ሐሰተኛ ሪፖርቶች አያደናግሩን!

በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት አማካይነት የሚወጡ ሪፖርቶችን ለማመን የማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡
በአኃዝና በመቶኛ ሥሌቶች እየተቀናበሩ የሚቀርቡ በርካታዎቹ ሪፖርቶች በጥንቃቄ ሲታዩ በከፍተኛ ደረጃ መጣረሶች እንዳሉባቸው በቀላሉ እንረዳለን፡፡ ሌላው ቀርቶ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተለጠጡ የሚታቀዱ ኢኮኖሚያዊም ሆኑ ማኅበራዊ ዕቅዶች መነሻቸው የተሳሳቱ ሪፖርቶች ናቸው፡፡
መንግሥት የአምስት ዓመቱን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ይፋ ሲያደርግ ብዙዎች የፈሩት ዕቅዱ ያለመጠን መጋነኑን ነበር፡፡ አሁን ዕቅዱ በዝርዝር ሲታይ ከአምስት ዓመት በኋላ ይደረስበታል የተባለው ግብ በተጨባጭ ተግባራዊ አልሆነም፡፡ በተለይ እየተለጠጡ የሚወጡ ዕቅዶች ተጨባጩን ሁኔታ ስለማያገናዝቡ በመጨረሻ የሚገኘው ውጤት ከተጠበቀው በታች ይሆናል፡፡
ከዚህ ቀደም ለፓርላማ ይቀርቡ የነበሩ የመንግሥታዊ ተቋማት ሪፖርቶች እርስ በርስ የሚጣረሱ ከመሆናቸውም በላይ፣ ያለውን እውነታ በትክክል የሚገልጹ አልነበሩም፡፡ ፓርላማው አስፈጻሚውን የመንግሥት አካል ወጥሮ መያዝ ሲጀምር ግን  እንዲህ ዓይነቶቹ ሪፖርቶች ቀስ በቀስ ፓርላማው ዘንድ መቅረባቸው እየቀነሰ መጥቷል፡፡ ምንም እንኳን አሁንም አስገራሚ ሪፖርቶች እንደሚቀርቡ ቢታወቅም፡፡
በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን አማካይነት የሚቀርቡ አንዳንድ ሪፖርቶች ግን የሕዝቡን የማወቅ መብት የሚጋፉ ከመሆናቸውም በላይ፣ የተቋማቱን ዝርክርክነት የሚያጋልጡ ናቸው፡፡ ለምሳሌ በአንድ ወረዳ አንድ ጤና ጣቢያ እንደነበር ይነገርና ተጨማሪ አንድ ጤና ጣቢያ ሲገነባ የወረዳው የጤና አገልግሎት ሽፋን መቶ በመቶ አደገ ይባላል፡፡ አንድ ትምህርት ቤት ላይ ሌላ ትምህርት ቤት ሲጨመር ስታትስቲክሱ በዚህ ሁኔታ ተባዝቶ ይቀርባል፡፡
በፌደራል መንግሥት ደረጃ ስንሄድም ተመሳሳይ ሪፖርቶች እየወጡ ወረቀት ላይ ያለውና መሬት ላይ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ሲጣረሱ ይታያሉ፡፡ እነዚህ ጥቃቅን ነገሮች ከመላ አገሪቱ እየተደመሩ ይመጡና አጠቃላይ የአገሪቱን ምሥል ለማሳየት ይሞከርባቸዋል፡፡ በዚህ ጊዜ በተለያዩ አገልግሎቶች መጓደል ምክንያት ምሬት እየደረሰበት ያለው ሕዝብ ግራ ይጋባል፡፡ ይደናገራል፡፡
በውኃ፣ በኤሌክትሪክ፣ በስልክና በትራንስፖርት አገልግሎቶች መቆራረጥና አለመሟላት ምክንያት ሥራውና ኑሮው አሳር እያየበት ያለው ሕዝብ የአገልግሎቱ ተደራሽነት በዚህን ያህል በመቶ አደገ ወይም ደረሰ ሲባል ቀልድ የተያዘ ይመስለዋል፡፡ ለሳምንታት ውኃ አጥቶ የሚንከራተት ሕዝብ የውኃ ተደራሽነት ከዘጠና በመቶ በላይ ሆኗል ተብሎ ሲለፈፍበት እንዴት ይቀበላል? በኤሌክትሪክ ኃይል እጦት ምክንያት ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ማምረት እያቃተውና ሕዝቡ በጨለማ ሲሰቃይ ተደራሽነቱ ይህን ያህል ደርሷል ሲባል ማን ያምናል? በሌሎች ዘርፎችም ተመሳሳይ ማደናገሪያዎች ሞልተዋል፡፡
ከአዲስ አበባና ከተለያዩ ክልሎች ገበያዎች የተገኙ ተብለው የሚቀርቡ የሸመታ ዋጋዎች መጣረስ የሚያስገርሙ ናቸው፡፡ ጤፍ፣ በርበሬ፣ ጥራጥሬና የተለያዩ የግብርና ምርቶች ዋጋ በመገናኛ ብዙኃኑ ሲተነተን፣ በፍፁም ገበያ ውስጥ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ አያሳይም፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ማደናገሪያ ማንን እንደሚጠቅም አይገባንም፡፡
ሕዝቡ በመልካም አስተዳደር እጦት ምክንያት እየተንገላታ በየቦታው ምሬት በበዛበት በዚህ ወቅት፣ የመልካም አስተዳደር ተግዳሮቶች በመቀረፍ ላይ ናቸው ይባላል፡፡ በፋይሎች ላይ ውሳኔ መስጠት አቅቶት ወይም በቸልተኝነት አልወስንም ብሎ የሚኮፈስ ቢሮክራሲ ዜጎችን ሲያስለቅስ በአደባባይ እየታየ መፍትሔ እየተገኘ ነው የሚል ማደናገሪያ ሲቀርብ ያሳዝናል፡፡ ያሳፍራል፡፡
በፍትሕ ሥርዓቱ አካባቢም ሲታይ እየወጡ ያሉ መግለጫዎችና ሪፖርቶች የሚያስገርሙ ናቸው፡፡ ፍትሕ ዘገየብን፣ ፍትሕ ተነፈግን የሚሉ በርካታ ዜጎች ባሉበት አገር ውስጥ የፍትሕ ሥርዓቱ ተደራሽነት ወደር የለውም ዓይነት ሪፖርቶች ይቀርባሉ፡፡ ሕዝቡ በየፍርድ ቤቱ በተጓደለ ወይም በተነፈገ ፍትሕ ምክንያት ከላይ ታች ሲቅበዘበዝ እየታየ የማይመስል ነገር ይነገራል፡፡ በዚህ መስክ ያለው ማደናገር ራስ ያሳምማል፡፡
በአጠቃላይ በበርካታ ዘርፎች የሚወጡ ሪፖርቶች መሬት ላይ ካለው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር አልዛመድ እያሉ ናቸው፡፡ በአኃዝና በመጠን ሊገለጹ የማይችሉ ጉዳዮች ዕቅዳቸው ከነአፈጻጸማቸው ተቀባብተው ሲቀርቡ ከማደናገራቸውም በላይ ወዴት እየሄድን ነው ያሰኛሉ፡፡ ሪፖርቶቹን የሚያዘጋጁትም ሆኑ ተቀብለው የሚያስተጋቡት ወገኖች ምን ነክቷቸዋል ያስብላሉ፡፡ በእነዚህ አደናጋሪ ሪፖርቶች ላይ በመመሥረት የአገሪቱ ገጽታ ሊተነተን ሲሞከር ውዝግቦች ይፈጠራሉ፡፡
መንግሥት የአገሪቱን ኢኮኖሚ ዕድገት በሁለት አኃዝ በሚያቀርብበት ወቅት ከዓለም ባንክም ሆነ ከዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ጋር የነበረውን እሰጥ አገባ አንዘነጋም፡፡ አሁንም ቢሆን እየተጋነኑና እየተለጠጡ ከሚወጡ ዕቅዶች ጀምሮ እስከ አፈጻጸም ሪፖርቶች ድረስ የምናያቸው አደናጋሪ ነገሮች አንድ ሊባሉ ይገባል፡፡
የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ የሦስት ዓመታት ጉዞ ሲገመገም በቀረበው ሪፖርት ላይ የታዩት የቁጥር መጣረሶችና በአጠቃላይ የተገኘው ውጤት እንደ ማስተማሪያ ሊወሰዱ የግድ ይላል፡፡ በሪፖርቶች ውስጥ የሚደረደሩ ቁጥሮች በተጨባጭ መሬት ላይ ያለውን እውነታ መግለጽ ከተሳናቸው አደጋ ነው፡፡ በመሆኑም ሐሰተኛ ሪፖርቶች አያደናግሩን!

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር