የሃዋሳን ከተማ ነዳጅ ማደያዎችን ጨምሮ የነዳጅ ምርቶችን በአግባቡ በማያከፋፍሉ ኩባንያዎች ላይ መንግስት እርምጃ ሊወስድ ነው

አዲስ አበባ ፣ ጥር 27 ፣ 2006 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ሰሞኑን የቤንዚንና የናፍታ እጥረት በመዲናችን አዲስ አበባና በበርካታ የክልል ከተሞች ተከስቷል ።
በአንዳንድ አካባቢዎች እና ከተሞች ችግሩ አሁን ድረስ ያልተፈታ ሲሆን  ፥ በትራንስፖርት እንቅስቃሴው ላይም ከፍተኛ ጫናን እያሳረፈ ይገኛል ።
የቤንዚንና የናፍታ እጥረቱ በዋናነት በአዲስ አበባና በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል በሚገኙት ከተሞች  በሃዋሳ ፣ ሆሳዕና ፣ ወላይታ ሶዶ እና ሚዛን አማን ነው የተከሰተው ።
በሃዋሳ ከተማ ወደ 45 ሺህ ሊትር የሚጠጋ የነዳጅ ስርጭት እየተካሄደ እንደሚገኝና ይህም ቢሆን በቂ እንዳልሆነ የንግድ ሚንስትር ድኤታ አቶ ዓሊ ሲራጅ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።
በተቀሩት ከተሞች ማለትም  ሆሳዕና ፣ ወላይታ ሶዶ እና ሚዛን አማን ግን እጥረት መስተዋሉን ነው የጠቀሱት።
በተመሳሳይ በተለያዩ የመዲናችን አካባቢዎች በዚህ ሳምንት የነዳጅ እጥረት የተስተዋለባቸውን ምክንያቶች አቶ ዓሊ ሲራጅ የገለፁ ሲሆን ፥ በዋናነትም ሃላፊነቱ የተሰጣቸው የነዳጅ አከፋፋይ ኩባንያዎች ሀላፊነታቸውን በአግባቡ ባለመወጣታቸውና ነዳጁን ማከፋፈል በማቆማቸው የተፈጠረ ነው ብለዋል።
ዋናውና እጥረቱን ያባባሰው  ኩባንያዎቹ በወሩ መጨረሻ የነዳጅ ዋጋ ይጨምራል በሚል የተሳሳተ እሳቤ ቀደም ብለው በርካሽ የገዙትን ነዳጅ በውድ ዋጋ ለመሸጥ ካላቸው ፍላጎት የተነሳ እንደሆነ የገለፁት ሚንስትር ድኤታው ፥ ይሁንና ምንም አይነት የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ እንደሌለ ህብረተሰቡም ሆነ የነዳጅ አከፋፋዮች መረዳት እንዳለባቸው ነው የገለፁት።
በተጨማሪም ኦይል ሊቢያ ይጠቀምባቸው የነበሩ 48 ያህል ተሽከርካሪዎች ወደ ሌሎች ኩባንያዎች በመሄዳቸው ፤ የነዳጅ አቅርቦት እጥረቱ ከተሽከርካሪ እጥረት ጋር ተያይዞ መምጣቱን አውስተዋል።
በመሆኑም  በኢትዮጵያ  ነዳጅ ድርጅት በቂ ነዳጅ ያለው መሆኑን በመጥቀስ ፥  አሁን የተፈጠረውንም ችግር  በአጭር ግዜ ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል ።
ችግሩ መከሰት አልነበረበትም የሚሉት አቶ ዓሊ የአንዳንድ የነዳጅ ኩባንያዎች ድርጊት በትራንፖርት እንቅስቃሴው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ከመፍጠር በዘለለ ክፍለ ኢኮኖሚውን በእጅጉ የሚጎዳ በመሆኑ ፤ ይህን ድርጊት በሚፈፅሙ ኩባንያዎች ላይ አስፈላጊውን እርምጃ ሁሉ መንግስት ለመውሰድ እንደሚገደድ አስታውቀዋል።
http://www.fanabc.com/index.php?option=com_content&view=article&id=7405:2014-02-04-16-53-18&catid=102:slide

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር