‹‹በጣም የጎላ የብር ምንዛሪ ቅነሳ የምናደርግበት ምክንያት የለም›› አቶ ሬድዋን ሁሴን


መንግሥት በጣም የጎላ የብር ምንዛሪ ቅነሳ የሚያደርግበት ምክንያት እንደሌለ፣ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴን አስታወቁ፡፡ 
ሚኒስትሩ ባለፈው ሰኞ ከቀትር በኋላ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ የዓለም ባንክ የብር የመግዛት አቅም እንዲቀንስ የሰጠውን ምክረ ሐሳብ አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ ነው ይህንን የተናገሩት፡፡ 
የዓለም ባንክ እ.ኤ.አ. ጁላይ 22 ቀን 2014 የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ካቀረባቸው የመፍትሔ ሐሳቦች መካከል የብር የመግዛት አቅምን በመቀነስ፣ የአገሪቱን የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ማጎልበትና የውጭ ምንዛሪ ገቢን ማሳደግ እንደሚቻል መምከሩ ተዘግቧል፡፡ 
ይህንን ምክረ ሐሳብ ተንተርሶ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ሚኒስትሩ፣ ‹‹የቀረቡ አማራጮች በሙሉ አይተገበሩም፣ መንግሥት አጠቃላይ አማራጮችን ግንዛቤ ውስጥ አስገብቶና ትርፍና ወጪውን አገናዝቦ በአጠቃላይ ለኢኮኖሚው ይጠቅማል የሚለውን ዕርምጃ ነው የሚወስደው፤›› ብለዋል፡፡ 
መንግሥት በ2002 ዓ.ም. የብር የመግዛት አቅምን በአሥር በመቶ፣ በ2003 ዓ.ም. ደግሞ 20 በመቶ በመቀነስ ወደ ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ትግበራ መግባቱን አስታውሰዋል፡፡ 
‹‹ይህ የተደረገው በተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታ ውስጥ በመሆን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድን ለመተግበር በማቀድ ነው፤›› ብለዋል፡፡ መንግሥት የብር የመግዛት አቅምን ዝቅ እንዲል ከማድረጉ በፊት ስፋት ያለው የማክሮ ኢኮኖሚ ትንተና እንደሚያደርግ የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ‹‹አሁን ባለው ሁኔታ በጣም የጎላ የምንዛሪ ቅነሳ የምናደርግበት ምክንያት የለም፡፡ ተለቅ ያለ ቅነሳ አሁን ትክክለኛ ነው ተብሎ አይታሰብም፤›› ብለዋል፡፡ 
እ.ኤ.አ. ጁላይ 22 ቀን 2014 የወጣው የዓለም ባንክ ሪፖርትና ምክረ ሐሳብ ኢትዮጵያ አሁን ካለው የውጭ ምንዛሪ ምጣኔ ላይ አሥር በመቶ የብርን የመግዛት አቅም መቀነስ ብትችል፣ ከኤክስፖርት በምታገኘው ገቢ ላይ የአምስት በመቶ ጭማሪና በዓመታዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ የሁለት መቶ ጭማሪ እንደሚመጣ ያስረዳል፡፡ 
ኢትዮጵያ ይህንን ምክረ ሐሳብ ተቀብላ ተግባራዊ የምታደርግ ከሆነ የብር የመግዛት አቅም በሁለት ብር ገደማ ሊቀንስ እንደሚችል ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ አቶ ሬድዋን ጎላ ያለ የምንዛሪ ቅነሳ አይደረግም ከማለት ባለፈ መለስተኛ ቅነሳ ይኑር አይኑር የተናገሩት የለም፡፡ ይህንን ለማብራራትም ተጨማሪ ዕድል አልሰጡም፡፡ 
ምንጭ፦ ሪፖርተር ጋዜጣ

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር