24ኛው አገር አቀፍ አጠቃላይ የትምህርት ዘርፍ ጉባኤ በሀዋሳ ከተማ ተጀመረ

ሀዋሳ ነሐሴ 5/2006 በመላው ሀገሪቱ ጠንካራ የትምህርት ልማት ሰራዊት በመገንባትና ምርጥ ተሞክሮዎችን በማስፋት የትምህርት ተሳትፎና ጥራትን ለማሳደግ ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንዳለበት ትምህርት ሚኒስቴር አሳሰበ፡፡
24ኛው ሀገር አቀፍ አጠቃላይ የትምህርት ዘርፍ ጉባኤ” በመላው ህብረተሰብ የነቃ ተሳትፎ የትምህርት ልማት ግቦቻችንን እናሳካለን “በሚል መሪ ቃል ዛሬ በሃዋሳ ከተማ ተጀምሯል፡፡
በትምህርት ሚኒስቴር የአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፉአድ ኢብራሂም ጉባኤውን ሲከፍቱ እንደተናገሩት የሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች ህገ መንግስታዊ መብትና እኩልነት ከተረጋገጠ ወዲህ በራሳቸው ቋንቋ በመማር ባህላቸውን በትምህርት ለማሳደግና ለማስተዋወቅ በተፈጠረላቸው ምቹ ሁኔታ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡
ሁሉም ዜጋ ፍትሃዊ የትምህርት አገልግሎትን በነፃ እንዲያገኝ፣ የትምህርት ጥራት የሀገሪቱን ቀጣይ ተወዳዳሪ በሚያረጋግጥ ሁኔታ እንዲጠበቅ፣ በዘርፉ የተገኘውን ምርጥ ተሞክሮ በማስፋት ሂደቱን በተቀናጀ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ለማሳደግ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል፡፡
ለሀገሪቱ ልማት፣ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር መረጋገጥ ቁልፍ ሚና የሚጫወተውን ትምህርት በፍትሃዊነትና ጥራት ለሁሉም ዜጋ ለማዳረስ ባለፉት ዓመታት በተሰሩ ስራዎች አበረታች ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል፡፡
በዋናነት የትምህርት ጥራት ማረጋገጫ ፓኬጅ ተቀርጾ ተግባራዊ መደረጉ፣ ህብረተሰቡ የትምህርት ጉዳይ የኔ ጉዳይ ነው በሚል ስሜት በጉልበት፣በገንዘብና እውቀት በተጨማሪ በየትምህርት ተቋማት በመገኘት የሚያደርገው የድጋፍና ክትትል ስራ ቁልፍ ሚና መጫወቱን ገልፀዋል፡፡
መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ግለሰቦች በመንግስት ያልተሸፈኑ የትምህርት ስራዎችን ለማገዝ የትምህርት ተቋማት በመክፈት፣ የውስጥ ቁሳቁሶች በማሟላትና መምህራን በመመደብ ያበረከቱት አስተዋፅኦ ለለውጡ ከፍተኛ እገዛ ማድረጉን አስታውቀዋል፡፡
የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ወላጅ፣ መምህራን፣ አጋር አካላት በጋራ ባከናወኑት የተቀናጀ ጥረት የተመዘገበው ውጤት እጅግ አበረታች መሆኑን በመጠቆም ይህን የልማት ሀይል በመጠቀም ከድህነትና ኃላቀርነት በመላቀቅ የበለፀገና የተለወጠ ህብረተሰብ ለመፍጠር መረባረብ አለብን ብለዋል፡፡
የደቡብ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ በበኩላቸው የትምህርት ተደራሽነትን እውን ለማድረግ በተከናወኑ ስራዎች በክልሉ የአንደኛ ደረጃ አጠቃላይ የትምህርት ተሳትፎ ሽፋን ከአንድ መቶ በላይ ንጥር ተሳትፎ ከ88 በመቶ በላይ መድረሱን ተናግረዋል፡፡
ባለድርሻ አካላትን በተደራጀ የልማት ሰራዊት በማንቀሳቀስ የተመዘገበው ውጤት አጥጋብ መሆኑን ገልጸው በፈጠራ ስራ የተካነ ተመራማሪና ብቁ ዜጋ በብቃትና በጥራት ለማፍራት በቁርጠኝነት መስራት አለብን ብለዋል፡፡
ለሶስት ቀናት በሚካሄደው ጉባኤ ላይ የትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችን ጨምሮ የዘጠኝ ክልሎችና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች የትምህርት ቢሮ ኃላፊዎች፣ የሙያ ማህበራትና ተጋባዥ እንግዶች በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡
በሁሉም ክልሎች የ2006 እቅድ አፈፃፀምና በ2007 የትኩረት አቅጣጫ፣በትምህርት ልማት ግቦች አፈፃፀምና በሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ውይይት እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡
ምንጭ፦ ኢዜኣ
______________________________________________________________
We welcome comments that advance the story through relevant opinion and data. If you see a comment that you believe is irrelevant or inappropriate, please! inform us. The views expressed in the comments do not represent those of Bloggers.

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር