በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ እየተገነባ ያለው ዘመናዊ ስታዲየም ዩኒቨርሲቲውን የሚያስተዋውቅና የማህበረሰብ አገልግሎትን የሚያጠናክር ማዕከል መሆኑ ተገለጸ

Photo from H.University website: Edited by Worancha Information Network
በሀዋሳ ዪኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ፤ በአንድ ጣሪያ ስር ሁሉን-አቀፍ አገልግሎት ሊሰጥ በሚችል መልኩ እየተገነባ ያለው ስታዲየም፤ ተማሪዎች በዙሪያው ባሉ መዝናኛ ማዕከላት ተጠቅመው የሚዝናኑበትና ትምህርታቸውንም ሊያጠኑ የሚችሉበት ማዕከል መሆኑን የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ቢዝነስና ዴቭሎኘመንት ምክትል ኘሬዚዳንት ኘ/ር ንጋቱ ረጋሳ ገለፁ፡፡ 
stad2የስታዲየሙ መገንባት ዩኒቨርሲቲው ከሁለት ዓመታት ወዲህ ለስፖርቱ ዕድገት የሰጠው ትኩረት ማሳያ ነው ያሉት ኘ/ር ንጋቱ፤ በከተማው የሚደረጉ ትላልቅ ዝግጅቶችን በማስተናገድ ረገድ ምቹ አማራጭ ሊሆን እንደሚችልና ጎን ለጎንም ዩኒቨርሲቲው የውስጥ ገቢውን ለማሳደግና የአከባቢውን ማህበረሰብ ለማገልገል የሚያመርታቸውን ምርቶች የሚያቀርብባቸው ሱቆች በስታዲየሙ ዲዛይን ውስጥ መካተታቸው ማዕከሉ ለየት ያለ ኮምኘሌክስ ያደረርገዋል ብለዋል፡፡  
በስፖርት ሳይንስ የተካኑ ባለሙያዎችን በማፍራት ለሀገሪቱ ስፖርት እድገት በትጋት እየሰራ ላለው ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ፤ ትልቅ ግብዓት እንደሚሆን የታመነበት ይህ ዘመናዊ የስፖርት ማዘውተሪያ ኮምኘሌክስ፤ ለአከባቢው የስፖርት ቡድኖችም የመወዳደሪያና የልምምድ አማራጭ በመሆን ዩኒቨርሲቲው የማህብረሰብ አገልግሎትን የበለጠ እንደሚያጠናክር የሚጠበቅ ሲሆን፤ እስካሁን ድረስ ለግንባታው 140 ሚሊዮን ብር ወጪ መደረጉን ኘ/ር ንጋቱ አስረድተዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ግንባታ ኘሮጀክት ጽ/ቤት ሥራ አስክያጅ የሆኑት አቶ ደንበሹ ነኤሬ በበኩላቸው የስታዲየሙን ግንባታ በማስመልከት በሰጡት ገለጻ¿ ዩኒቨርሲቲው በ2002 ዓ.ም የመንግስት ከፍተኛ ዩኒቨርሲቲዎችን ስፖርት ውድድር ለማዘጋጀት አምስት ሺህ ሰው እንዲይዝ ታቅዶ ግንባታው የተጀመረ ብሆንም፤ ከስፖረቱ ውድድር በኋላ የግንባታው ዲዛይን ላይ ማሻሻያ በማድረግ አሥራ አምስት ሺህ ተመልካቾችን እንዲይዝ ዲዛይኑ ተከልሶ በ2004 ዓ.ም በአዲስ መልክ የተጀመረው ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
stad1ዩኒቨርሲቲው ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል የመማር ማስተማር፣ የማህብረሰብ አገልግሎትና የዕውቀት ሽግግር ቁልፍ ተግባሮቹ ናቸው ያሉት አቶ ደንበሹ፤ እንደምርምር ስራዎቹ ውጤቶች ሁሉ፤ ዩኒቨርሲቲው በብዙ ወጪ የሚያስገነባቸው ማዕከላትም ማህብረሰቡን ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ እንዲከናወኑ ጽ/ቤታቸው በትጋት እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የስታዲየሙ ግንባታ በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ ቤት የተባለ አማካሪ ክተትልና ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ያስረዱት የኘሮጀክት ጽ/ቤት ሀላፊ፤ በዩኒቨርሲቲው ስር ባሉት ሌሎች ካምፓሶች የስፖርት ማዘውተሪያና ሌሎች አገልግሎት መስጫ ማዕከላትን ለመገንባት በቂ መሬት አለመኖሩን ገልጸው ችግሩን ለመቅረፍ ዩኒቨርሲቲው ከከተማው አስተዳደር ጋር በመነጋገር ላይ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የስታዲየሙ ግንባታ ስራ የወሰደው ተቋራጭ፤ የሳንታ ማሪያም ኮንስትራክሽን፤ ተወካይ የሆኑት አቶ ቢንያም ሽፈራው በበኩላቸው፤ ግንባታውን ጥራቱን በጠበቀ መልኩና በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ ድርጅታቸው እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ በአሁኑ ጊዜ የመቀመጫ ቦታዎችን ዝግጁ በማድረግና የስታዲየሙን ግራና ቀኝ የጥላ መቀመጫ ሥራዎችን በማጠናቀቅ ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በሀዋሳ ዪኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ ት/ት ከፍል ኃላፊ የሆኑት አቶ ብዙነህ ይርጋ የዚህ ዘመናዊ ስታዲየም ግንባታ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተቀመጠውን ብቁ የስፖርት ባለሙያዎችን በማፍራት ረገድ የጎላ ድርሻ እንደሚኖረው ጠቅሰው ዩኒቨርሲቲው በሀገር አቀፍ ደረጃ እስከ ማስተርስ ዲግሪ ድረስ ተቀብሎ ከሚያሰለጥናቸው ባለሙያዎች በተጨማሪ፤ ከደቡብ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ጋር በመሆን በክልሉ ካሉ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች በርካታ ባለሙያዎችን ተቀብሎ በመጀመሪያ ዲግሪና በሁለተኛ ዲግሪ ስልጠናውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልና በአሁኑ ወቅትም በዋና ዋና ስፖርቶች የአሰልጣኝነት ስልጠናዎችን በመስጠት ላይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
እየተገነባ ያለው ዘመናዊ ስታዲየም አሥራ አምስት ሺህ መቀመጫ ያለው በመሆኑ፤ ከሀዋሳ ከተማ አልፎ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄዱ ማንኛውንም ስፖርታዊና ተዛማጅ ዝግጅቶችን ማካሄድ እንደሚችል ታውቁዋል፡፡


ምንጭ፦ የዩኒቨርሲቲው ድህረ ገጽ

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር