ክትባት ለህጻናት እና እናቶች በሲዳማ

ሀዋሳ መጋቢት 10/2006 በሲዳማ ዞን የእናቶችና ህፃናት ጤና አገልግሎትን ተደራሽ በማድረግ የምዕተ ዓመቱን የጤና ልማት ግብ ለማሳካት በትኩረት እየሰራ መሆኑን የዞኑ ጤና መምሪያ አስታወቀ፡፡
በዞኑ በላፉት ስድስት ወራት ከ318 ሺህ ለሚበልጡ ህፃናት የተለያየ የበሽታ መከላከያ ክትባት ሲሰጥ ከ274 ሺህ የሚበልጡ እናቶች የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡
ለልጆቻቸው የሚሰጠው ክትባት ህፃናት ከበሽታ በመጠበቅ ጤናቸው የተሻለ እንዲሆን እንደረዳቸው እናቶች ገልፀዋል፡፡
በመምሪያው የጤና ልማት እቅድ ዝግጅት፣ክትትልና ግብረ መልስ የስራ ሂደት ኦፊሰር አቶ አበበ በካዬ እንደገለጹት የእናቶችና ህፃናትን የጤና አገልግሎት ተደራሽ በማድረግ የምዕተዓመቱን የጤና ልማት ግብ ለማሳካት በትኩረት እየሰራ ነው፡፡
ባለፉት ስድስት ወራት ዕድሜያቸው ከአንድ ዓመት በታች የሆኑ ሁሉም ህፃናት ክትባት እንዲወስዱ የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
በዚህም ባለፉት ስድስት ወራት በ19 ወረዳና ሁለት የከተማ አስተዳደሮች 318 ሺህ 715 ዕድሜያቸው ከአንድ ዓመት በታች የሆኑ ህፃናት የፖሊዮ፣ የቲቪ፣ የኩፍኝና የሳንባ ምች በሽታ መከላከያ ክትባት መሰጠቱን ገልፀዋል፡፡
ለህፃናት ሞት ምክንያት የሆነው የሳምባ ምች መከላከያ ክትባት በመደበኛ የክትባት አገልግሎት ውስጥ በማካተት 107 ሺህ 751 ህፃናት መከተባቸውን አስታውቀዋል፡፡
በወሊድ እድሜ ክልል ለ274ሺህ ሴቶች ይርጋዓለም ሆስፒታልን ጨምሮ ከ650 በሚበልጡ ጤና ጣቢያዎችና ጤና ኬላዎች የስነ ተዋልዶና ቤተሰብ ምጣኔ የአገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ወይዘሮ እቴነሽ ጋላናና ወይዘሮ አልማዝ ወርቁ ለህፃናት በሚሰጠው የበሽታ መከላከያ ክትባት ህፃናት ከበሽታ ተጠብቀው ጤናቸው የተስተካከለ እንዲሆን ከፍተኛ እገዛ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
በጤና ተቋማቱ የተጠቃሚውን ፍላጎት መሰረት ያደረገ የመድሃኒትና ህክምና አገልግሎት በነፃ መሰጠቱ ያለምንም ችግር ሴቶች የስነ ተዋልዶና ቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸው እንዳስደሰታቸው ገልፀዋል፡፡
ምንጭ፦http://www.ena.gov.et/

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር