ችግር ለሚፈጥሩ ቡና ላኪዎች የሥነ ምግባር ደንብ ተዘጋጀ

ችግር የሚፈጥሩ የቡና ነጋዴዎች አደብ እንዲገዙ ያደርጋል የተባለ የሥነ ምግባር ደንብ ተዘጋጀ፡፡ ደንቡን ያዘጋጀው የኢትዮጵያ ኮፊ ኤክስፖርተርስ አሶሴሽን ሲሆን፣ ማኅበሩ በዚህ ሳምንት በጠራው ጠቅላላ ጉባዔ ደንቡን ያፀድቀዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ምንጮች ገልጸዋል፡፡ 
የተዘጋጀው የሥነ ምግባር ደንብ በተለይ ከውጭ አገር ገዥዎች ጋር የገቡትን የቡና ሽያጭ ስምምነት ውል የማያከብሩ ነጋዴዎች በአገሪቱ ቀጣይ የቡና ግብይት ላይ ሳንካ የሚፈጥሩ የቡና ኤክስፖርተሮችን ከጨዋታ ውጭ እንዲሆኑ ማድረግ የሚያስችል ዕርምጃ ለመውሰድ ከማስቻሉም በተጨማሪ፣ የሥነ ምግባር ችግር አለባቸው ተብለው የተፈረጁ ኤክስፖርተሮችን ጥቁር መዝገብ ውስጥ ያሳፍራል ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማኅበር ከሌሎች አገሮች የቡና ላኪ ማኅበራት፣ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተቋቋሙ የቡና ማኅበራት ጋር ግንኙነት ያለው በመሆኑ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ጥቁር መዝገብ ውስጥ የገባ የቡና ኤክስፖርተር እነዚህ ተቋማት በሙሉ እንዲያውቁት ይደረጋል ተብሏል፡፡ 
ይህም አጥፊ ከተባለው ኤክስፖርተር ጋር ቀጣይ ግብይት ማድረግ አደጋ እንደሚመጣ ጠቋሚ በመሆኑ የተፈረጀው ላኪ ችግር ውስጥ ይወድቃል ተብሏል፡፡ ማኅበሩ ጥቁር መዝገብ ውስጥ ያሰፈረው ቡና ላኪ በመንግሥት በኩልም ምርመራ ተካሂዶበት ለቅጣት እንደሚዳረግም ተገልጿል፡፡
በማኅበሩ የተዘጋጀው የሥነ ምግባር ደንብ የንግድ ሚኒስቴር፣ ግብርና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ምርት ገበያን ጨምሮ የተለያዩ የሚመለከታቸው አካላት አስተያየት እንዲሰጡበት ተደርጎ፣ የሰጧቸው አስተያየቶችም ተካተው የመጨረሻው ረቂቅ ተዘጋጅቷል፡፡ 
ነገር ግን የሥነ ምግባር ደንቡን በጥርጣሬ የሚመለከቱ ኤክስፖርተሮችም አሉ፡፡ እነዚህ ኤክስፖርተሮች እንደሚሉት፣ በሥነ ምግባር ደንቡ ላይ ከዚህ በፊት ውይይት አልተካሄደም፡፡ በዚህ ሳምንት የተጠራው ጠቅላላ ጉባዔ ከያዛቸው አጀንዳዎች መካከል አንዱ የሥነ ምግባር ደንቡን ማፅደቅ ነው፡፡ ‹‹ይህ ግን በፍፁም ሊሆን አይገባም›› በማለት ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የቡና ላኪ ተናግረዋል፡፡ 
ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ሌላ የቡና ላኪዎች ማኅበር አባል በበኩላቸው የቡና ዘርፉን ከችግር ሊያወጡ ከሚችሉ ዕርምጃዎች አንዱ ሥነ ምግባር በሌላቸው ላኪዎች ላይ ዕርምጃ መውሰድ ተጠቃሽ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የሥነ ምግባር ደንቡን ያልወደዱ ላኪዎች መኖራቸው አይቀርም ነገር ግን የግድ ተግባር ላይ መዋል አለበት በማለት ያስረዳሉ፡፡ 
‹‹በፍፁም ጊዜ ሊሰጠው አይገባም›› በማለት ደንቡ በአስቸኳይ ሊፀድቅ እንደሚገባ የማኅበሩ አባል ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ማኅበሩ 128 የቡና ላኪዎችን ያቀፈ ሲሆን፣ በአገሪቱ ደረጃ ደግሞ ከ250 በላይ ቡና ላኪዎች እንደሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ 

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር