የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ መልካም ተሞክሮዎችና ያልተሻገራቸው መሥመሮች

በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ በመማር ማስተማር፣ በምርምር ሥራዎች፣ በማሕበረሰብ አገልግሎትና የሰባ ሰላሳ ቅበላን ተግባራዊ ለማድረግ የመምህራንና ቤተ ሙከራ ቁሶችን ከማሟላት አንጻር ያጋጠሙ ችግሮች እንዲሁም በተወሰዱ መፍትሔዎችና በሌሎችም ጉዳዮች ከፕሬዚዳንቱ ዶክተር ዮሴፍ ማሞ ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ በክፍል አንድ ይዘን መቅረባችን ይታወሳል። በዛሬው እትማችን በዩኒቨርሲቲው ሌሎች እንቅስቃሴዎች ዙሪያ ያደረግነውን ቆይታ ይዘን ቀርበናል።
አዲስ ዘመን ፦ በዩኒቨርሲቲው ወጣቶችን በተለይም ሴቶችን ከትምህርታቸው የሚያሰናክሉ የተለያዩ ችግሮች እንደሚያጋጥሙ ይነገራል። ይህ ምን ያህል እውነት ነው? ምን የመፍትሔ እርምጃስ ተወሰደ?
ዶክተር ዮሴፍ፦ የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ በርካታ ተማሪዎችን ያቀፈ ነው። ከእነዚህ ተማሪዎች መካከል እጅግ በጣም ጥቂት በሚባሉ ተማሪዎች የተነሳ የአብዛኛው ስም መነሳት የለበትም። ተቋሙ እነዚህም ቢሆኑ ለተለያዩ ችግሮች መጋለጥ የለባቸውም የሚል አቋም ይዞ እየሰራ ነው። ያለው አመለካከት በጣም የተዛባ ነው። አብዛኛዎቹ ሴት ተማሪዎችም ቢሆኑ እኛ ለመማር ነው የመጣነው፤ አላማ አለን የሚሉ ናቸው። ከዚህ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ሴት ተማሪዎችን ሰብስበን ለማወያየት ስንፈልግ አይመጡም። ምክንያታቸው በተወሰኑ ተማሪዎች የተነሳ ሰብዕናችንን ትነካላችሁ የሚል ነው።
ሐዋሳ ትልቅ ከተማ በመሆኑ በወሲብ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሴቶች ሳይቀሩ ራሳቸውን ተማሪ በማስመሰል «ሹገር ዳዲ» የሚባሉትን ያጠምዳሉ። የተማሪ መታወቂያ ይዘውም ይገኛሉ። ይህን ችግር ለመፍታት ከከተማው ፖሊስ ጋር በመተባበር እየሰራን ነው። በመምህራን በኩልም ከውጤት ጋር በተያያዘ ከሴት ተማሪዎች ጋር አግባብ ያልሆነ ግንኙነት ለመፍጠር የሞከረ አንድ መምህር እንዲቀጣ አድርገናል። በዩኒቨርሲቲው ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሥርዓተ ጾታ ዳይሬክቶሬትና ክበባት የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያደረጉ ነው።
አዲስ ዘመን ፦ የዩኒቨርሲቲውን ቅጥረ ግቢ ለማስዋብ ከፍተኛ ገንዘብ ተመድቦ ሥራው በመከናወን ላይ ይገኛል። ይህን ለማድረግ ምን አነሳሳችሁ ውጤቱስ ምን ይመስላል?
ዶክተር ዮሴፍ፦ በእርግጥ እንደተባለው የዩኒቨርሲቲውን ቅጥረ ግቢ ለማስዋብ 52 ሚሊዮን ብር መድበን ሥራው እየተከናወነ ነው። ሥራውን የሚያከናውነው ድርጅት በዘርፉ ልምድ ያለው ነው። በጨረታ ተወዳድሮ የተረከበው ቢሆንም በዝቅተኛ ዋጋ ከስሮ ነው የሚሰራው። የእኛን ሥራ ካዩ በኋላ ግን ሌሎችም እየጠሩት ነው።
እኛ እዚህ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ከሁለት ሳምንት በላይ ተቸግረን ነበር። በግልም ይህን ያህል ከፍተኛ ብር ግቢውን ለማስዋብ ማውጣት የሚለው ሃሳብ እንቅልፍ ነስቶኝ ነበር። ይህ በእኛ ሀገር የተለመደ ባይሆንም በሌላው ዓለም የዩኒቨርሲቲዎችን ግቢ ለተማሪዎች የሚስብ ማድረጉ አዲስ አይደለም። ውሳኔውን አጽድቀን ወደ ሥራ ተገብቶ ለውጡ ከታየ በኋላ ግን ያገኘነው አዎንታዊ ምላሽ ከፍተኛ ነው። የዛሬ ዓመት የክልሉ ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ሽፈራው ሽጉጤ በተማሪዎች የምረቃ በዓል ላይ በተገኙበት ወቅት ሥራው በጣም ጥሩ መሆኑን መስክረው ነበር።
ግቢውን ማስዋቡ በመማር ማስተማሩ ሥራ ላይ አዎንታዊ ሚና አለው። ከዚህ ቀደም መምህራን በምሳ ሰዓት ግቢ ውስጥ ለመቆየት አይፈልጉም ነበር። አሁን ግን ዘመናዊ ላውንጅ፣ ምቹ አካባቢና ነፃ የዋይ ፋይ ኢንተርኔት አገልግሎት ስላለ በግቢው ውስጥ ይቆያሉ። ፋውንቴን፣ መብራቶች፣ የእግረኛ መንገዶችና ሌሎችም ግንባታዎች ሲጠናቀቁ የበለጠ ውበት ይኖረዋል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ለሕንፃ ግንባታዎችም ከፍተኛ ትኩረትና ጥንቃቄ እናደርጋለን። በሌሎች ተቋሞች እንደሚያጋጥመው የመጓተት ችግር አይታይም። ሕንፃዎቻችንም በተቀመጠላቸው ጊዜ ግንባታቸው እየተካሄደ ነው። ለአካል ጉዳተኞች ምቹ እንዲሆኑ ተደርገው የተሰሩ ሲሆን፤ እስከ ላይኛው ፎቅ ድረስ ያለችግር እንዲወጡ ተደርገው ነው የተገነቡት።
የሕንፃዎቹን ግንባታ የሚከታተል ቡድን አለ። እኔም በየጊዜው የደረሱበትን ደረጃ አያለሁ። ለሕንፃ ግንባታ ጨረታ ስናወጣ የኮንትራክተሮቹን የኋላ ታሪክ እንመረምራለን። ዝቅተኛ ገንዘብ የሚያቀርቡትን ብቻ አናይም። ግንባታ ጀምረው የሚያቋርጡ ከሆነ አንቀበላቸውም። በእዚህም አምና ለሥራ ማስኬጃ የተመደበልን በጀት ዘጠኝ መቶ ሚሊዮን ብር አካባቢ ቢሆንም ተጨማሪ በመጠየቅ 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን አካባቢ ነው የተጠቀምነው። በእዚህ ዓመትም 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ተመድቦልናል። የእኛ ዩኒቨርሲቲ በፋይናንስ አጠቃቀም የተሻለ አፈጻጸም ነው ያስመዘገበው።
አዲስ ዘመን ፦ ዩኒቨርሲቲው ከሌሎች አቻ የውጭ ተቋማት ጋር ያለው ትብብር ምን ይመስላል?
ዶክተር ዮሴፍ፦ የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ቀድሞ በግብርና ስለጀመረ ከተለያዩ የውጭ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በዘርፉ ግንኙነት ነበረው። ከዚህ በተጨማሪ በሌሎችም መስኮች ከተለያዩ የአውሮፓ፣ የአሜሪካና የአፍሪካ ተቋማት ጋር ብዙ ፕሮጀክቶች አሉት። ከአላባማ፣ ኮሎራዶ ኦስሎ፣ ካስኬድና ሌሎችም ተቋማት ጋር ባለን ግንኙነት የሁለተኛና የሦስተኛ ዲግሪ መምህራንን በማሰልጠንና በሌሎችም ዘርፎች ትብብር እናደርጋለን። በገንዘብ ደረጃም ቢሆን ከፍተኛ ድጋፍ እናገኛለን። ሙራድ ከሚባለው ተቋም ጋር ለሁለት ዓመት ባለን ስምምነት 220 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ይደረግልናል።
አንድ ዩኒቨርሲቲ ሊኖረው የሚገባው የመምህራን ስብጥር መካከል 75 በመቶ በሦስተኛ ዲግሪ ቀሪው 25 ከመቶ ደግሞ በሁለተኛ ዲግሪ የሰለጠኑ እንዲሆኑ ይጠበቃል። እኛ በሦስተኛ ዲግሪ የሰለጠኑ መምህሮቻችን ብዛት ከ10 በመቶ አልበለጠም። ትብብሮቹም ይህን በማሟላት ረገድ ትልቅ ፋይዳ አላቸው። ብዙ የምርምር ሥራዎችን ለመስራትም የገንዘብ እጥረት አለ። ከእነዚህ ተቋማት ጋር የምናደርገው ስምምነት ችግሩን አስወግዶ ምርምሮችን ለማካሄድ ከፍተኛ ፋይዳ አለው። በእዚህም ዩኒቨርሲቲውም ሆነ መንግሥት ይጠቀማሉ። አሁን ከውጭ ተቋማት ጋር የምናደርገው ትብብር እየበዛ ስለመጣ የፕሮጀክት ማስተባበሪያ ቢሮ ከፍተናል።
አዲስ ዘመን ፦ የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የራሱን ገቢ ለማሳደግ የሚያደርገው ጥረት ምን ይመስላል?
ዶክተር ዮሴፍ፦ ከሌሎች አገራት ከምናየው ተሞክሮ የከፍተኛ ትምህርት ብዙ ገንዘብ ተከፍሎበት የሚገኝ ነው። ዩኒቨርሲቲዎችም በራሳቸው ገቢ ነው የሚተዳደሩት። እኛም ሀገር የመንግሥት ሚና እየቀነሰ የሚሄድበት ወቅት ይመጣል። ከዚህ አንጻር የውስጥ ገቢን ለማሳደግ ብዙ ሥራ እየሰራን ነው። ሰፊ የሆነ ዘመናዊ የዶሮ እርባታ አለ። በቀን 5 ሺ እንቁላል ይመረታል። የከብት እርባታና የወተት ላም ጀምረናል። ወደፊት ፓስቸራይዝድ የሆነ ወተት የማምረት እቅድ አለን። በወርክሾፓችን ወንበር፣ ጠረጴዛና አልጋ እናመርታለን። ለተቋሞቻችን እኛ ነን የምናቀርበው። የአሳማም ርቢ ጀምረናል። ይህን የጀመርነው ከተማሪዎች የሚተርፈው ምግብ ከሚባክን በማለት ነው። ከተማሪዎች የሚተርፈው ምግብ በብዙ ዩኒቨርሲቲዎች ከፍተኛ ችግር የሚፈጥር ነገር ነው። ለሌላ አላማ ሲሸጥ ለሰዎች የሚያውሉት አሉ። ከተከማቸበት ቦታ ገብተው ለመስረቅም የሚሞክሩ አሉ። በእኛ ዩኒቨርሲቲ ከበርካታ ተማሪዎች በቀን ሦስት ጊዜ የሚወጣ ተረፈ ምግብ አለ። ይህን ለአሳማዎች ቀለብ አድርገነዋል። በአጠቃላይ ባለፈው ዓመት ከተለያዩ የውስጥ ገቢዎች 70 ሚሊዮን ብር አስገብተናል። ይህንን እያሰፋን ስንሄድ ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ከምናቀርበው አገልግሎት ባሻገር ለዩኒቨርሲቲያችንም የገቢ ምንጭ ይሆናል።
አዲስ ዘመን ፦ ከዩኒቨርሲቲው የሚወጡ ተመራቂዎች ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ የሚደረጉ ጥረቶች አሉ ?
ዶክተር ዮሴፍ፦ ተመራቂዎች ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ የሚደረገው ጥረት ብዙዎቻችን ያልተሻገርነው መስመር ይመስለኛል። እኛም ጋር ይታያል። ይሁን እንጂ በአንድ ወቅት «ኢንኩቤሽን ሴንተር» አቋቁመን ተመራቂዎች ከዩኒቨርሲቲው ከመውጣታቸው በፊት የሥራ ፈጠራን ተግባራዊ የሚያደርጉበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ሞክረን ነበር። ለምሳሌ የኮምፒዩተር ተመራቂዎች በመጨረሻው ሦስተኛና አራተኛ ዓመት የትምህርት ጊዜያቸው ቦታ ተዘጋጅቶላቸው የተለያዩ ሶፍትዌሮችን እንዲፈጥሩ ይደረጋል። ከኢንዱስትሪ ጋር ትስስር እንዲፈጥሩ በማድረግም ገቢ የሚያገኙበትና የሥራ ፈጠራ ባህልን የሚያዳብሩበት እድል ይፈጥር ነበር። ሲመረቁም በእዚሁ ሥራ ይቀጥላሉ። አሁንም ይህ እንቅስቃሴ ቢቀጥልም የተፈለገውን ያህል ግን እየተሰራበት አይደለም።
ጥሩ ፈጠራ የሚመነጨው ከዩኒቨርሲቲዎች ነው። እዚህ የፈጠራ ቀን ብለን በምናከብርበት ወቅት ብዙ አዳዲስና የሚያስገርሙ ፈጠራዎችን ተማሪዎች ይዘው ይቀርባሉ። ይሁን እንጂ በአመለካከት ደረጃ ችግሮች አሉ። በዩኒቨርሲቲው የሥራ ፈጠራ ኮርስ ቢሰጥም በቂ አይደለም። ከመምህራንም ብዙ ይጠበቃል። ይህን ችግር የግድ መሻገር አለብን።
አሁን እንደ አጭር ጊዜ እቅድ ይዘን እየተገበርን ያለነው የተለያዩ ማሽኖችን አስመስሎ በመስራት በተለይ የአርሶ አደሩን ችግር የሚያቃልሉ ተግባራትን ማከናወንና የቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ ነው። በእዚህ በኩል በምክትል ፕሬዚዳንት የሚመራ ክፍል አቋቁመን እየተንቀሳቀስን ነው።
አዲስ ዘመን፦ ሞጁላራይዜሽን የትምህርት አሰጣጥን ተግባራዊ በማድረግ የተሻለ ጥራት ለማምጣት የምታደርጉት ጥረት ምን ደረጃ ላይ ይገኛል ?
ዶክተር ዮሴፍ፦ ሞጁላራይዜሽን የትምህርት አሰጣጥን ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ነው የተጀመረው። አሁን አራተኛ ዓመት ላይ ደርሰናል። በእዚህ የትምህርት አሰጣጥ የሰለጠኑ ተማሪዎች አምና ተመርቀዋል። በእዚህ የትምህርት አሰጣጥ ሥርዓት በተከታታይ ምዘና እስከ ስድስት የሚደርሱ የተለያዩ ሙከራዎች ይሰጣሉ። በፊት በተለያየ ሴሚስተር የሚሰጡ ተመሳሳይ ትምህርቶች አንድ አካባቢ ይደረጋሉ። ለምሳሌ ኮምፒዩተር ጥገና የተመለከቱ ትምህርቶች በተለያየ ወቅት ይሰጡ ከነበረ አንድ ላይ ይሆናሉ። ይህ ተማሪው በተለያየ ምክንያት ትምህርት ቢያቋርጥ ቢያንስ ስለ ኮምፒዩተር ጥገና አውቆ እንዲወጣና እንዲሰራ ያስችለዋል። ብክነንትንም ያስቀራል ከሚል የታቀደ ነው። ባለፉት ሦስት ዓመታት የነበረውን አፈጻጸምና ያመጣውን ለውጥ አስመልክቶ ጥናት አድርገናል። በእዚህም መጠነ ማቋረጥ መቀነሱን አረጋግጠናል። ስለዚህ በትክክል ከተተገበረ ለውጥ ያመጣል።
በእርግጥ የተማሪ መብዛት ተግባራዊ ለማድረግ ችግር ሊሆን ይችላል። ትምህርቶቹንም አንድ ላይ በማድረግ በሞጁል መልክ ማዘጋጀት ይቀረናል። በሞጁላር አሰራር ተማሪው አንድ ዓይነት ይዘት ያላቸው ትምህርቶችን ሲጨርስ እውቅና ማግኘት (ሰርቲፋይድ መሆን) አለበት። እያንዳንዱ ሞጁል እውቅና ይሰጠዋል። ይህ ብክነትን ለማስቀረት ይረዳል። ይህን ማድረግ አልጀመርንም።
አዲስ ዘመን፦ የትምህርት ሠራዊት በማደራጀት በኩል ምን ተግባራት ተከናውነዋል? ያጋጠሙ ችግሮችስ አሉ ?
ዶክተር ዮሴፍ፦ የአንድ ለአምስት የትምህርት ሠራዊትን በተመለከተ በተማሪ ሳይሆን በመምህሩ በኩል ቶሎ ያለመቀበል ችግር ነበር። ይህን ቀድሞም በቡድን የሚሰሩ ሥራዎች ስለነበሩ አዲስ አይደለም ይሉ ነበር። ከሌላ ነገር ጋር የሚያይዙም ነበሩ። አንዳንድ ተማሪዎችም ሌላውን ለመደገፍ ጊዜ የለንም በማለት ይሸሹት ነበር። ፎረሞች አካሂደን ጠቀሜታውን ለተማሪውም ለመምህሩም አሰልጥነናል። አሁን ለውጥ አለ። ሌሎች ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞችንም ወደእዚህ አደረጃጀት ለማስገባት እየሰራን ነው።
የትምህርት ሠራዊቱ ለተማሪውም ሆነ ለመምህሩ ጠቀሜታው የጎላ ነው። የአቻ ለአቻ ትምህርት እንደሚጠቅም ሳይንሱ ያመለክታል። አንዱ ሲያስረዳ በዚያው ለራሱም ያጠናል። አንድ ሰው ለብቻው ሲያጠና ለመገንዘብ ጊዜ ይፈጃል። ሲያስረዳ ግን ጊዜ ይቆጥባል። በቡድን ሥራ አነስተኛ አቅም ያለውም አንድ ነገር ያጋራል። በአቻ ለአቻ የመማማር ሂደት ጊዜ አይባክንም። በአጭር ጊዜ የመቀበልን ነገር ያዳብራል።
አዲስ ዘመን ፦ ወደ ፊት ለዩኒቨርሲቲው ያለዎት ራዕይ ምንድንነው ?
ዶክተር ዮሴፍ፦ ዩኒቨርሲቲያችን እየተለወጠ ነው። ወደ ፊት በአፍሪካ ተወዳዳሪ በዓለም ደግሞ ታዋቂ ዩኒቨርሲቲ ሆኖ የማየት ራዕይ አለኝ ።
http://www.ethpress.gov.et/addiszemen/index.php/addiszemen/society/7208-2014-01-03-08-07-15

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር