በሙስና ወንጀል ተከሰው በሲዳማ ዞን ከፍተኛ ፍርድቤት በነጻ የተለቀቁት ግለሰቦች በቀረበባቸው የይግባኝ አቤቱታ ጥፋተኛ ተባሉ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 27 ፣ 2006 (ኤፍ.ቢ.ሲ.) በሙስና ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸው በሲዳማ ዞን ከፍተኛ ፍርድቤት በነጻ የተለቀቁት የቀድሞው የክልሉ ውሃ ቢሮ ምክትል ሃላፊ ፥ ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድቤት በቀረበ የይግባኝ አቤቱታ ጥፋተኛ ተባሉ ።
ተከሳሾቹ  የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ ውብሸት ጸጋዬ ፣ መሃንዲሶቹ ማጊሳ ዮሃንስ እና አቦሰጥ መብራቱ እንዲሁም የግዥና ፋይናንስ ንብረት አስተዳደር የስራ ሂደት መሪው ይገረሙ ፋሲቆ እና ኮንትራክተሩ ተክለወልድ ማሞ ናቸው።
የኮሚሽኑ አቃቤ ህግ ሃዋርያት ሃደሮ እንደተናገሩት ፤ ተከሳሾቹ ጥፋተኛ የተባሉት ከ 40 በመቶ በታች የተከናወነ የውሃ ፕሮጀክት ሙሉ በሙሉ ተጠናቋል በማለት መንግስት ከ2 ሚሊየን ብር በላይ እንዲያጣ በማድረጋቸው ነው።
ኮንትራክተሩ  በአቋራጭ ለመበልጸግ ላልሰራው ስራ ክፍያ ሲጠይቅ ሁለተኛው ተከሳሽ ማጊሳ ዮሀንስ የክፍያ ሰርተፊኬቱን ካዘጋጀ በኋላ 3ኛው ተከሳሽ አቦሰጥ መብራቱ ክፍያውን በማረጋገጥ ይገረሙ ፋሲቆም ገንዘቡን ከመንግስት ካዝና አውጥቶ ኮንትራክተሩ እንዲያገኝ አድርጓል።
4ኛው ተከሳሽ ይገረሙ ፋሲቆ የወንጀሉ ዱካ እንዳይገኝ የኮንትራክተሩን  ሙሉ መረጃ ከቢሮው እንዲጠፋም አድርጓል ነው የሚለው ክሱ።
የደቡብ ክልል ስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን አቃቤ ህግ ፥ ይህንን ጭብጥ በመያዝ ለሲዳማ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ ሁሉንም ተከሳሾች የመንግስትን ስራ በማይመች አኳኋን መምራት በሚል የሙስና ወንጀል ከሷቸው ነበር።
ጉዳዩን ሲመረምር የቆየው ፍርድቤቱ በተያዘው አመት ታህሳስ ወር ላይ ሁሉንም ተከሳሾች በነጻ ያሰናብታቸዋል።
የዞኑ ከፍተኛ ፍርድቤት በሰጠው ውሳኔ ቅር የተሰኘው ኮሚሽኑ ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ያቀርባል።
የስር ፍርድ ቤት ውሳኔ የህግ ግድፈት አለበት ብሎ በማመኑ ጠቅላይ ፍርድቤቱ ያስቀርባል ማለቱን ተከትሎ ፥ በነጻ መሰናበታችሁ አግባብነት የለውም በማለት ባለፈው አርብ ሚያዚያ 24 ፍርድቤቱ ሁሉንም ጥፈተኛ ብሏቸዋል።
በጋዜጣ ሳይቀር ጥሪ የተደረገለት ሁለተኛው ተከሳሽ መሃንዲሱ ማጊሳ ዮሀንስ በሌለበት ጉዳዩ የሚታይ ሲሆን የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤተ በተከሳሾቹ ላይ የቅጣት ውሳኔ ለማስተላለፍ ለሚያዚያ 30 2006 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል።
ምንጭ፦ ኤፍ ቢ ሲ

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር