሐኪም ትዕዛዝ ከሚወሰዱት መድኃኒቶች መካከል የፀረ ተህዋስያን መድኃኒቶች (Antimicrobials) ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ፀረ ተህዋስያን መድኃኒቶች የሚባሉት በቫይረስ፣ በባክቴሪያ፣ በፈንገስና በፕሮቶዝዋ አማካይነት የሚመጡ በሽታዎችን ለማከም የሚያገለግሉ ናቸው፡፡ 
ፀረ ተህዋስያን መድኃኒቶችን ያለሐኪም ትዕዛዝ መውሰድ ከሚያስከትላቸው ችግሮች መካከል አንዱና ዋነኛው የፀረ ተህዋስያን መድኃኒቶች መላመድ (Drug Resistance) ነው፡፡ አንድ የፀረ ተህዋስያን መድኃኒት በትክክለኛ መጠኑ ወይም የሰውነታችን ሴሎች ሊቋቋሙት በሚችሉት መጠን ወይም ከመጠኑ በላይ ተሰጥቶ ተህዋስያኑ የማይሞቱ ወይም መራባታቸውን የማያቆሙ ከሆነ ተህዋስያኑ መድኃኒቱን ተላመዱ ይባላል፡፡ 
የፀረ ተህዋስያን መድኃኒቶች መላመድ በዓለም አቀፍ በተለይም በታዳጊ አገሮች ያለችግር ነው፡፡ እነዚህ መድኃኒቶች ያለሐኪም ትዕዛዝ ከተወሰዱ በበሽተኛው ላይ ብቻ ሳይሆን በኅብረተሰቡ ላይ የሚያደርሱት ጉዳት ከፍተኛ ነው፡፡ 
ተህዋስያኑ መድኃኒቶቹን መላመዳቸው ከሚያስከትላቸው ችግሮች መካከል፤ በእነዚህ ተህዋስያን አማካይነት የሚመጡትን በሽታዎች በፀረ ተህዋስያን መድኃኒቱ ማዳን አለመቻል፣ በሽታው ለብዙ ጊዜ እንዲቆይ በማድረግ በሽተኛውን እስከ ሞት ማድረስና ፀረ ተህዋስያኑን የተላመዱ ተህዋስያን የያዘ በሽተኛ ለብዙ ጊዜ ታሞ ስለሚቆይና በሚንቀሳቀስበትም ጊዜ ሌላውን የኅብረተሰብ ክፍል መድኃኒቶቹን ለተላመዱት ተህዋስያን በማጋለጥ ከፍተኛ የሆነ ችግር ማስከተል ናቸው፡፡ ከመላመድ በተጨማሪ፣ ያለሐኪም ትዕዛዝ የፀረ ተህዋስያን መድኃኒቶችን መውሰድ ለጎንዮሽ ጉዳቶች (Side Effects)፣ ከሌሎች መድኃኒቶች ጋር አለመስማማት (Drug Interactions) እና መስጠት ለማይገባው በሽተኛ በመስጠት (Contraindications) ከፍተኛ ችግር ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡ 
ከሕግ አንፃር በአገራችንም ሆነ በዓለም ላይ ያለሐኪም ትዕዛዝ የሚሰጥ አንድም የፀረ ተህዋስያን መድኃኒት የለም፡፡ ነገር ግን በአገራችን  የፀረ ተህዋስያን መድኃኒቶች ያለሐኪም ትዕዛዝ (ያለ ማዘዣ ወረቀት) በተለያዩ የመድኃኒት ቤቶችና መደብሮች ሲሸጡ ይስተዋላሉ፡፡ በተለያየ ጊዜ የተካሄዱ ጥናቶች የፀረ ተህዋስያን መድኃኒቶች ያለሐኪም ማዘዣ እየተሸጡ መሆናቸውን ያመለክታሉ፡፡ ለምሳሌ፤ በ2000 ዓ.ም. በወራቤ ከተማ በስልጤ ዞን የተካሄደው ጥናት እንደሚያሳየው ያለሐኪም ትዕዛዝ መድኃኒት ከወሰዱት ሰዎች ውስጥ ከግማሽ በላይ (59.6%) የሚሆኑት የፀረ ተህዋስያን መድኃኒቶችን ተጠቅመዋል፡፡ በ2001 ዓ.ም. በጅማ ዩኒቨርሲቲ በጤና ሳይንስ ተማሪዎች ላይ የተሠራው ጥናት እንደሚያመለክተው ያለሐኪም ትዕዛዝ መድኃኒት ከወሰዱት ተማሪዎች መካከል 35.8% የሚሆኑት የፀረ ተህዋስያን መድኃኒቶችን ወስደዋል፡፡ በ1994 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ የተካሄደው ጥናት እንደሚያሳየው ያለሐኪም ትዕዛዝ ከተወሰዱት መድኃኒቶች ውስጥ 26.4% የሚሆኑት የፀረ ተህዋስያን መድኃኒቶች ናቸው፡፡ እንዲሁም በ2003 ዓ.ም. በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ በጤና ሳይንስ ኮሌጅ በተሠራው ጥናት መሠረት ያለሐኪም ትዕዛዝ ከተወሰዱት መድኃኒቶች ውስጥ 17.2% የሚሆኑት የፀረ ተህዋስያን መድኃኒቶች ናቸው፡፡ 
ጥናቶቹ የሚያመለክቱት በአገራችን ያለሐኪም ትዕዛዝ የሚወሰዱት የፀረ ተህዋስያን መድኃኒቶች መጠን ከፍተኛ መሆኑን ነው፡፡ በመሆኑም ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ያለሐኪም ትዕዛዝ የሚወሰዱ የፀረ ተህዋስያን መድኃኒቶችን በመከላከል ደረጃ የራሱን ድርሻ ሊወጣ ይገባል፡፡ 
የመድኃኒት ተጠቃሚው ያለሐኪም ትዕዛዝ የሚወሰዱ የፀረ ተህዋስያን መድኃኒቶችን ከብዙ አንፃር ጉዳት እንደሚያስከትሉ ተገንዝቦ ያለሐኪም ትዕዛዝ እነዚህን መድኃኒቶች ከመውሰድ መቆጠብ ይኖርበታል፡፡ 
የመድኃኒት ባለሙያው የሙያው ሥነ ምግባርና ሕጉ በሚያዘው መሠረት ሕዝቡን በአግባቡ ማገልገልና እነዚህን መድኃኒቶች ያለሐኪም ትዕዛዝ በመውሰድ የሚመጡትን ችግሮች መከላከል ይገባዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የሚመለከተው የመንግሥትም ሆነ መንግሥታዊ ያልሆነ አካል የእነዚህን መድኃኒቶች አጠቃቀም በተመለከተ የኅብረተሰቡን የዕውቀት ደረጃ ከፍ ለማድረግ የተለያዩ የመረጃ መስጫ መንገዶችን (ለምሳሌ ሬዲዮ፣ ቴሌቪዥን፣ ጋዜጣ፣ ኢንተርኔት፣ ወዘተ) በመጠቀም መረጃውን ማስፋፋት ይኖርበታል፡፡ 
ሁሉም የመድኃኒት ተጠቃሚ ያለሐኪም ትዕዛዝ የፀረ ተህዋስያን መድኃኒቶችን በመጠቀም የሚመጡ ችግሮችን ተገንዝቦ በጤና ባለሙያ ብቻ የታዘዘለትን መድኃኒት በአግባቡ በመጠቀም ራሱንና ኅብረተሰቡን መድኃኒቶችን ከተላመዱ ተህዋስያን ሊጠብቅ ይገባል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ በጤና ሳይንስ ኮሌጅ መምህርና የፋርማሲ ዲፓርትመንት ኃላፊ ናቸው፡፡ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜል አድራሻቸው tadele.eticha@mu.edu.et ማግኘት ይቻላል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር