በአራት ቢሊዮን ብር ወጪ የሚስፋፋው ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ

ፎቶ ከሪፖርተር ጋዜጣ
ሐዋሳ ከተማ እንደ ዕድሜ ለጋነቷ ሁሉ በውስጧ አቅፋ የያዘቻቸው ከፍተኛ የትምህርት ተቋሞች ዕድሜ ከሁለት አሠርት ብዙም አይርቅም፡፡
ወንዶ ገነት ደንና ተፈጥሮ ኮሌጅን፣ ሐዋሳ ግብርና ኮሌጅን፣ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅንና ሌሎችን ጨምሮ የያዘው ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን በመጀመርያና በሁለተኛ ዲግሪ ሲያስመርቅ የዘንድሮው ለ15ኛ ጊዜ ነው፡፡ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዮሴፍ ማሞ እንደገለጹት፣ ዩኒቨርሲቲው ዘንድሮ ከሁሉም ተቋማቱ 4,276 ተማሪዎችን አስመርቋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ሲመሠረት በቅድመ ምረቃ የነበሩት ስምንት የሥልጠና መስኮች ሲሆኑ፣ በአሁኑ ወቅት መስኩን ወደ 67 አሳድጎ በድኅረ ምረቃ 52 ፕሮግራሞችን ከፍቷል፡፡ ከዚህ ውስጥ ሰባቱ የዶክትሬት (ፒኤችዲ) ዲግሪ ፕሮግራሞች ናቸው፡፡ ከመማር ማስተማሩ ሒደትና ተያያዥ ጥያቄዎችን በማንሳት ደረጀ ጠገናው የዩኒቨርሲቲውን ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዮሴፍ ማሞን አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከተቋቋመበት መሠረታዊ ዓላማና ከዕድሜው ለጋነት አኳያ ምን ያህል ኃላፊነቱን ተወጥቷል ማለት ይቻላል?
ዶ/ር ዮሴፍ፡- ዩኒቨርሲቲው አምስት ካምፓሶች ያሉት ሲሆን፣ በሰባት ኮሌጆችና በአንድ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የተደራጀ ነው፡፡ ከሐዋሳ ዋናው ግቢ፣ ግብርና ኮሌጅ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጆች በተጨማሪ፣ በይርጋለም የሚገኘው የሐዋሳ ካምፓስና ወንዶገነት ደንና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጆች የዩኒቨርሲቲው አካል ናቸው፡፡ በዚህ መነሻነት ዩኒቨርሲቲው ከተቋቋመበት መሠረታዊ መርሆዎች ማለትም መማር ማስተማር፣ ምርምር፣ የኅብረተሰብ አገልግሎትና የቴከኖሎጂ ሽግግር አኳያ በ2006 የትምህርት ዘመን ከመንግሥት በተመደበለት 1.2 ቢሊዮን ብር በጀት መጠነ ሰፊ ሥራዎችን አከናውኗል፡፡ ይኼውም ተቋሙ ሲመሠረት በቅድመ ምረቃ ከነበሩት ስምንት የሥልጠና  መስኮች ወደ 67 ያሳደገበት ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ማለት በድኅረ ምረቃ 52 ፕሮግራሞች የከፈተ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ሰባቱ የዶክትሬት (ፒኤችዲ) ዲግሪ ፕሮግራሞች ናቸው፡፡ ዩኒቨርሲቲው በዚህ ዓመትም በአጠቃላይ 4,276 ተማሪዎችን ሲያስመርቅ፣ ከዚሁ ውስጥ በቅድመ ምረቃ 3,847፣ በድኅረ ምረቃ ዲግሪ 429 ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡ ከተመራቂዎቹ ውስጥ በዩኒቨርሲቲው ታሪክ ከሌሎች ጊዜያት በተለየ መልኩ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ማለትም 219 የሕክምና ዶክተሮች አስመርቋል፡፡ ከ147 የፒኤችዲ ተማሪዎች ውስጥ በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ በፐብሊክ ሔልዝ አንድ ተማሪ አስመርቋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ሲመሠረት የነበረው 2,300 ተማሪ በአሁኑ ወቅት ወደ 30,570 አድጓል፡፡ ከዚህ ውስጥ 20,269 መደበኛ ተማሪዎች ናቸው፡፡ የመምህራን ቁጥሩንም ቀድሞ ከነበረበት 136 ወደ 1,373 አሳድጓል፡፡ ከመምህራኑ ውስጥ 67ቱ የውጪ አገር ዜግነት ያላቸው ናቸው፡፡ ዩኒቨርሲቲው በ2007 የትምህርት ዘመን 26,000 ተማሪዎችን በመደበኛው መርሐ ግብር ለመቀበል ያቀደ ሲሆን፣ ቀልጣፋና ዘመናዊ አሠራር ለመተግበር በሚዛናዊ ውጤት ተኮር (ቢኤስሲ) ሥርዓት የተቃኘ የአምስት ዓመት (ከ2005 እስከ 2009) ስትራቴጂክ ዕቅድ ነድፎም በመተግበር ላይ ይገኛል፡፡ 
ሪፖርተር፡- በሚዛናዊ ውጤት ተኮር ሥርዓት የተቃኘ ሲሉ የትምህርት ጥራቱን ከመጠበቅ አኳያ እንዴት ይገለጻል?
ዶ/ር ዮሴፍ፡- በአካዴሚክና መማር ማስተማር ረገድ ፕሮግራሙ ተቀርፆ በሥራ ላይ መዋል የጀመረው በተለይም ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ ነው፡፡ ይኼውም በሁሉም የትምህርት ዘርፎች ዩኒቨርሲቲው ተግባራዊ ያደረገው አዲሱን ተማሪ ተኮር የሞጁላር የትምህርት አሰጣጥ ዘዴና ተከታታይ የተማሪዎችን ውጤት ምዘና ሥርዓት ነው፡፡ ይህን አጠናክሮ በመቀጠል ከዚህ ቀደም ከትምህርታቸው ሊሰናበቱ ይችሉ የነበሩበትን የተማሪዎች ቁጥር መቀነስ ተችሏል፡፡ የትምህርት ጥራቱም በዚያው መጠን ማለት ነው፡፡ ሌላው መንግሥት በአገር አቀፍ ደረጃ የነደፈው 70 በመቶ የቴክኖሎጂና የተፈጥሮ ሳይንስ እንዲሁም 30 በመቶ በማኅበራዊ ሳይንስ የተማሪ ቁጥር ምጣኔ ሙሉ በሙሉ ተተግብሯል፡፡ ይህም የቴክኖሎጂ ተማሪዎች ድርሻ 40 በመቶ እንዲሆን አስችሏል፡፡ የተተገበረው የሞጁላር ትምህርት ሥርዓት ያስገኘው ውጤት ተጠንቶ፣ ጠንካራና ደካማ ጎኖች ተለይተው በዚያው አንፃር የመፍትሔ ዕርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ በተጨማሪም የትምህርት ጥራትን ለመጠበቅ ቀደም ሲል የተጀመረውን በኤሌክትሮኒክስ የታገዘ የትምህርት አሰጣጥና የመማሪያ ክፍሎችን በኤልሲዲ ፕሮጀክተር የማጠናከር ሥራ ተከናውኗል፡፡ ለመማር ማስተማር አጋዥ የሆኑትን የትምህርት ግብዓቶች ማለትም የማጣቀሻ መጻሕፍት፣ የቤተ ሙከራና ወርክሾፖችን አግባብነት ባላቸው ቁሳቁሶች የማሟላትና የውስጥ ፋሲሊቲዎችን የማደራጀት ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ 
ሪፖርተር፡- ለመማር ማስተማር እንቅፋት ተደርገው ከሚጠቀሱት ውስጥ የመሠረተ ልማት አለመሟላት ተጠቃሽ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ እንዴት ይገለጻል?
ዶ/ር ዮሴፍ፡- ዩኒቨርሲቲው በዚህ ረገድ በአገሪቱ ከቀደምት ተቋማት በበለጠ የተሟላ ተቋም ነው፡፡ በዚሁ መሠረት በ2006 ዓ.ም. በርካታ ግንባታዎች ተጠናቀው አገልግሎት እንዲሰጡ ከመደረጉ በተጨማሪ አዲስ የቴክኖሎጂ ካምፓስ ግንባታና ሌሎች በርካታ የግንባታ ሥራዎች በመገባደድ ላይ ናቸው፡፡ በአምስቱም ካምፓሶች በዚህ ዓመት በመገንባት ላይ ያሉ ግንባታዎችና በ2007 የሚጀመሩትን ጨምሮ ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው ናቸው፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን በ2006 ዓ.ም. የተማሪዎች እርስ በርስ የመማማር ዘዴ (Peer learning) እና የመምህራንና ሠራተኞች የትምህርት ልማት ቡድኖች እንዲዋቀሩ ተደርጓል፡፡ ይኼው በ2007 ዓ.ም. ተጠናክሮ እንዲቀጥል ይደረጋል፡፡
ሪፖርተር፡- የመምህራንን አቅም በመገንባት ረገድስ?
ዶ/ር ዮሴፍ፡- በአገር ውስጥና በውጪ አገር በሁለተኛና በሦስተኛ ዲግሪ በድምሩ ከ319 በላይ መምህራን የከፍተኛ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ፡፡ በተጨማሪም መምህራን በራሳቸው ተነሳሽነትና ጥረት የሚያገኙትን የከፍተኛ ትምህርት ሥልጠና ዕድል ዩኒቨርሲቲው ከመምህራን ልማት ዕቅድ አኳያ በማገናዘብ በመተግበር ላይ ይገኛል፡፡ በዚሁ መሠረት ባሳለፍነው ዓመት 80 መምህራን ትምህርት በማሻሻልና በምርምር ሥራዎች የደረጃ ዕድገት እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ ከነዚህ ውስጥ ሁለት መምህራን ሙሉ የፕሮፌሰርነት ማዕረግ አግኝተዋል፡፡ አዲስ የሚቀጠሩ መምህራን ማስተማር ከመጀመራቸው በፊት የማስተማር ክሕሎትን ለማዳበር እንዲችሉ የማስተማር ክሕሎት ላይ ያተኮሩ ሥልጠናዎች እንዲሰጣቸው ይደረጋል፡፡ መንግሥት የጀመረውን የልማት እንቅስቃሴ የጥናትና ምርምር ውጤት ለመደገፍ በዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብና ባለድርሻ አካላት የተገመገሙ 140 የምርምር ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡ በዚሁ መሠረትም 13 ዓይነት ቴክኖሎጂዎች ተሸጋግረዋል፡፡ 
ሪፖርተር፡- ለምሳሌ ቢጠቅሱልን?
ዶ/ር ዮሴፍ፡- የውኃ መሳቢያ፣ የማር መጭመቂያ፣ የእንስሳት መኖ መከትከቻ፣ የወተት መናጫና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም እየተከናወነ የሚገኘውን ምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግሩን ተደራሽ ለማድረግ በተለያዩ ወረዳዎች አሥር የቴክኖሎጂ መንደሮችን በማቋቋም በእነዚህ ወረዳዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ ነው፡፡ በተለይም የአካባቢውን ኅብረተሰብ የግብርና ምርትና ምርታማነት የሚያሻሽሉ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን የማስተዋወቅ፣ የማላመድና የማሰራጨት፤ ለምሳሌ ምርጥ ዘር፣ የአረም መከላከያ ዘዴ፣ ለዘመናዊ የእንስሳት እርባታ፣ ዘመናዊ ንብ ማነብ ቴክኖሎጂዎችን፣ በሰብል ምርቶች በተለይም በአገሪቱ ከፍተኛ እጥረት በሚታይበት በቢራ ገብስ ዘርና የእንስሳት መኖ ወዘተ ተከናውነዋል፡፡ በማኅበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ ተጠቃሽ ሊሆን የሚችለው ዩኒቨርሲቲው በርካታ የክልሉን የመንግሥት አመራሮች አቅም ለማጎልበት በተለያዩ የትምህርት መስኮች በሁለተኛ ዲግሪ አስመርቋል፡፡ አሁንም በማስተማር ላይ ይገኛል፡፡ ለአካባቢው ሥራ አጥ ወጣቶችና ጡረተኞች በሥራ ፈጠራና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ዙሪያ አጫጭር ሥልጠናዎችን ሰጥቷል፡፡
ሪፖርተር፡- ዩኒቨርሲቲው ዘንድሮ ካስመረቃቸው ተማሪዎች በተለይም የምሕንድስና ተማሪዎች ምርቃት የተከናወነው መርሐ ግብሩን ሳያሟሉ መሆኑ ይነገራል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የሲቪል ምሕንድስና ተማሪዎች ከመደበኛው ትምህርት በተጨማሪ የከተማ ምሕንድስናን ጨምረው እንዲወስዱ በመደረጉ ነው ይባላል፡፡ በሌላ በኩል በአምና ተመራቂ ተማሪዎች ላይ ቀጣሪዎች ‹‹ሲቪልና የከተማ ምሕንድስና የሚል ዘርፍ አናውቅም›› በማለታቸው ችግር መፈጠሩ ይወሳል፡፡ መፍትሔው ምንድን ነው? 
ዶ/ር ዮሴፍ፡- የምሕንድስና ትምህርት ፕሮግራሙ ሐዋሳን ጨምሮ በአራት ዩኒቨርሲቲዎች መካከል በተደረገ ስምምነት መሠረት የዳሰሳ ጥናት ተደርጎ የተጀመረ ነው፡፡ ምክንያቱም አንድ ተማሪ ሲቪልና የከተማ ምሕንድስና ቢያውቅ ጥሩ ነው የሚል ድምዳሜ ተወስዶ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲዎቹ ስምምነት ላይ የደረሱት፡፡ ለተማሪዎቹም ጠቀሜታ ሲባልም ነው ሆኖም ግን ኅብረተሰቡ ላይ በሰፊው የተለመደው ሲቪል ምሕንድስና ለብቻው የከተማም እንደዚያው ስለነበረ አምና በተመረቁ ተማሪዎች ላይ በተለይ ቅጥር ላይ ተፅዕኖ ፈጥሯል፡፡ ሁኔታው እንደገና ታይቶ ወደ ቀድሞ ፕሮግራም እንዲመለስ ተደርጓል፡፡ በዚሁም አራቱ ዩኒቨርሲቲዎች ለዘንድሮዎቹ ተመራቂ ተማሪዎች ከዚያ በፊት የሲቪል ምሕንድስና ትምህርታቸውን ወስደው፣ ነገር ግን የቀሩ ኮርሶችን በክረምቱ መርሐ ግብር እንዲወስዱና እንዲያሟሉ ውሳኔ ላይ ተደርሷል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎቹ በተስማሙበት መሠረት የጋራ ኮሚቴ አቋቁመው ካጠናቀቁ በኋላ የችግሩ ሰለባ የሆኑት ተማሪዎች የምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ታዳሚዎች እንዲሆኑ፣ ያም ሆኖ ግን የተማሪዎቹ ይፋዊ የምርቃት ሥነ ሥርዓት ሳይነገር እንዲቆይና በዚህ ክረምት የቀረውን ኮርስ እስከ ጥቅምት ድረስ አጠናቀው በልዩ ፕሮግራም እንዲመረቁ ይደረጋል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ግን ተማሪዎቹ በተጨማሪነት የወሰዱት የከተማ ምሕንድስና ትምህርት እንዲመዘገብላቸው ይደረጋል፡፡
ሪፖርተር፡- የዘንድሮ የተማሪዎች የምረቃ ሥነ ሥርዓት 15ኛው መሆኑ ቢነገርም ዩኒቨርሲቲው የዘንድሮውን ጨምሮ ሥነ ሥርዓቱ ለ37ኛ ጊዜ መሆኑን ደግሞ በሌላ ወገን የሚናገሩ አሉ?
ዶ/ር ዮሴፍ፡- ትክክል ነው፡፡ ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ አሁን ያለውን ይዘት ከመያዙ አስቀድሞ በግብርና ተፈጥሮ ሀብት የትምህርት ፕሮግራም ታሳቢ በማድረግ ያሠለጠናቸውን ተማሪዎች በዲፕሎማ መርሐ ግብር ሲያስመርቅ ቆይቷል፡፡ ነገር ግን ተቋሙ በቅድመና ድኅረ ምረቃ ሲያስመርቅ የዘንድሮው ለ15ኛ ጊዜ ነው፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር