የቡና ንግድ ቀይ መብራት በርቶበታል

ሚኒስትሮች ተሰብስበዋል፡፡ የሚኒስትሮቹ ጠቅላይ አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ስብሰባውን ይመራሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ሚኒስትሮችና ከዚያ በታች በተዋረድ የሥልጣን ዕርከን ላይ የሚገኙ 37 ሹማምንት ለስብሰባው ሲጠበቁ 25ቱ ተገኝተዋል፡፡
በሦስት ሚኒስቴሮች የኤክስፖርት አፈጻጸም ላይ በብሔራዊ ኤክስፖርት አስተባባሪውና የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ሚኒስትር በአቶ አርከበ ዕቁባይ (የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ይዘዋል) ጠሪነት ለአምስት ሰዓት የዘለቀ ስብሰባ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ተካሂዷል፡፡
ስብሰባው ከጥቂት ወራት በፊት የተካሄደ ነው፡፡ ከመነጋገሪያ ነጥቦቹ አንዱ የሆነው የንግድ ሚኒስቴር የኤክስፖርት አፈጻጸም ነበር፡፡ ከዚህም ውስጥ ቡና ላይ ትኩረት አድርጎ፣ ሌሎች የግብርና ምርቶችንም ተመልክቷል፡፡ ‹‹በንግድ ሚኒስቴር ክትትል የሚደረግባቸው የግብርና ምርቶች የኤክስፖርት ዕቅድ አፈጻጸም በተያዘው ዕቅድ መሠረት ለማሳካት የተከተልነው የአሠራር ሥርዓትና የማኔጅመንት አመራር ለውጥ ያላመጣው በምን ምክንያትን እንደሆነ አጽንኦት ተሰጥቶት ቢታይ፤›› የሚል መነሻ ያሰፈረው የመወያያ አጀንዳ፣ ከዚህ ቀደም በኤክስፖርት ብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚቴው በኩል የተሰጡ ማሳሰቢያዎችና የሥራ መመርያዎች ብዙም ለውጥ እንዳላመጡ ይገልጻል፡፡ 
ከቀረቡት ዝርዝር ነጥቦች መካከል ለአብነት መጥቀስ ቢያስፈልግ፣ ከዚህ ቀደም ኮሚቴው የኢትጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን፣ የንግድ ሚኒስቴር፣ የግብርና ሚኒስቴርና የፀጥታ አካላት በጋራ ተቀናጅተው በተለይ የቡና ኤክስፖርት ዕቅድ አፈጻጸምን ለማቀላጠፍ ይቻል ዘንድ፣ ቡና በብዛት ወደ ምርት ገበያ እንዲገባ በማድረግ የአቅርቦት መጠኑ እንዲጨምር የሚል መመርያ ሰጥቶ እንደነበር ያስታውሳል፡፡ ሆኖም ግን የተለየ ለውጥ አለመምጣቱን ለአባላት ሚኒስትሮችና ለሌሎች ሹማምንት ተነግሯቸዋል፡፡ ይህ የሆነው በወርኃ የካቲት የመጀመሪያዎቹ አሥር ቀናት ውስጥ ነበር፡፡ በተለይ በንግድ ሚኒስቴር ላይ ያጠነጠነው የወጪ ንግድ አፈጻጸም ውይይት፣ የተጠበቀው ውጤት አለመገኘቱን ኮሚቴው ትኩረት አድርጎበታል፡፡ 
ከወራት ቆይታ በኋላ ግንቦት ላይ ንግድ ሚኒስትሩ አቶ ከበደ ጫኔ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚኒስቴራቸውን የአሥር ወራት ዕቅድ አፈጻጸም አቅርበዋል፡፡ በጠቅላላ በአሥር ወራት ውስጥ አገሪቱ ከወጪ ንግድ ዘርፍ ታገኛለች ተብሎ የታቀደው መጠን 4.25 ቢሊዮን ዶላር እንደነበር ሆኖም ግን 2.61 ቢሊዮን ዶላር መገኘቱን ሚኒስትር ከበደ ተናግረዋል፡፡ ከታሰበው መጠን በግማሽ ያህል የቀነሰ ገቢ ያገኘበትን ምክንያት በሪፖርታቸው ሳያካትቱ፣ ካለፈው ተመሳሳይ ጊዜ አኳያ በ120.11 ሚሊዮን ብር ብልጫ ያስገኘ ገቢ መገኘቱን ጠቅሰዋል፡፡ 
ሚኒስቴራቸው ክትትል የሚያርግባቸው የግብርና ውጤቶችን በተመለከተ ሲናገሩም፣ 776,000 ቶን የሰብል ምርቶች ለውጭ ገበያ ቀርበው (የቁም እንስሳትን አይጨምርም) 1.14 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል ብለዋል፡፡ የታቀደው ግን 1.16 ሚሊዮን ቶን ምርቶችን በመላክ ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘት ነበር፡፡ ከዚህ ውስጥ የቡናን አፈጻጸም የተመለከተው ሪፖርታቸው እንዲህ አስረድቷል፡፡ 
በበጀት ዓመቱ አሥር ወራት ውስጥ ለዓለም ገበያ ይቀርባል ተብሎ ይጠበቅ የነበረው የቡና መጠን 207,000 ቶን ገደማ ነበር፡፡ ከዚህ መጠን ይገኛል የተባለው ገንዘብ ደግሞ 822 ሚሊዮን ዶላር ነበር (ሪፖርታቸው የቁጥር ስህተት አለበት ከዚህ ቀደም በወጡ አኃዞች መሠረት ዕቅዱ 882 ሚሊዮን ደላር ይገኛል የሚል ነው) ሁለቱም ሳይሳኩ ቀሩ፡፡ የተላከው መጠን 136,000 ቶን ላይ፣ የተገኘው ገቢም 489 ሚሊዮን ዶላር ላይ ተገድቧል፡፡ ለዓመቱ ይገኛል የተባለው የገቢ መጠን ሁለት ቢሊዮን ዶላር ነበር፡፡ ግማሹ ላይ እንኳ ለመድረስ አቀበት ሆኖበት ይታያል፡፡ ቡናው የታሰበውን ያህል ለምን አልተሸጠም? የሚል ጥያቄ ቢነሳ ሚኒስትሩ ምላሽ አላቸው፡፡ የሚፈለገውን መጠን ያህል ቡና ለገበያ ባለመቅረቡ፣ በዓለም ገበያ የቡና ዋጋ መዋዠቅ የተነሳ የሚፈለገውን ያህል ቡና ለውጭ ገበያ ባለመላኩ፣ በየደረጃው ያለው ፈጻሚ በቅንጅት ሊሠራ ባለመቻሉ፣ የኤክስፖርት ቡና በሕገወጥ መንገድ በአገር ውስጥ መሸጡና ወደ ጎረቤት አገሮች መውጣቱ፣ የኮንትሮባንድ ንግድን ለመከላከል በቂ ጥረት አለመደረጉን በምክንያትነት አቅርበዋል፡፡ ይህም ሆኖ እያንሰራራ የመጣው የዓለም ቡና ዋጋ የበጀት ዓመቱን ዕቅድ ለማሳካት ዕድል ሊሰጥ እንደሚችል ተስፋቸውን ገልጸው ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዕለታዊ የቡና ዋጋ መረጃዎች የሚያሳዩት ብዙም ተስፋ የሚሰጠውን ነገር አይደለም፡፡ ላለፉት ሦስት ወራት የነበረውን የተሻሻለው የገበያ ዋጋ ከምርት ገበያው መረጃዎች ማየት እንደሚቻለው፣ ከቀደሙት ጊዜያት ይልቅ በአብዛኛው እየቀነሰ የሚገኝ ዋጋ መሆኑን ነው፡፡  
በዚህ ዓመት ጥር ወር ላይ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር የ2005 በጀት ዓመትን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ይፋ አድርጎ ነበር፡፡ በሪፖርቱ ከተካተቱት ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ውስጥ የሸቀጦች የወጪ ንግድ አፈጻጸም ይገኝበታል፡፡ የወጪ ሸቀጦች ንግድ መጠን ከአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት አኳያ በ2007 ዓ.ም. መጨረሻ 15.6 ከመቶ እንደሚደርስና የወጪ ንግድ የገቢ መጠንም ስምንት ቢሊዮን በላይ ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅ ይዘረዝራል፡፡ 
በዚህ መሠረት በ2005 ዓ.ም. ወደ ውጭ ይላካል የተባለው ሸቀጥ የሚያስገኘው ገቢ አራት ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ሲሆን፣ የተገኘው ግን 3.1 ቢሊዮን ዶላር ነበር፡፡ ይህ መጠን በ2004 በጀት ዓመት ከተገኘው ገቢ በ2.5 ከመቶ ያነሰ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ለቅናሹ ምክንያት ከተደረጉት ውስጥ ቡና አንዱና ዋናው ነው፡፡ ቡናን ተከትለው ከታሰበው በታች ገቢ ያስገኙት ደግሞ ወርቅ፣ ቅባት እህሎች፣ አበባ፣ ቁም ከብት፣ ሥጋና የሥጋ ውጤቶች፣ እንዲሁም አትክልትና ፍራፍሬ በምርት አቅርቦት መቀነስ እንዲሁም በዓለም ዋጋ መውረድ ምክንያት የታሰበውን ገቢ ሊያስገኙ አልቻሉም፡፡ 
ከ2003 እስከ 2005 በነበሩት ሦስት ዓመታት ውስጥ የቡና የወጪ ንግድ ገቢ በአማካይ 806 ሚሊዮን ዶላር ነበር፡፡ በ2003 ዓ.ም. 841 ሚሊዮን ዶላር ተገኘ፡፡ እሰይ ተባለ፡፡ በቀጣዩ ዓመት 822 ሚሊዮን ዶላር ሲገኝ ብዙም የማያስከፋ ተብሎ ታለፈ፡፡ በ2005 ዓ.ም. ግን ወደ 745 ሚሊዮን ዶላር ዝቅ አለ፡፡ ይገኛል የተባለው መጠን ግን ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ነበር፡፡ ይኼኔ የ10.6 በመቶ ቅናሽ ተከሰተና የቡና ዓለም አቀፍ ዋጋ መውደቅ ሙሉ ለሙሉ ተጠያቂ ነው ተባለ፡፡ ከቡና ንግድ የተገኘው ገቢ ከጠቅላላው የወጪ ሸቀጦች ንግድ ገቢ አኳያ የቡና ድርሻ ወደ 24 ከመቶ ዝቅ ያለ ሆነ፡፡ ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር እንደሚዘረዝረው ቅናሹ በ2004 በጀት ዓመት ከነበረው 26.4 ከመቶ አኳያ ያነሰ መሆኑንም አስፍሯል፡፡ ይህንን ተከትሎ ሚኒስቴሩ አስተያየቱን ሰንዝሯል፡፡ 
‹‹በቀጣይ የቡና ግብይት ሥርዓቱን ይበልጥ ግልጽና ተወዳዳሪ በማድረግ ቡናን በጥራትና በብዛት ለውጭ ገበያ ማቅረብ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራበት የሚገባ ጉዳይ ይሆናል፤›› ብሎ ነበር፡፡ ይህ ግን ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ የቡናው የውጭ ገበያ መጠን ገቢም ብሶበት፣ ከሚጠበቀውም ከሚታሰበውም በታች ቀንሷል፡፡ በአሥር ወር ውስጥ የተገኘው ገቢና የተላከው ቡና መጠን ዝቅተኛነት በንግድ ሚኒስቴር ሪፖርት መነሻነት መጠቀሱን ልብ ይሏል፡፡ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር በ2005 ዓ.ም. የነበረውን የኤክስፖርት አፈጻጸም ሲገመግምና ሲያጠቃልል፣ ‹‹በአጠቃላይ በ2005 በጀት ዓመት የታየው የኤክስፖርት አፈጻጸም ከዕቅዱና ካለፈው ዓመት አፈጻጸም ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ ነው፡፡ ለኤስክፖርት አፈጻጸማችን ዝቅተኛ መሆን አንዱ ምክንያት ወደ ውጭ የምንልካቸው ሸቀጦች የዓለም ዋጋ በመውረዱ ሲሆን፣ በዋነኛነት ግን የወጪ ሸቀጦችን በዓይነት፣ በብዛትና በጥራት ማቅረብ ባለመቻላችን ነው፤›› ሲል ይደመድማል፡፡ 
ኢትዮጵያ ቡናን ለዓለም ያበረከተች አገር ናት፡፡ ከእረኛው ካልዲ አፈ ታሪክ  እስከ ከፋ ድረስ ያሉ ንግርቶች ኢትዮጵያ የቡና መገኛነቷን ይዘክራሉ፡፡ ቡናውም በጣዕሙ ከየትኛውም አገር ቡና ተመራጭ ስለመሆኑ ዓለም አቀፍ ተጠቃሚዎች፣ ነጋዴዎች፣ ደላሎች፣ ቡና አቅራቢ አገሮችም እንደሚገነዘቡት ይታወቃል፡፡ ልዩ ጣዕም ያላቸው፣ የፍራፍሬ ቃና ያላቸው ቡናዎች በኢትዮጵያ ይገኛሉ፡፡ 
ይህ ሁሉ ግን የኢትዮጵያ ቡና በሚፈለገው ደረጃ በዓለም ገበያ ውስጥ እንደልብ ለመሸጥና ብልጫ ያለው ዋጋ እንዲሰጠው አላስቻለም፡፡ ሌሎች ትልልቅ ቡና አቅራቢ አገሮችን ትተን የኬንያን እንኳ ብንመለከት፣ ከኢትዮጵያ ቡና በዋጋ በተሻለ ደረጃ ይሸጣል፡፡ በጣዕሙ ተወዳጅ የሆነው ኢትዮጵያዊው ቡና፣ በዓለም ገበያ ውስጥ በርካሽ መሸጡን ቀጥሏል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ የተሻለ ዋጋ የሚያገኘው የብራዚል ቡና ችግር ውስጥ ሲገባ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ 
የዓለም የቡና ገበያን በበላይነት የሚዘውረው የስታርባክስ ኩባንያ ወኪሎች ከጥቂት ወራት በፊት በኢትዮጵያ ጉብኝት አድርገው ነበር፡፡ ወኪሎቹ እንዳስታወቁት፣ በኢትዮጵያ ቡና አቅርቦት መጠን ላይ መተማመን ስለማይቻል ዋጋው ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ ራሱ ስታርባክስም በሚቀርብለት የቡና መጠን ደስተኛ አለመሆኑን አስታውቀዋል፡፡ አቅርቦቱ ያዝ ለቀቅ ስለሚበዛበትም ሌሎች አማራጭ ገበያዎችን መፈለግ ግድ ብሏል፡፡ በዚያም ላይ እንደ ኬንያ፣ ኡጋንዳና ቡሩንዲ ያሉት አገሮች የአገር ውስጥ የቡና ፍጆታቸው ከቁጥር የማይገባ በመሆኑና እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ ዓረቢካ ቡናን ስለሚያመርቱ፣ ያመረቱትን በሙሉ ለውጭ ገበያ በማቅረብ በኢትዮጵያ ላይ የበላይነት ለመያዝ አስችሏቸዋል፡፡ እርግጥ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚመረተው ቡና ውስጥ ከግማሽ ያላነሰው መጠን ለአገር ውስጥ ፍጆታ መዋሉም ለወጪ ገበያ አቅርቦት ማነስ ዋናው መንስዔ ይደረጋል፡፡ የአገር ውስጥ ፍጆታ ጠንካራ መሆን ገበሬውን በዓለም የቡና ዋጋ ውጣ ውረድ ምክንያት የሚደርስበትን ኪሳራ ለመከላከል አስችሏል በሚል የሚሞግቱም አሉ፡፡ ከስድስት ዓመት በፊት ከፍተኛ የተባለው የዓለም የሸቀጦች ዋጋ ቀውስ ወቅት እንደኬንያ ያሉት አገሮች የቡና ምርታቸውን ድባቅ ሲመታው ኢትዮጵያ ላይ የተፈጠረ ቀውስ አልነበረም፡፡ እርግጥ የሚጠበቀውን ያህል የወጪ ገበያና ዶላር ማግኘት ባይቻልም፣ ቡናው ግን ገበያ አጥቶ አገሪቱን ለጉዳት አልዳረገም፡፡ 
ከአምራች ገበሬው የቡና ምርት የሚሰበሰበሰው በሁለት መንገድ ነው፡፡ አንደኛው እሸት ቡና ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የደረቀ ቡና (ጀንፈል) ነው፡፡ እነዚህ ሁለት ዓይነት ቡናዎች ከየአካባቢው ተሰብስበው እየተመዘኑ ለአቅራቢዎች ይቀርባሉ፡፡ አቅራቢዎችም የተሰበሰበውን ቡና ለኢትዮጵያ ምርት ገበያ ያቀርባሉ፡፡
ለማዕከላዊው ገበያ የሚቀርበው ቡና የታጠበ ሆኖ ከነሸሚዙ ያለ ቡና ወይም ጀንፈል ከሆነ ደግሞ ገለባው ከላዩ ላይ ወጥቶለት ይቀርባል፡፡ ቡናው ከገበሬዎች  ከተሰበሰበ በኋላ በየዞኑ በሚገኙ መጋዘኖች ይከማቻል፡፡ በመጨረሻ አዲስ አበባና በየክልሉ በሚገኙ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ መጋዘኖች ይሰበሰባል፡፡ የቡና አቅራቢዎች ወደእነዚህ መጋዘኖች ሲያስገቡ፣ ቡናው ደረጃ ይወጣለታል፡፡ ከዚያም በኢትዮጵያ ምርት ገበያ አማካይነት ለቡና ላኪዎች በጨረታ ይቀርባል፡፡ ጨረታውን ያሸነፈ ቡና ላኪ ከውጭ ገዥዎች ጋር ባለው ስምምነት ላይ ተመሥርቶ ቡናውን ወደ ውጭ መላክ ይጠበቅበታል፡፡ 
ነገር ግን  ከአርሶ አደሩ ጀምሮ ለዓለም ገበያ እስከሚቀርብበት ድረስ ያሉት የገበያ ሰንሰለቶች በችግር የተሞሉ፣ በአሻጥር የተሸበቡ መሆናቸው ስለሚነገር፣ የአገሪቱን የቡና ንግድ መረጋጋት አሳጥተውታል፡፡ እነዚህን ችግሮች ለመፍታትም የመንግሥት ተነሳሽነት ይህ ነው በሚባል ደረጃ ያልተደራጀና አንዱ መሥርያ ቤት ከሌላው ያልተባበረ በመሆኑ፣ የዘርፉ ባለሙያዎች የአገሪቱ ቡና በዓለም ገበያ ውስጥ ያለው ሚና እየኮሰሰ እንደሚገኝ ይከራከራሉ፡፡ የዘርፉ ተዋናዮችም ሥጋት ውስጥ ገብተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቡና በተለይም ይርጋ ጨፌ፣ ሲዳማ፣ ሊሙና ሐረር የልዩ ጣዕም ወይም ስፔሻሊቲ ቡናዎች አምራች ናቸው፡፡ በአንፃሩ ጅማና በበቃን የመሳሰሉ አካባቢዎች ከፍ ያለ ዋጋ የሚቆረጥለትን የጫካ ቡና አምራቾች ቢሆኑም፣ በጥራትና በአቅርቦት ችግር ምክንያት ለቡናቸው ተገቢውን ዋጋ እንደማያገኙ የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ 
እሸት ቡና፣ ጥሬና ብስሉ ተቀላቅሎ በዘፈቀደ ከዛፉ ላይ የሚሸመጠጥ በመሆኑ፣ እንዲሁም ጀንፈል ቡና ደርቆ በሚፈጭበት ወቅት፣ አንዳንዴም ከመሬት እየተለቀመ የሚቀላቀለው ቡና፣ ለቡና ጥራት ዋነኛ ችግሮች ተብለው ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህ አሠራሮች በቡና ግብይት ወቅት ደረጃ በማውጣት በኩል ከፍተኛ ተፅዕኖ ያላቸው ናቸው፡፡ ድኅረ ምርት የቡና አያያዝ ኋላቀር መሆኑ በጅምላ የዓለም ቡና ገበያ ላይ ዋጋ የሚያስከፍል ነው፡፡ የተመረተው ቡና በተለያዩ በሽታዎች ከሚደርስበት ጥቃት ባሻገር፣ በድኅረ ምርት አያያዝ ጉድለት ምክንያት የሚባክነው ወይም ደረጃ የሚያጣው ቡናም ከፍተኛ መሆኑ ይነገራል፡፡ ላኪዎች በተደጋጋሚ የሚያሰሙት ስሞታ ለውጭ ገበያ የሚገዙት ቡና ከጋዝ፣ ከቅቤና ከሌሎችም የቡናን ጣዕም ከሚያበላሹ ባዕድ ነገሮች ጋር ተቀላቅሎ የሚቀመጥ በመሆኑ ጥራቱ እየተፈተነ ነው፡፡ 
የቡና ምርት በባለቤትነት የሚያስተዳድረው ግብርና ሚኒስቴር መሥራት ያለበትን ያህል ሠርቷል ለማለት እንደሚቸገሩ ቡና ላኪዎች ይናገራሉ፡፡ ነጋዴዎች ይህንን የሚገልጹት ከገዥዎቻቸው ጋር የሚነጋገሩበት ዋነኛው ጉዳይ ጥራት በመሆኑ ነው፡፡ የጥራት ችግር የጃፓንን ሰፊ ገበያ እንዳሳጣ የሚታወስ ነው፡፡ ምንም እንኳ አሁን ላይ ገበያው እያንሰራራ ቢሆንም፣ ከስድስት ዓመታት በፊት ወደነበረበት ደረጃ ለመመለስ ገና እየዳኸ ነው፡፡ ወደ ጃፓን በተላከ ቡና ላይ የፀረ አረም ኬሚካል በመገኘቱ ነበር ጃፓን ከኢትዮጵያ ቡና ላለመግዛት ወስና የቆየችው፡፡  
 ገበሬዎች ያቀረቡት ቡና ላይ ተመሥርተው ከገበሬው ሰብስበው ለማዕከላዊው ገበያ የሚያቀርቡት ነጋዴዎችም በቡና ጥራት ላይ ተመሥርተው የራሳቸውን ጥቅም ለማስከበር ሲሉ ችግር መፍጠራቸው አልቀረም፡፡ ባለሙያዎች እንደሚናገሩት፣ አቅራቢው ለኢትዮጵያ ምርት ገበያ የሚያቀርበው ቡና የተሻለ ደረጃ እንዲያገኝ የሚፈጥሯቸው አሻጥሮችም አሉ፡፡ አሻጥሮቹ ጉቦ በመስጠት የታጀቡ መሆናቸውም ይነገራል፡፡ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ደረጃ ተሰጥቶት አንደኛ ደረጃ ተብሎ የተሸጠ ቡና ዕውነትም አንደኛ ሆኖ የማይገኝበት ጊዜ ጥቂት ባለመሆኑ፣ ግዢውን ለፈጸሙ ቡና ላኪዎች ትልቅ ችግር እየፈጠረ ነው ይላሉ፡፡ 
ስፔሻሊቲ ቡና የሚልኩ ነጋዴዎችም ላይ ትችት ይሰነዘራል፡፡ ስፔሻሊቲ ቡና ለሚልኩ ነጋዴዎች ተብሎ የተፈጠረ የንግድ ሰንሰለት ባይኖርም ጥቂት ነጋዴዎች  በፈጠሩት ሕገወጥ አካሄድና በሚያቀርቡት አማላይ ጉቦ ያልተገባ ጥቅም እያገኙ ነው በሚል የሚወረፉ ናቸው፡፡ የሚልኩት መጠን አነስተኛ መሆኑ ግን ተጽኗቸው የጎላ እንዳይሆን ማድረጉን የሚናገሩ ባለሙያዎችም አልታጡም፡፡ 
እነዚህ ነጋዴዎች ገዥዎችን ከውጭ አስመጥተው እስከ ገበሬ ማሳ ድረስ ይወስዳሉ፡፡ ላመጡት ገዥ የቡናቸውን ዓይነት ከማሳየት ጀምሮ ያንኑ ቡና ያቀምሱታል፡፡ ገዥው ስምምነት ፈጽሞ፣ የተሻለ ገንዘብ በመስጠት ውል ፈርሞ ይሄዳል፡፡ እነዚህ ነጋዴዎች የራሳቸውን መንገድ ተጠቅመው ይኼንኑ ቡና በምርት ገበያ በኩል አሳልፈው ያገኙታል፡፡ ነጋዴዎቹ በሕገወጥ መንገድ በጥራት እንዲዘጋጅ ያደረጉትን ቡና ለማግኘት ከሚሠሯቸው በርካታ አሻጥሮች መካከል፣ የእነሱ ቡና ለምርት ገበያ ከመቅረቡ በፊት የተወሰነ ቡና ከምርት ገበያው ለመግዛት ይጫረታሉ፡፡ በዚህ ወቅት የሚያቀርቡት ገንዘብ ከገበያ ዋጋ በላይ የናረ ስለሚሆን ለቡና ዋጋ ወጣለት ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ የእነሱ ቡና ገበያ በቀረበበት ወቅት እነሱ ሆን ብለው ያቀረቡት የናረ ዋጋ መነሻ የመጫረቻ ዋጋ ሆኖ የሚሠራ በመሆኑና በዚህ ዋጋ ደግሞ ማንም ተጫራች ሊወዳደር ስለማይችል፣ በቀላሉ ራሳቸው ያዘጋጁትን ቡና መልሰው ያገኙታል ሲሉ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ከጉቦ ሌላ ነጋዴዎች የሚከተሉትን አሻጥር ያብራራሉ፡፡ 
በቡናው ዘርፍ አንጋፋዎቹ እንደሚያስረዱት ግን በቡና ላኪነት የማይታወቁ ሰዎችና ድርጅቶች መቀላቀላቸው ችግሩን አባብሶታል፡፡ ሌሎች ዕቃዎችን በማስመጣት የሚታወቁት እነዚህ ድርጅቶችና ግለሰቦች ከገበያ በላይ ዋጋ በማቅረብ ቡናውን ከአገር ውስጥ ገበያ ገዝተው ለውጭ የሚያቀርቡት ግን ከገዙበት ዋጋ በታች ነው፡፡ ይህም በአገሪቱ ያለውን የምንዛሪ ዕጥረት መነሻ በማድረግ ዶላር እንደልብ ለማግኘት ሲሉ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ፣ አዲሱ የቡናው ዘርፍ ፈተና መሆኑን በግልጽ ለመንግሥት እየተናገሩ ይገኛሉ፡፡ 
በዚህ ሒደት የዓለም የቡና ዋጋ ዝቅተኛ በመሆኑና የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የቡና ዋጋ ደግሞ ከፍተኛ መሆኑ እንቆቅልሽ ሆኖባቸው፣ ወይም አሻጥሩን መበጣጠስ ያልቻሉ በርካታ ነባር ቡና ላኪዎች ከጨዋታ ውጪ ከመሆን አልፈው ሥራቸውን እየለቀቁ መሆኑ በሰፊው እየተነገረም ነው፡፡ 
ይህ አሠራር የኢትዮጵያ የቡና ዋጋ በአገር ውስጥ ደረጃ ተሰቅሎ እንዲቀር የሚያደርግ በመሆኑ የተመረተ ቡና፣ ከአገር እንዳይወጣ ሰበብ እየሆነም ነው፡፡ ጣት የሚቀሰርባቸው ነጋዴዎች ግን ይህንን ያስተባብላሉ፡፡ ስማቸውን ለመግለጽ ያልፈለጉ አንድ በዚህ ተግባር የሚታሙ ቡና ላኪ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኩባንያቸው ከገበያ በላይ ዋጋ በመስጠት ኪሳራ ሳይሆን ትርፍ እያስተናገደ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ይህንንም አገር ውስጥ ገቢ በሚገባ የሚረዳው በመሆኑ በእውነተኛ መረጃ ላይ ያልተመሠረተ ሐሜት ነው ሲሉ ይከራከራሉ፡፡ 
ከዚህ መከራከሪያ ርቀው የሚሄዱና ይህ መረጃ እውነት ነው ብለው የሚያምኑ ቡና ላኪዎች እንደሚሉት፣ እነዚህ ቡና ላኪዎች አትራፊ መሆናቸውን አይክዱም፡፡ ነገር ግን አትራፊ የሆኑት በላኩት ቡና ሳይሆን፣ ወደ አገር አስገብተው በውድ በሚሸጡት ሸቀጣሸቀጥ አማካይነት መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ እነዚህ ነጋዴዎች ከቡና ንግድ የተገኘው ትርፍ ተለይቶ መረጃው ቢቀርብ እውነቱ ይወጣል የሚል ዕምነት አላቸው፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ ክርክሩ ቀጥሏል፡፡ የንግድ ሚኒስቴር የቡና ግብይት ኃላፊ አቶ ጌታሁን ቢረካ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በቡና ዘርፍ ግብይት በኩል በርካታ ችግሮች እንዳሉ ያምናሉ፡፡ ነገር ግን አንዳንድ የቡና ነጋዴዎች በዓለም ገበያ ላይ ሆነ ብለው ከስረው ይሸጣሉ በሚለው ጉዳይ ዕምነት እንደሌላቸው ቢገልጹም፣ የቡና ነጋዴዎች ተወዳዳሪ ዋጋ አይሰጡም የሚለው ግን ሚዛን እንደሚደፋባቸው አስረድተዋል፡፡
በዓለም ገበያ ውስጥ አንድ ሲኒ ቡና በውድ ገንዘብ ይሸጣል የሚሉት አቶ ጌታሁን፣ በዚህ ገበያ ለኢትዮጵያ የሚሰጠው ዋጋ በፍላጎትና አቅርቦት ላይ ተመሥርቶ ሳይሆን የቴክኒክ ይዘቶችን በማዛባት (በቴክኒካል ማኒፑሌሽንስ) መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ለኢትዮጵያ ቡና አስቸጋሪው በአቶ ጌታሁን ገለጻ መሠረት፣  የቡና ነጋዴዎች የመደራደር አቅም ውስንነት አንዱ ነው፡፡ ይህንን ችግር ለማስቀረት ልክ እንደ ብራዚልና ኮሎምቢያ የሚሠራ ጠንካራ የቡና ማኅበር አለመኖሩ፣ የቡና ጥራት ችግር፣ በውላቸው መሠረት ነጋዴዎች በወቅቱ አለመላክ ወይም ውል ማፍረስም (ዲፎልት) ተጠቃሽ ችግሮች ናቸው፡፡ ሚኒስቴሩ የቡና ችግሮችን አያውቃቸውም ማለት እንደማይቻል ግን አቶ ጌታሁን ይከራከራሉ፡፡ 
ኮሎምቢያ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ምርታማነቷን አሳድጋ በዓለም ገበያ ውስጥ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡ ቬትናም የዓለም የቡና ገበያ ላይ ትልቅ ድርሻ የያዘችው በጥቂት ዓመታት ውስጥ ነው፡፡ እንደ ብራዚል ሁሉ ኮሎምቢያም ጠንካራ የቡና ቦርድ በመፍጠሯ ገበያዋን በማይዋዥቅበት ደረጃ ላይ አድርሳለች፡፡ የሦስቱ አገሮች ትልቁ ብቃት ከፍተኛ የምርትና አቅርቦት አቅም መፍጠራቸው ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የዓለምን የቡና ዋጋ የሚወስኑ ሆነዋል፡፡ ኢትየጵያ በእነዚህ አገሮች አማካይነት የሚወሰነውን የገበያ ዋጋ ለመቀበል ትገደዳለች፡፡  
ኢትዮጵያ ከአንድ ሺሕ ዓመታት በላይ በቡና አምራችነቷ ብትታወቅም፣  የዓለም የቡና ግብይትን ፈጥና ብትቀላቀልም፣ ገበያውን ወደእሷ እንዲያደላ ማድረግ አልቻለችም፡፡ ይህ ቀርቶ ተገቢውን የቡና መጠን ማምረትና ማቅረብ ላይ ብዙ ምዕራፎችን መጓዝ ይጠበቅባታል፡፡ አንጋፋ ቡና ላኪዎች መላ አገሪቱ ለቡና ተስማሚ የሆነ የአየር ንብረት ስለሆነ፣ በቡና አብቃይነት የማይታወቁ አካባቢዎችም በገፍ እንዲያመርቱ ቢደረግ፣ ቢያንስ የአገር ውስጥ ፍጆታን በአዳዲሶቹ በመሸፈን ጥራት ያለው ቡና ለውጭ ገበያ ማቅረብ ይቻል እንደነበር ከመናገር ወደኋላ አይሉም፡፡  
በርካታ ነባር ነጋዴዎች ከጨዋታ እየወጡ፣ አብዛኛዎቹ ነጋዴዎች የሚያደርጉት ጠፍቶባቸዋል፡፡ ችግር ያለባቸው ነጋዴዎች ላይ ዕርምጃ እየተወሰደ አይደለም የሚል ቅሬታ በላኪዎች ዘንድ ይነሳል፡፡ ንግድ ሚኒስቴር በበኩሉ ከላኪዎች ጋር እጅና ጓንት ሆኖ እየሠራ፣ አብሮ እያቀደና ችግሮች ሲከሰቱም እየተመካከረ እየፈታ እንደሚገኝ ይገልጻል፡፡ ችግር ያለባቸው ነጋዴዎች ፊት ለፊት እየወጡ ማስተካከያ እንዲያደርጉ የሚደረገው በዘርፉ ተዋናዮች መሆኑን ሚኒስቴሩ ይናገራል፡፡
ዘርፉ ስላለበት ችግር ከዚህም፣ ከዚያም በሚመጡ ጥቆማዎች የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን እጁን በማስገባት ከወራት በፊት ከንግድ ሚኒስቴር  የእያንዳንዱ ቡና ላኪን የአምስት ዓመት የሥራ አፈጻጸም መረጃ ወስዷል፡፡
የሚኒስቴሩ ባለሙያዎች መረጃ ቢሰበስቡም በሰበሰቡት መረጃ ላይ ትንተና ተሠርቶ ይህ ነው የሚባል አስተዳደራዊ ዕርምጃ አልተወሰደም እየተባለ ነው፡፡
በርካታ ነጋዴዎች የፀረ ሙስና ኮሚሽን ወደ ዘርፉ መግባቱን እንደመልካም አጋጣሚ ተመልክተውት ነበር፡፡ ምክንያቱም የፀረ ሙስና ኮሚሽን ከሚኒስቴሩ የወሰደውን መረጃ ተንትኖ ዕርምጃ መውሰድ ከጀመረ ዘርፉ የመስተካከል ዕድል ይኖረዋል በሚል ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ዘርፉ ላይ ሊወሰድ የሚችለው ዕርምጃ በቅርብ ጊዜ ከተወሰዱ ዋና ዋና የሙስና ዕርምጃዎች አንዱ እንደሚሆን እምነታቸውን የሚገልጹም አልታጡም፡፡
የበጀት ዓመቱ ሊጠናቀቅ አንድ ወር እየቀረው፣ ይላካል የተባለው 206,825 ቶን ቡና አልወጣም፡፡ ሚኒስትር ከበደ በአሥር ወር ውስጥ 236,000 ቶን መላኩን ገልጸዋል፡፡ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ከ30,000 ቶን የበለጠ ቡና ሊላክ እንደማይችል መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የቡና ምርት በያመቱ የተወሰነ ዕድገት ቢኖረውም፣ በገቢ ደረጃ ግን ባለፉት ሦስት ዓመታት ቅናሽ እያሳየና ዘንድሮም ብሶበት ቀጥሏል፡፡
የቡና አርሶ አደር ያመረተውን ያህል ቢያመርትም፣ የተመረተው ምርት የውጭ ገበያ ከማግኘት ይልቅ መርካቶ ላይ እየተሸጠ፣ አገሪቱ ማግኘት ያለባትን የውጭ ምንዛሪ እንዳታገኝ አድርጓታል፡፡ ከዚህም ባለፈ በምርት ገበያና በሌሎችም መጋዘኖች ያለተግባሩ የሚከማቸው ቡና በየጊዜው እያሻቀበ ነው፡፡
ከዚህ በላይ በምርት ገበያ በኩል የሚታየው ሙስና እየተስፋፋ ስለመሆኑ ሪፖርት ቀርቧል፡፡ በቅርቡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ይህ ጉዳይ ቀርቦለታል፡፡ የማዕከሉ ጊዜያዊ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሽመልስ ሀብተወልድና ባልደረቦቻቸው ባቀረቡት ሪፖርት የምርት ገበያውን የግብይት ሕጎችና ሌሎች አግባብ ያላቸው ሕጎችን በተላለፉ 730 ጉዳዮች ላይ የምርመራ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡
ምርመራው ያተኮረው የምርት ገበያው አባላት፣ ደንበኞችና ተወካዮች በሚፈጽሟቸው ድርጊቶች ላይ ነው፡፡ ኃላፊዎቹ እንደገለጹት፣ 167 የገበያ መድረክ ተወካዮች፣ 28 የገበያው አባላትና 77 ደንበኞች ሕገወጥ ተግባር ላይ መሠማራታቸውን የሚያስረዳ መረጃ በመገኘቱ፣ በበጀት ዓመቱ አሥር ወራት ውስጥ ክስ ተመሥርቷል፡፡ በ218 ምርመራዎች ላይ ደግሞ የዲሲፕሊን ውሳኔዎች ተላልፈዋል ብለዋል፡፡ 
ኃላፊዎቹ የሕግ ጥሰት የሚመነጨው ገንዘብ ያላቸው የቡና ተገበያዮችና በቀላሉ ሙስና በሚያጠቃቸው ሠራተኞች አማካይነት ነው ይላሉ፡፡ ‹‹የቡና ዋጋ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዋጋው ቢቀንስም በኢትዮጵያ ግን ከፍተኛ በመሆኑ፣ ላኪዎች ወደውጭ ከመላክ ይልቅ ለአገር ውስጥ ገበያ ማቅረብን ይመርጣሉ፡፡ ለዚህም ከደረጃ አውጪዎች ጋር ይመሳጠራሉ፤›› ሲሉ ኃላፊዎቹ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ባለፈም አሻጥረኛ ነጋዴዎች ከከፍተኛ ኃላፊዎች ጋር በመመሳጠር ብዛት ያለውን የቡና ምርት ደረጃው ዝቅተኛ ከሆነ ቡና ጋር ደባልቀው ያቀርባሉ፡፡ ከዚህም ባለፈ ሆነ ብለው ጋዝ በነካው ሸራ በመሸፈን የቡናውን ደረጃ ያበላሻሉ ሲሉ ኃላፊዎቹ ይናገራሉ፡፡
ምርት ገበያው ካጋጠሙት ተግዳሮቶች መካከል በዋናነት የተቀመጠም በአንዳንድ ሠራተኞች የሚፈጸሙ ከሥነ ምግባር ውጭ የሆኑ ድርጊቶችና የሙስና አዝማሚያዎች መሆናቸውን አስቀምጧል፡፡
ንግድ ሚኒስቴር ዕርምጃ ወሰድኩ እያለ የሚናገረው ቡና ለመላክ ፈቃድ አውጥተው እስከዛሬ አላኩም ያላቸውንና በሕገወጥ መንገድ የቡና ጥራትና ቁጥጥር ግብይት አዋጁ ከሚፈቅደው ውጪ አከማችተዋል ባላቸው ነጋዴዎች ላይ ነው፡፡ ይህም በቂ ባለመሆኑ የቡናው ችግር ባለበት እየቀጠለ ከመሆኑ በቀር ያመጣው ለውጥ እንደሌለ እየተነገረ ነው፡፡
 ንግድ ሚኒስቴር ቡናን ለመምራት ተቸግሯል የሚሉ ወገኖች፣ ራሱን የቻለና ቡናን የሚያስተዳደር ተቋም ያስፈልጋል ይላሉ፡፡ ሚኒስቴሩ ይህንን አምኖ ጥናት አስጠንቶ አማራጭ መዋቅር ቢቀርብለትም፣ እስካሁን ተጨባጭ እንቅስቃሴ በማድረግ ተቋሙን በአፋጣኝ ዕውን ለማድረግ አልቻለም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማኅበር ከጥቂት ቀናት በፊት ያፀደቀው የሥነ መግባር ደንብ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም እየተገለጸ ነው፡፡ ምክንያቱም በቡና ንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ አካላት ለሥነ ምግባር መርሆዎች ተገዥ ሆነው ሥራቸውን እንዲሠሩ ከማድረጉም በላይ ውል በሚያፈርሱ ወይም ዲፎልት በሚያደርጉ፣ የራሳቸውን ጥቅም ብቻ በማሰብ ያልተገባ ችግር የሚፈጥሩ ነጋዴዎችን ይገራል የሚል ዕምነት ተጥሎበታል፡፡ ከዚህ ባለፈም ነጋዴዎቹ አንድ ላይ በቡድን እየወሰኑ ንግዱን ቢያካሂዱ በዓለም ገበያ ውስጥ የመደራደር አቅም ስለሚኖራቸው፣ የአገሪቱ ቡና ጥሩ ዋጋ የማግኘት ዕድሉ ከፍ ይላል የሚል ዕምነት አለ፡፡ 
ነገር ግን ይህ የሥነ ምግባር ደንብ በማኅበሩ የተወሰኑ የቦርድ አባላት ብቻ የሚያዝ ከሆነ የቦርዱ አባላት ያልፈለጉትን ነጋዴ የሚጐዱበት መሣሪያ ሊሆን ስለሚችል ጥንቃቄ ሊደረግበት ይገባል የሚል ምክር ባለሙያዎች ይለግሳሉ፡፡ 
እነዚህ ጉዳዮች ተስተካክለው የሚቀጥሉ ከሆነ የኢትዮጵያ ቡና ትንሳዔ ስለሚሆን ከቡና ጋር ተያያዥ ሥራዎችን ለሚሠሩ 30 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ታላቅ የምሥራች ይሆናል የሚል ተስፋ አለ፡፡ 

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር