በሃዋሳ ከተማ ኣስተዳደር ስር የተጠቃለሉት የገጠር ቀበሌያት የልማት ያለህ እያሉ ነው፤ በቀበሌያቱ ውስጥ በባለሃብቶች የሚካሄደው የመሬት ወረራ ኣሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል

የሃዋሳ ዙሪያ የገጠር ቀበሌዎች ለከተማይቱ ቅርብ ከመሆናቸው ኣንጻር በልማት በኩል ሊያገኙ የሚገባቸውን ያህል ትኩረት ኣላገኙም።

በሃዋሳ ከተማ ኣስተዳደር በቱላ ክፍለ ከተማ ስር የተጠቃለሉት የሃዋሳ ዙሪያ የገጠር ቀበሌያት ቁጥር 14 ነው። በጊዜው የደኢህዴን ካድሬዎች ቀበሌያቱ ከሃዋሳ ከተማ ኣስተዳደር ሰር ከተጠቃለሉ ብዙ ጥቅሞች እንዳሉት በመስበክ የየቀበሌያቱን ነዋሪዎች መቆሚያ እና መቀመጫ በማሳጣት ነበር እንዲጠቃለሉ የተደረጉት። በርግጥ በርካታ ሰዎች በጉዳዩ ላይ ደሰተኛ ባይሆኑም ለልማት እና ለለውጥ ጉጉ ስለነበሩ ደጋፋቸውን ከመስጠት ኣልተቆጠቡም። እንዳውም የቀበሌያቱን ከሃዋሳ ከተማ ኣስተዳደር ስር መሆንን ኣስመልክተው ከብት ኣርደው ደግሰዋል።

የሆነ ሆኖ ሰሞኑን ሪፖርተራችን ጥቻ ወራና የቀበሌያቱን ነዋሪዎች በማነጋገር ያሰባሰበው መረጃ እንደምያመለክተው፤ በወቅቱ የቀበሌያቱን በሃዋሳ ከተማ ኣስተዳደር መጠቃለልን የደገፉትን ጨምሮ በርካታ ሰዎች በካድሬዎቹ የተገባላቸው የልማት ስራ ኣለመሰራቱን ኣመልክተዋል። በርግጥ ኣንዳንድ የልማት ስራዎች እየተሰሩ ያሉ ብሆኑም እየተሰሩ ያሉት የልማት ስራዎች በየትኛዎቹን መሰል የገጠር ቀበሌዎች እየተሰሩ ያሉ መሆናቸው ኣስራርተዋል። ኣያይዘውም የዛሬ 20 ኣመት ከዳቶኦዳሄ ( ከሃዋሳ ከተማ መግቢያ ላይ ከጥቁር ውሃ ቀጥሎ ካለው ቀበሌ ማለት ነው) ተነስታ የውሃ ጀርካኗን ተሸክማ ከ 5 እስከ 7 ኪሎ ሜትር ርቀት ተጉዛ ከሃዋሳ ከተማ ቀበሌያት ውሃ ቀድታ ለምትመለሰዋ የዳቶኦዳሄ እማወራ ኣሁንም የተለወጠ ነገር የለም ብለዋል።


እንደነዋሪዎቹ ገለጻ ከሆነ፤ የቀበሌዎቹ ከከተማ ኣስተዳደር ስር መሆናቸውን ተከትሎ በተለይ ከመሬት ይዞታ ጋር በተያያዘ በርካታ ችግሮች ኣጋጥሞቸዋል። በየቀበሌያቱ ያለው መሬት ተጠንቶ ፕላን እስኪሰራ ድረስ ቤት መገንባት በመከልከሉ የየቀበሌያቱ ነዋሪዎች በወግ ባህላቸው መሰረት የመሬት ይዞታቸውን ለልጆቻቸው ኣውርሰው ቤት መገንባት ኣልቻሉም። ከዚህም ባሻገር የከተማው ኣስተዳደር የመሬት ይዞታችንን ሸንሽኖ ለሌላ ይሰጥብና፤ መሬታችንን በመንግስት እንቀማለን በምል ስጋት ሳይቀድሜን እንቅዴም ኣይነት ኣስተሳሰብ በርካታዎቹ የየቀበሌያቹ ነዋሪዎች የመሬት ይዞታቸውን በህገወጥ መንገድ ለጸጉረ ልውጦች በመሸጥ ላይ ናቸው። ለኣብነትም ያህል የዳቶኦዳሄ ቀበሌ ከጥቁር ውሃ ኣንስቶ እስከሃዋሳ ሴራሚክ ፋብሪካ ጀርባ ወደ ውስጥ በርካታ ኪሎ ሜትሮች በህገ ወጥ ፕላን በሌላቸው ቤቶች ተሞልተዋል። ኣከባቢው በሃዋሳ ከተማ ማስተር ፕላን ውስጥ ያልተካተተ ከመሆኑ በላይ ለኑሮ ኣስፈላጊ የሆኑ ውሃ እና መብራትን የመሳሰሉ መሰረተ ልማት ያልተሟላበት ነው። የቤቶቹ ግንባታ የኣካባቢውን ብሎም የከተማዋን ገጽታ ከማበላሸ ኣልፎ ሃብታም የሃዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ከድሃው የሲዳማ ተወላጆች መሬት በቀላል ዋጋ በመግዛት የመሬት ወረራ ያካሄዱበት ነው።መንግስት መሬትን መሸጥ እና መለወጥ ከልክሎ እያለ የድሃ ሲዳማ ኣርሶ ኣደሮች የመሬት ይዞታ በሃብታሞች ስወረር የከተማው ኣስተዳደር ጆሮ ዳባ ልበስ ብሏል።

የከተማው ኣስተዳደር በመሬት ወረራው ላይ ዝምታ ከመምረጡም በላይ ኣንዳንድ የኣስተዳደሩ ኣመራር ኣባላት የድሃ ኣርሶ ኣደሩን መሬት በልማት ስም በማጠር ለግል ጥቅም ማዋላቸው ታውቋል። ለኣብነትም ከሃዋሳ ቃንጫ ፋብሪካ ጀርባ ያለው መሬት ባለቤቶች ማንነትን ማጣራት በቂ ይሆናል።

እነዚህ በቱላ ክፍለ ከተማ ስር የተካተቱት 14 ቀበሌያት በኢኮኖሚ በኩል ለከተማው ኣስተዳደር ዋነኛ የገቢ ምንጭ ሆነዋል። የሲዳማ ዞን ለምን የቀበሌያቱን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ከግምት ውስጥ እንዳላስገባ ግልጽ ባይሆንም፤ ለምሳሌ ያህል ከቱላ የጫት ቀረጥ የምሰበሰበው በሚሊዮኖች የምቆጠር ብር ገቢ ለከተማው ኣስተዳደር ዋነኛ የገቢ ምንጭ ነው። የከተማው ኣስተዳደር በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገቢ ከነዚሁ ቀበሌያች እየሰበሰበ ለቀበሌያቱ መልሶ በተለያዩ የልማት ስራዎች ካላፈሰሰ የቀበሌያቱ ከከተማው ኣስተዳደር ስር መሆን ጥቅሙ ምኑ ላይ ነው?

ሪፖርተራችን ጥቻ ወራና ቱላ ኣከባቢ ያሰባሰበው መረጃ እንደሚያሳየው፤የቱላ እና የኣከባቢው ቀበሌ ነዋሪዎች በከተማው ኣስተዳደር ደስተኞች ባለመሆናቸው የሸበዲኖ ወረዳ ኣካል የሆነውን ኣቤላ ሊዳን ጨምረው በኣንድ ወረዳ ስር ለመደራጀት ውስጥ ለውስጥ እንቅስቃሴ ጀምረዋል። የከተማው ኣስተዳደ የየቀበሌያቱን ነዋሪዎች የልማት እና የመልካምኣስተዳደር ጥማት ማርካት ካልቻለ ኣሁን ውስጥለውስጥ እየተቀጣጠለ ያለው ህዝባዊ ጥያቄ ገሃድ በውጣቱ ኣይቀርም። ስለዚህ የሃዋሳ ከተማ ኣስተዳደር የእነዚህን የቀድሞ የገጠር ቀበሌዎችን መልሶ በማልማት፤ የመልካምኣስተዳደር ችግሮችን በመቅረፍ እንድሁም የመሬት ወረራውን የማቆም ስራ መስራት ይጠበቅበታል።

ወራንቻ ኢንፎርሜሽን ኔትዎርክ



Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር