ሃዋሳ «እኔን ነው ማየት» ትላለች

ሃዋሳ መሐል ከተማ ከአንዱ ግራር ሥር ቁጭ ብዩ የይርጋ ጨፌ ቡናን እያጣጣምሁ ነው። ሀዋሳ ሞቃት ብትሆንም ከሀይቋና ከከተማዋ ዛፎች የሚወጣው ንፋስ ሙቀቱን እንድትመክት አድር ጓታል። የመንገዶቿ ስፋትና ውበት ከንጽህነዋ ጋር ተደምሮ ዓይንን ይስባል። የመኖሪያ ቤቶችም ሆኑ የንግድ ህንጻዎቿ ውበቷ ልዩ ነው። እየተገነቡና ለግንባታ ቦታ የተከለላቸው ቦታዎች ከተማዋ በእቅድ እየተገነባች መሆኑን ያመለክታሉ። በአጠቃላይ ከተማዋ ወገቧን ይዛ «እኔን ነው ማየት የምትል ወይዘሪት» ትመስላለች። ይህን ያየ ምንው ሌሎቹ የአገራችን ከተሞች ከሃዋሳ ቢማሩ ያስብላል። የከተማዋ እንዲህ መሆን ምስጢር ምን ይሆን ብለው እንዲመረምሩም ያደርግዎታል።
እኔና ሌሎች የሥራ ጓደኞቼ በሥራ አጋጣሚ ሃዋሳ ሂድን ነበር። ከተማዋን በግር በባጃጅ እየዞርን ከተመለከትን በኋላ የውብቷን ምስጢር ለማወቅ ልባችን ተነሳሳ። ተነሳስተን ብቻ አልተውነውም ስለከተማዋም አጠቃላይ መረጃ የሚሰጠንን ሰው ለማናገር ወሰንን። በሃሳቡም ሁሉም ተስማምቶ የከንቲባው የቅርብ ሰው ቀጠሮ እንዲያሲዝልን ተነጋገርን። ተሳክቶልን ፈቃደኛ ሆኑ። በቀጠሯችን መሰረትም ከከንቲባው ቢሮ ከሥራ ባልደረቦቼ ጋር ተገኘን። የሃዋሳ ከንቲባ አቶ ዮናስ ዮሴፍ በፈገግታ ተቀበሉን። እኛም ለተደረገልን ትብብር አመስግነን ስለ ከተማዋ ያሉንን አጠቃላይ ጥያቄዎችን አቀረብን። እሳቸውም «መረጃ መስጠት አንዱ ሥራዬ ነው። እንኳን ወደ ከተማችን በደህና መጣችሁ» በማለት አቀባበል አደረጉልን። «ከፍት ፍቱ ፊቱ» የሚለው የአገሬ ሰው ወዶ አይደለም። ሁሉም ነገር የሚጀመረው ከፊቱ እንደሆነ ለማመላከት እንጂ። የከንቲባው አቀባበልና መረጃ ቶሎ ለመስጠት ያደረጉት ትብብር ምነው ሌሎቹስ ባለሥልጣኖችም እንደእርሳቸው ቢሆኑ ያስብላል።

የሃዋሳ ከተማ ከንቲባ አቶ ዮናስ ዮሴፍ ማብራሪያቸውን የጀመሩት የከተማዋ አመሰራረት ታሪክ በመግለፅ ነው።ከተማዋ የሃምሳ አራት ዓመት ጎልማሳ ነች። የተመሰረተችው በንጉሰ ነገሥቱ አፄ ኃይለሥላሴ ትዕዛዝ ነው። መሐንዲሶቹ ደግሞ የስዊድን ባለሙያዎች ናቸው።
ከተማዋ በአሁኑ ወቅት ከ350 ሺ በላይ ነዋሪዎች አሏት። በስምንት ክፍለ ከተማና በሠላሳ ሁለት ቀበሌዎች የተከፋፈለች ናት። የከተማዋ እድገት በጣም ፈጣን ነው። በተለይም ከደርግ ውድቀት በኋላ በፍጥንት ካደጉት የሀገራችን ከተሞች የመጀመሪያዎቹ ተርታ እንደምትመደብ ነው ከንቲባው ያብራሩት።
ከተማዋ የተመሰረተችው በፕላን ነው። ልማቷም ከምስረታው ጀምሮ እየተከናወነ ያለው በፕላኑ መሰረት ነው። አሁንም እየተከናወነ ያለው በእቅዱ መሰረት ነው። እግረኛና የመኪና መንገዶች፤ ቤቶችና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ዕቅዱን ተከትለው ስለሚሰሩ የከተማዋን ውበት ልዩ አድርጎታል። ሁሉም ዓይነት ልማቶቿ ከነዋሪዎቿ ጋር የተሰማማ በመሆኑ እድገቷን አፋጥኖላታል። የከተማዋን አረንጓዴ ልማት ዛፎችን በመትከልና በመንከባከብ፣ የመንገድ ዳርቻዎችን አረንጓዴ በማድረግ ከሌሎቹ የአገሪቱ ከተሞች ሃዋሳ የተሻለች ናት። ንጽህናዋም ቢሆን በአንጻራዊነት መልካም ነው። በመሆኑም ሌሎች የአገራችን ከተሞች እነኝህን መልካም ተሞክሮዎች ሊቀስሙ ይገባል ባይ ናቸው ከንቲባው።

ሌላው ከተማዋ የተሻለ እድገት ላይ እንደሆነች ማሳያ ነው የሚሉት ከንቲባው በከተማዋ የተገነቡ ዘመናዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ነው። እንደ ሆቴል፣ሪዞርትና ትላልቅ መሰረተ ልማቶች በግልና በመንግሥት እየተሠሩ ነው። ወደ ከተማዋ የሚገባው የኢንቨስትመንት ፍሰትም ቢሆን ከፍተኛ ነው። በአገር አቀፍ ደረጃ ለኢንዱስትሪ ዞን ከተመረጡ በጣት የሚቆጠሩ ከተሞች መካከል ሃዋሳ አንዷ ናት።በርካታ ኢንዱስትሪዎች ተገንብተው የተለያዩ ምርቶችን ለገበያ እያቀረቡ ነው። ወደፊትም ማምረት የሚጀምሩ በርካታ ኢንዱስትሪዎች እንዳሉ ከንቲባው ያመለክታል። የከተማ አስተዳደሩ የኢንዱስትሪ መንደር በመከለል ለአገር ውስጥና ለውጭ አገር ባለሀብቶች እየሰጠ ነው። ከተማዋ ከዚህ ጎን ለጎን ለአጎራባች ከተሞች የንግድ ማዕከል በመሆንም እያገለገለች ነው። ከተለያዩ የክልሉና የአጎራባች ክልሎች መገናኛ ስለሆነች ከፍተኛ ንግድ እየተካሄደባት እንደሆንም ይናገራሉ።
ከተማዋ የውጭና የአገር ውስጥ ቱሪስቶች መዳረሻም ናት። በዚህም ከፍተኛ ጥቅም እያገኘች ነው። የቱሪስት መዳረሻ እንድትሆን ያደረጋት የከተማዋ ስያሚ የሆነው የሃዋሳ ሐይቅ፣ ዘመናዊ እና የክልሉ ዋና ከተማ መሆኗ፣ ከአጎራባች ከተሞች ጋር በመንገድ መገናኘቷና ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቅት ላይ መገኘቷ ነው። ሐይቁ ከተማዋ ለኑሮ ምቹ እንድትሆን አድርጓታል።ለመዝናኛና ለቱሪስት መስህብም እየዋለ ነው። በሐይቁ ላይ ጎብኚዎች በጀልባ እንዲዝናኑ በማስቻል፤ አሣ አጥምዶ ለገበያ በማቅረብና እዚያው ተጠብሶ በማቅረብ ቱሪስቶች እንዲመገቡ በማድረግ ለከተማዋ ትልቅ አስተዋፅኦ እያደረገ ነው።
ከንቲባው ማብራራታቸውን ሲቀጥሉም ይህ የከተማዋ ሁሉ ነገር የሆነው ሐይቅ በጥንቃቄ ካልተያዘ ሊበከልና አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል ይላሉ። ከከተማውና ከፋብሪካዎች የሚወጣው ቆሻሻና ዝቃጭ ወደ ሐይቁ ከገባ በሐይቁ ህልውና ላይ ችግር ይጋረጣል። ይህ እንዳይሆን የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወነ እንደሆነ ይናገራሉ።
ክልሉም ሆነ የከተማ አስተዳደሩ ይህን ሁኔታ ተገንዝቦ የሐይቁን ህልውና ችግር ላይ እንዳይወድቅ የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ ነው እንደ ከንቲባው ገለፃ። ሐይቁ በደለል እንዳይሞላ በከተማዋ አካባቢና በተራሮች ላይ የአካባቢ ጥበቃ ስሥራ እየተሠራ ነው። በየዓመቱ እቅድ ተይዞ በርካታ ችግኞች ይተከላሉ። ከፋብሪካ የሚወጡ ዝቃጮችንና ቆሻሻውን እንዳይበክለው ለማድረግም የማስተማር፣ የቁጥጥርና የቅጣት ሥራዎች በአስተዳደሩ ይደረጋል። ሁሉም ፋብሪካዎች የራሳቸው ማጣሪያ እንዲኖራቸው እየተደረገ ነው። በአጠቃላይ ከተማዋ ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ለመጪው ትውልድ ተጠብቃ እንድትቆይ ለማድረግ እየተሠራ እንደሆነ ይናገራሉ ከንቲባው።
የከተማዋ የባህል፣ ቱሪዝምና የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ወይዘሮ ምህረት ገነኒ የሲዳማ ዞን በርካታ የመስህብ ቦታዎች እንዳሏት ይናገራሉ። ሃዋሳ ለእነዚህ የመስህብ ቦታዎች ማዕክል ናት። በተለይም የሃዋሳ ሐይቅ የከተማዋ ነዋሪዎች እስትንፋስ ነው። ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድሎችን ፈጥሯል፣ የምግብ ምንጭና የከተማዋ ውበት ነው። በዚህም የሃዋሳ ከተማ የቱሪስት መስህብ ለመሆን ችላለች ይላሉ።
ከዚህም በተጨማሪ በሌሎች መስህብም ሃዋሳ የታደለች እንደሆነች ኃላፊዋ ያመለክታሉ። ባህላዊና ትውፊታዊ ቅርሶች አሏት። ትክል ድንጋይ፣ ዋሻዎች፣ ጣሊያን ሲዋጋ ትቶት የሄደው መድፍ፣ ጥንታዊ ቤተ መንግሥቶች፣ ለኤኮቱሪዝም የሚውል የታቡር ተራራ፣ የቡርቂቱ ፍል ውሃ ለመታጠቢያና ለሚጠጣ፣ እና ሌሎችም የቱሪስትመስህብ ቦታዎች በከተማዪቱ ይገኛሉ።
ኃላፊዋ እነኝህ ሁሉ የመስህብ ቦታዎች ሙሉ በሙሉ እንዳልተጠቀሙባቸው ተናግረው የመስህብ ቦታዎችን በማልማትና በማስተዋወቅ ተጠቃሚ ለመሆን የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ይናገራሉ። በአሁኑ ወቅት የአገራችን ሕዝብ የመስህብ ቦታዎችን ለመጎብኘት ያለው ፍላጎት ጨምሯል። የሰውም አስተሳሰብ እየተቀየረ ነው። ከተማ ለመዝናናትና ለመጎብኘት በወር ከአስር ሺ እስከ አስራ አምስት ሺ የአገር ውስጥ ጎብኚዎች ወደ ከተማዋ እንደሚመጡ ይገልፃሉ። ከአምስት እስከ ሰባት ሺ የውጭ አገር ጎብኚዎች ይመጣሉ። አሁን ያለው መነቃቃት እንዲቀጥልም ያሉትን ሀብቶችን መንከባከብና ማስተዋወቅ ቁልፍ ጉዳይ ነው ይላሉ- ኃላፊዋ።
ከዚህም በተጨማሪ የከተማዋ የጸጥታ ሁኔታ ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን ወይዘሮ ምህረት ያመለክታሉ። ምክንያቱም ሲናገሩ ሰላም በሌለበት ቦታ የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ አገር ጎብኚዎች ወደ ከተማዋ አይመጡም። በመሆኑም የከተማዋን ጸጥታ ከባለፉት ዓመታት እያሻሻልን መጥተን በአሁኑ ወቅት ምንም ዓይንት ችግር ባይኖረም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ይላሉ። በአሁኑ ወቅት የወንጀል መፈጸም መጠን ወደ ዜሮ ለማድረስ እየሰሩ መሆኑንም ይገልፃሉ ። የኮሚኒቴ ፖሊስ ከህብረተሰቡ ጋር ተቀናጅቶ እየሠራ ነው።
ሌላው መሠራት አለበት የሚሉት የቱሪስት መስህብ ባለባቸው አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎች ከጎብኚዎች የሚገኘውን ጠቀሜታ በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል። ይህም ተደራጅተው የተለያዩ አገልግሎቶችን በማቅረብ ተጠቃሚ መሆን ቢጀምሩም ተጠናክሮ መሄድ አለበት ይላሉ።
በመጨረሻ ኃላፊዋ ያነሱት ጉዳይ ከቱሪዝም ኢንዱስትሪው የሚገኘው ጥቅም ቀጣይነት እንዲኖረው ለማድረግ ኢትዮጵያዊ ቱባ ባህላችንን መጠበቅ ያስፈልጋል። ይህም እንዲሆን በእያንዳንዱ ወረዳ እና የከተማ አስተዳደር ወጣቶች ቱባውን ባህል ጠብቀው እንዲሄዱ የተለያዩ ኪነጥበባዊ ዝግጅቶች ይደረጋሉ። ሥልጠናዎችም ይሰጣሉ። ኃላፊዋ እንደሚሉት ሃዋሳ ከሌሎች ከተሞች የምትማረው በርካታ ነገሮች ቢኖሩም እሷም ለሌሎች ከተሞች የምታካፍለው በርካታ መልካም ነገሮች እንዳሏት ኃላፊዋ ያምናሉ። በከተሞች መካከል ያለው ግንኙነት አሁን ካለው በበለጠ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።
http://www.ethpress.gov.et/addiszemen/

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር