የሰብዓዊ መብት አፈጻጸምን የሚከልሰው ዕቅድ

ዕውቁ ኖርዌያዊው ተመራማሪ ሼትል ትሮንቮል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) በኢትዮጵያ ላይ ያወጣውን ሪፖርት ተመርኩዞ፣ ‹‹Human Rights Violations in Federal Ethiopia: When Ethnic Identity is a Political Stigma››
በሚል ርዕስ በ2000 ዓ.ም. አንድ የምርምር ጽሑፍ አሳትመው ነበር፡፡ ተመድ በ1999 ዓ.ም. ያወጣው ሪፖርት በኢትዮጵያ ብሔርን መሠረት ያደረገ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደሚፈጸም ይከሳል፡፡ ፕሮፌሰር ትሮንቮል በጥናታቸው የተመድ ሪፖርት ድምዳሜ ትክክል እንደሆነ ይከራከራሉ፡፡ 
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት መምህር የሆኑት አቶ ጌታቸው አሰፋ ለትሮንቮል በጻፉት የታተመ ምላሻቸው በኢትዮጵያ መንግሥት የሰብዓዊ መብት ጥበቃ እንደሚደረግና የመብት ጥሰቱ ክስ ስህተት እንደሆነ፣ ጥሰት አለ ከተባለም ብሔርን መሠረት ያደረገ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደማይፈጸም ተከራክረዋል፡፡ በ2001 ዓ.ም. ለንባብ በበቃው ምላሻቸው አቶ ጌታቸው እንደ ሼትል ትሮንቮል ያሉ የውጭ አገር ተመራማሪዎች ስለ ኢትዮጵያ ማኅበራዊ፣ ሕጋዊና ፖለቲካዊ ውስብስብ ጉዳዮች በድፍረት ለማሳተም ለራሳቸው ነፃነት የሚሰጡት፡ በአገሪቱ ጥቂት ቀናትን በዛ ካለም ወራትን ካሳለፉ በኋላ መሆኑን ተችተው ነበር፡፡ እነዚህ ተመራማሪዎች በውጭ ጸሐፍት የተጻፉ የምርምር ሥራዎችን ብቻ በማጣቀስ ከባድ ድምዳሜ ላይ እንደሚደርሱም አመልክተዋል፡፡ 
ፕሮፌሰር ትሮንቮል ለአቶ ጌታቸው ምላሽ በሰጡት ሌላ ምላሽ ስለኢትዮጵያ ከአቶ ጌታቸው የተሻለ ግንዛቤ እንዳላቸው ገልጸው ነበር፡፡ የመመረቂያ ጽሑፋቸው በኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት ላይ እንደነበር ያሰታወሱት ትሮንቮል፣ ከ1980ዎቹ መጀመሪያ ጀምረው በኢትዮጵያ ስላለው የፖለቲካና የሰብዓዊ መብት ሁኔታ መረጃ እንደሰበሰቡና ይህም በጻፏቸውና አርትኦት በሠሩባቸው ሰባት መጻሕፍት በኢትዮጵያ ስላለው የዲሞክራሲ ሒደት፣ ስለ ግጭት፣ ስለ ሰብዓዊ መብትና የፖለቲካ ዕድገት ጉዳይ በጻፏቸው በርካታ የምርምር ሥራዎች፣ ሪፖርቶችና የፖሊሲ ሰነዶች እንደሚገለጽ ጠቁመዋል፡፡ ትሮንቮል ከሁለት አሥርት ዓመታት በላይ ስለኢትዮጵያ በቅርበት ቢያጠኑም አቶ ጌታቸው እንደ ጀማሪ ተመራማሪ መውሰዳቸው የእርሳቸውን የመረጃ እጥረት ስለሚጠቁም፣ ከስድስት ኪሎ ካምፓስ ወጣ ብለው በምልከታና በተግባራዊ ልምድ ላይ የተመረኮዘ ግንዛቤ እንዲያዳብሩም መክረዋቸው ነበር፡፡
በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብትን አስመልክቶ እንኳን የውጭ አገር ዜጋ የአገሪቱ ዜጎችም ተመሳሳይ አቋም የላቸውም፡፡ ከላይ በክርክሩ (ዘለፋ ማለትም ይቻላል) የተሳተፉት ሁለት ታዋቂ ምሁራን በጉዳዩ ላይ ተመራማሪዎች ጭምር የማይስማሙበት መሆኑን ማሳያ ነው፡፡ 
እንደ ሂዩማን ራይትስ ዎች፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ ክራይሲስ ግሩፕና ፍሪደም ሃውስ የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ሁልጊዜም የኢትዮጵያን መንግሥት በከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚከሱ ሪፖርቶቻቸው ሲያጠናቅሩ ሳይንሳዊ የምርምር አካሄዶችን እንደማይከተሉ መንግሥት ይተቻል፡፡ በተጨማሪም የውጭ ተማራማሪዎች ከተጣመመው መነሻ ሐሳባቸውም በላይ የአገሪቱን አግባብነት ያለው አውድ እንደማይረዱ ይገልጻል፡፡ ተቋማቱ በምላሻቸው እንደ ፕሮፌሰር ትሮንቮል ስለአገሪቱ በሚገባ የሚረዱና የሚያውቁ ተመራማሪዎችን እንደሚያሳትፉ ያስረዳሉ፡፡ 
ስለኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ይዞታ የሚደረገው ክርክር ሕገ መንግሥቱ ለሰብዓዊ መብት ዕውቅና ስለመስጠቱና ስለመንፈጉ አይደለም፡፡ ይልቁንም የክርክሩ ዋነኛ ጭብጥ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት የተካተቱት የሰው ልጅ የሚያውቃቸው መሠረታዊ የሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች አፈጻጸም ጉዳይ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያ መንግሥት ዕውቅና ያገኘው በሰብዓዊ መብት ጥሰት እንጂ ሰብዓዊ መብት እንዲከበር፣ እንዲጠበቅና እንዲተገበር በሚያደርገው ጥረት አይደለም፡፡ ለዚህ ጮክ ብለው ተቃውሞአቸውን የሚያሰሙ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድኖች ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡
ነገር ግን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኢትዮጵያ መንግሥት በጉዳዩ ላይ ያለውን አቀራረብ እየቀየረ ይመስላል፡፡ በዚህ አካሄድ መንግሥት ከዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት አካላት ጋር ተቀራርቦ መሥራት የመረጠ መስሏል፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት የኢትዮጵያ መንግሥት በአገሪቱ ያለውን የሰብዓዊ መብት ይዞታ ለማሻሻል ያለውን ቁርጠኝነት ለመላው ዓለም ለማሳየት ከፍተኛ ጥረት ማድረጉን ይገልጻል፡፡ ለሰብዓዊ መብት አካላት ወቅታዊ የአፈጻጸም ሪፖርት ማቅረቡ፣ በአፍሪካ የአቻ ለአቻ መገማገሚያ መድረክና በሁሉን አቀፍ ወቅታዊ ግምገማ መሳተፉ ለዚህ ማሳያ መሆኑንም እንዲሁ፡፡ የእነዚህ ጥረቶቹ ዋነኛ እንቅስቃሴው ግን የብሔራዊ የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሐ ግብር ዝግጅቱ ነው፡፡
የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሐ ግብር የማዘጋጀቱ ጉዳይ እኤአ በ1993 ዓ.ም. በተካሄደው በሁለተኛው የቪየና የዓለም የሰብዓዊ መብት ኮንፈረንስ ላይ ትኩረት ተሰጥቶት በአገሮች መካከል መግባባት የተደረሰበት አጀንዳ ነው፡፡ የዚሁ ኮንፈረንስ ውጤት በሆነው በቪየና ዴክላሬሽንና የትግበራ ፕሮግራም ክፍል ሁለት አንቀጽ 71 አገሮች የሰብዓዊ መብቶችን በማስፋፋት፣ በማስጠበቅና በማረጋገጥ ረገድ ያላቸውን አፈጻጸም ወደተሻለ ደረጃ ከፍ ለማድረግ ሊወስዱት የሚገባውን ዕርምጃ በግልጽ የሚያመላክት አገር አቀፍ የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሐ ግብር የማዘጋጀት አስፈላጊነትን በአፅንኦት እንዲቃኙት አሳስቧል፡፡ 
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ካውንስል አገሮች ሰብዓዊ መብትን በማረጋገጥ በኩል ያላቸውን አፈጻጸም የሚገመግሙበት በየአራት ዓመቱ የሚካሄድ ሁሉን አቀፍ የግምገማ መድረክ አመቻችቷል፡፡ ኢትዮጵያ ‹‹ዩኒቨርሳል ፔርየዲክ ሪቪው›› ተብሎ በሚጠራው በዚህ የግምገማ መድረክ ባቀረበችው ሪፖርት ላይ በመመሥረት ከተሰጡትና ከተቀበለቻቸው አስተያየቶች አንዱ የድርጊት መርሐ ግብር ማዘጋጀት ነበር፡፡ 
ከሁለት ሳምንታት በፊት መንግሥት ለሁለት ዓመታት ያዘጋጀው የድርጊት መርሐ ግብር ወደ ትግበራ ማምራቱን ለሁለት ቀናት ባዘጋጀው ብሔራዊ ኮንፈረንስና የውይይት መድረክ ጠቁሟል፡፡ መንግሥት የድርጊት መርሐ ግብሩ ዝግጅትና ትግበራ ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና ያገኙትን መብቶች በተለያዩ የመንግሥት አካላት በተናጠል ይፈጸሙ የነበረበትን ሁኔታ በተዋሀደና በተቀናጀ አኳኋን የሚካሄዱበትን ሁኔታ በግልጽ ለማመላከትና ተቋማቱ የሚመሩበትን መስመር ለመትለም የሚያገለግል ወሳኝ ሰነድ እንደሚሆን አመልክቷል፡፡
በተጨማሪም ይህ የድርጊት መርሐ ግብር የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት ከሚመለከታቸው የልማት አጋሮች፣ ከሲቪል ማኅበራትና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የሚፈጽሙት ከአምስት ዓመቱ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ተግባራዊነት አካል የሆነና ከዚሁ ዕቅድ ጋር በመተሳሰርና በመቀናጀት የሚተገበር ሰነድ መሆኑንም መንግሥት ያስገነዝባል፡፡ መርሐ ግብሩ መብቶቹ በተቀናጀ ሁኔታ እንዲተገበሩ ለማድረግ፣ የመልካም አስተዳደርና የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሒደቱን ለማፋጠንና የኢኮኖሚ ልማትን ለማስቀጠል ወሳኝ ሚና እንደሚኖረውም ያመላክታል፡፡
ዝርዝር አቀራረብ
የድርጊት መርሐ ግብሩ ዋነኛ መለያ ባህሪ ነገሮችን በዝርዝር ማቅረቡ ነው፡፡ መርሐ ግብሩ በዋነኛነት የእያንዳንዱን መብት ወቅታዊ ሁኔታ በመከለስ፣ የተስተዋሉ ችግሮችን በመለየትና የመፍትሔ አቅጣጫዎችን በመጠቆም የተሰናዳ ነው፡፡ 
በመጀመሪያ ረድፍ የተቀመጡት መብቶች የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ናቸው፡፡ እነዚህን በሕይወት የመኖር መብት፣ የአካል ደኅንነት መብትና የኢ-ሰብዓዊ አያያዝ ክልከላ፣ የተያዙ በጥበቃ ሥር ያሉና በፍርድ የታሰሩ ሰዎች መብት፣ የተከሰሱ ሰዎች መብት፣ ፍትሕ የማግኘት መብት፣ የአመለካከትና ሀሳብን በነፃ የመያዝና የመግለጽ መብት፣ የመደራጀት መብት፣ የሃይማኖትና የእምነት ነፃነት ናቸው፡፡
የድርጊት መርሐ ግብሩ በሁለተኛው ረድፍ መብቶች የኢኮኖሚያዊ፣ የማኅበራዊና ባህላዊ መብቶችን ይጠቅሳል፡፡ ይህም በቂ ምግብ የማግኘት መብት፣ የጤና መብት፣ የትምህርት መብት፣ የሥራ መብት፣ በቂ የመኖሪያ ቤት የማግኘት መብት፣ ንፁህ ውኃ የማግኘት መብት፣ የማኅበራዊ ዋስትና መብትና የባህል መብት ያካትታል፡፡ 
በሌላ በኩል የድርጊት መርሐ ግብሩ በሦስተኛው ረድፍ መብቶች ላይ ለመብት ጥሰት ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች መብቶችን ትኩረት ሰጥቷል፡፡ እነዚህም የሴቶች መብት፣ የሕፃናት መብት፣ የአካልና የአዕምሮ ጉዳተኞች መብት፣ ኤችአይቪ/ኤድስ ቫይረስ በደማቸው  ውስጥ የሚገኝ ሰዎች መብትና የአረጋውያን መብትን ያጠቃልላል፡፡ የመጨረሻው ረድፍ መብቶች ደግሞ የአካባቢ ደኅንነትና የልማት መብትን ያቅፋል፡፡ 
በአራቱም ረድፍ ለተጠቀሱት መብቶች ሁሉ የድርጊት መርሐ ግብሩ የመብቶቹን ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ፣ ዓለም አቀፋዊ የሕግ ማዕቀፍ፣ የተከናወኑ ተግባራት (የፖሊሲ ዕርምጃዎች፣ ብሔራዊ ሕጎች፣ ተቋማዊና አስተዳደራዊ ዕርምጃዎች)፣ ችግሮችና ተግዳሮቶች፣ የሚከናወኑ ተግባራትና ፈጻሚ አካላት እንዲሁም የክትትልና የግምገማ ሥርዓትን በዝርዝር ለይቶ አስቀምጧል፡፡ 
መርሐ ግብሩን መፈጸም ከአቅም በላይ ነውን?
የድርጊት መርሐ ግብሩ በውስጡ የያዛቸው መብቶችና የአፈጻጸም ዝርዝር መመርያዎቹ ያላቸውን ጠቀሜታ በደስታ የተቀበሉ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሰብዓዊ መብት ኤክስፐርቶች የመንግሥት ተነሳሽነት የሚደነቅ ቢሆንም፣ ዕቅዱን ሙሉ በሙሉ ለመተግበር የአቅምና የባህል ችግር እንዳለ ግን ያመለክታሉ፡፡ አገሪቱ በወረቀት ላይ የሚያምሩ ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎችና ዕቅዶች የማውጣት ችግር እንደሌለባት አስታውሰው፣ በአፈጻጸም ረገድ ያለው ተግባራዊ ተሞክሮ የወረቀቶቹን ያህል የሚያምር እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡ 
ከእነዚህም አንዱ በአንድ ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ውስጥ የሚሠሩ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የሰብዓዊ መብት ኤክስፐርት የድርጊት መርሐ ግብሩ በተቀናጀ ሁኔታ ሰብዓዊ መብትን ለመፈጸም ያለመ ቢሆንም፣ ዕቅዱ ከአገሪቱ አቅም ጋር የተመጣጠነ ነው ብለው እንደማያምኑ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ኤክስፐርቱ በድርጊት መርሐ ግብሩ ሦስት መሠረታዊ ችግሮች እንደሚስተዋሉ ጠቁመዋል፡፡ በኢትዮጵያ በጠቅላላ ሕዝቡ ለሰብዓዊ መብቶች ያለው አረዳድና ግንዛቤ በጣም ዝቅተኛ መሆኑን ያስገነዘቡት ኤክስፐርቱ፣ ሁሉም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤትና የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በዓመታዊ ዕቅዳቸው ውስጥ የሰብዓዊ መብት አፈጻጸምን እንዲያካትቱ መደረጉ እንደየግንዛቤ ልዩነታቸው እንዲሠሩ ስለሚያስገድድ፣ መርሐ ግብሩ በወጥነት የመተርጎም ችግር ይገጥመዋል፡፡ በሌላ በኩል ለሰብዓዊ መብት አፈጻጸም ወሳኝ የሆኑ ባለድርሻ አካላት ሳይቀር የሰብዓዊ መብት ደጋፊዎች ባልሆኑበት የኢትዮጵያ ከባቢ ሁኔታ ይህን የመሰለ ትልቅ ዕቅድ በሁለት ዓመት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ለመፈጸም አዳጋች መሆኑ እንደ ሁለተኛ ተግዳሮት በኤክስፐርቱ ተወስዷል፡፡ ሦስተኛው ችግር ከዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር በትብብር ከመሥራት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበራት ሕግ እነዚህ ተቋማት በአገሪቱ የሰብዓዊ መብት ላይ እንዳይሠሩ መከልከላቸውን ያስታወሱት ኤክስፐርቱ፣ የድርጊት መርሐ ግብሩ ሙሉ በሙሉ ለመተግበር የመንግሥትን የፖሊሲ አቅም እንደሚፈተን ገምተዋል፡፡ 
በጅማ ዩኒቨርሲቲ የሰብዓዊ መብት ኤክስፐርት የሆኑት አቶ አይተነው ደበበ ተቃራኒ አቋም አላቸው፡፡ ለአቶ አይተነው መርሐ ግብሩ የመንግሥትን ግልጽ አሠራርና ተጠያቂነት ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና ይጫወታል፡፡ በመርሐ ግብሩ አማካይነት ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶችንና ሕገ መንግሥታዊ ዕውቅና የተሰጣቸውን መብቶች፣ መንግሥት መቼና እንዴት ሊፈጽማቸው እንዳሰበ ለዜጎቹና ለዓለም አቀፍ ባለድርሻ አካላት እንደሚገልጽም አቶ አይተነው ያስገነዝባሉ፡፡ ነገር ግን መርሐ ግብሩን ለመፈጸም የሰው ኃይልና የሎጅስቲክስ እጥረት ሊኖር እንደሚችል ይቀበላሉ፡፡ ‹‹መልካም አጋጣሚ ሆኖ ሁሉም መብቶች የሰው ኃይልና ሎጂስቲክስ አይጠይቁም፡፡ በአብዛኛው የኢትዮጵያ መንግሥት ራሱ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይፈጽማል ተብሎ ይከሰሳል፡፡ የመብት ጥሰት እንዳይፈጸም ለማድረግ ብዙ ሀብት አይጠይቅም፡፡ ሌሎች መብቶች ደግሞ ከአቅም ጋር ቀስ በቀስ የሚፈጸሙ ናቸው፤›› በማለትም አቶ አይተነው አብራርተዋል፡፡ 
አቶ አይተነው የሁለት ዓመት የጊዜ ገደቡ በአዎንታዊ ጎኑ መታየት እንዳለበትም ተከራክረዋል፡፡ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ መንግሥት ሰብዓዊ መብትንና ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብን የማክበር ባህል በመገንባት መሠረት ካስያዘ ስለሰብዓዊ መብት የሚደረገው የሐሳብ ልውውጥ ቀጣይ ሒደት በመሆኑ የጊዜ ገደቡ ጉዳይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደማይኖረው አብራርተዋል፡፡ ነገር ግን የድርጊት መርሐ ግብሩን በሚገባ ለመፈጸም በሚደረገው ጥረት እንደ ሲቪል ማኅበራት ያሉ መንግሥታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ አካላት ሰፊ ሚና ሊኖራቸው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሥልጠና በመስጠትና የሰብዓዊ መብት ትምህርት በማስፋፋት ከሚጫወተው ሚና ባሻገር፣ ተከታታይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሪፖርቶችን በማዘጋጀት የመንግሥትን ተጠያቂነት ሊያጠናክር እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡ 
አቶ ይበቃል ግዛው በፍትሕ ሚኒስቴር ሥር የቴክኒክ ጉዳዮችን ለማስተባበር የተቋቋመው የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሐ ግብር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ናቸው፡፡ አቶ ይበቃል ስለ ድርጊት መርሐ ግብሩ ሲነሳ የሰብዓዊ መብት አፈጻጸምን ለመጀመር በማሰብ ሳይሆን የወጣው ይበልጥ አፈጻጸሙን ለማጠናከር በመሆኑ፣ በቅድሚያ ከዚህ በፊት በአፈጻጸም ረገድ ለተመዘገቡ ስኬቶች ዕውቅና መስጠት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡ አቶ ይበቃል መርሐ ግብሩ መንግሥት፣ ዜጎች፣ ዓለም አቀፍና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ሲቪል ማኅበራትና የሙያ ማኅበራትን በዋነኛነት አቀናጅቶ የሰብዓዊ መብት አፈጻጸምን ይበልጥ ስኬታማ ለማድረግ እንደወጣ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ 
የሰብዓዊ መብት አፈጻጸም ጉዳይ መቼም ቢሆን የሚጠናቀቅ ሒደት እንዳልሆነ ያመለከቱት አቶ ይበቃል፣ በመጪዎቹ ሁለት ዓመታት ሕግ በማውጣት፣ ሥርዓት በመገንባትና በከፍተኛ ደረጃ በሚታየው የፖለቲካ ቁርጠኝነት የሚጣለው መሠረት ከዚያ በኋላ ላሉ ዓመታት ወሳኝ እንደሚሆን አገንዝበዋል፡፡ ዕቅዱን ያወጣው መንግሥት ትልልቅ ዕቅዶችን በተሳካ ሁኔታ የመፈጸም ልምድ ያለው በመሆኑ የድርጊት መርሐ ግብሩ በስኬት ይፈጸማል ብለው እንዲያምኑ እንዳደረጋቸው አቶ ይበቃል ገልጸዋል፡፡
የድርጊት መርሐ ግብሩን ለመፈጸም መንግሥት ዓለም አቀፍ ትብብር ለማግኘት የሚያደርገው ጥረት ከሲቪል ማኅበራት ሕግ ጋር የሚያጋጨው ነገር እንደሌለም አቶ ይበቃል አስረድተዋል፡፡ ‹‹በመርህ ደረጃ መንግሥት መርሐ ግብሩን የሚፈጽመው በራሱ በጀት ነው፡፡ አስፈላጊ ከሆነ ተጨማሪ በጀት ይለቀቃል፡፡ ሆኖም ዓለም አቀፍ ትብብር መጠየቅ አስፈላጊ ከሆነ እሱ የሚፈጸመው የሲቪል ማኅበራትን ሕግ በማክበር ብቻ ነው፤›› በማለትም መንግሥት በሕጉ ላይ እንደማይደራደር አቶ ይበቃል ያስረዳሉ፡፡ 
የፖለቲካ ቁርጠኝነት
መንግሥት መርሐ ግብሩን ለማስፈጸም በፈጻሚ አካላት ዝርዝር የማስፈጸሚያ ዕቅድ ውስጥ ማካተት፣ ስለ መርሐ ግብሩ ግንዛቤ መፍጠር፣ ሕዝባዊ ተሳትፎና ከመንግሥት የልማት አጋሮችና ከበጎ አድራጎት ድርጅቶች ጋር መተባበር፣ ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት ተቋማትን መጠቀምና የሰብዓዊ መብት ትምህርት መስጠት ዋነኛ የማስፈጸሚያ ስልቶች መሆናቸውን መንግሥት ያመለክታል፡፡ 
መንግሥት የፖለቲካ ቁርጠኝነቱን በስልቶቹ ላይ ለማሳየት ከወዲሁ እንቅስቃሴዎች በማድረግ ላይ ሲሆን፣ በተለይ የዲሞክራሲ ተቋማት ከሚባሉት ተቋማት መካከል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወቱ ይጠበቃል፡፡
በተለይ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በአገሪቱ የሰብዓዊ መብት አያያዝ እንዲጠበቅ፣ እንዲከበርና እንዲሻሻል እንዲሁም መብቶች ተጥሰው ሲገኙ የእርምት ዕርምጃ እንዲወሰድ ለማድረግ በሚሠራቸው ሥራዎች ላይ፣ የመንግሥት ትብብር መጠን እውነተኛ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ስለመኖር አለመኖሩ አመላካች ይሆናል፡፡
የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር አምባሳደር ጥሩነህ ዜና ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኮሚሽኑ በመጪዎቹ ዓመታት እጅግ ተጠናክሮ በመንግሥት ላይ ቁጥጥር ያደርጋል፡፡ በተለይ ከሰብዓዊ መብት ትምህርትና ሥልጠና በተጨማሪ የተለያዩ ምርምሮችን በማሳተምና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሪፖርቶችን በማዘጋጀት ቁጥጥሩን ይበልጥ እንደሚያጠብቅ አምባሳደር ጥሩነህ አስረድተዋል፡፡ በተለያዩ አወዛጋቢ ሕጎች ላይ የሚሠሯቸው ምርምሮች ሕጎቹ ከሰብዓዊ መብት ስምምነቶች ጋር የተጣጣሙ መሆን አለመሆናቸውን የሚወስኑ ስለመሆናቸውም አመልክተዋል፡፡ መርሐ ግብሩ ኮሚሽኑ ሕግ ይወጣባቸዋል ተብለው በተለዩ ጉዳዮች ረቂቅ ሕግ በሚዘጋጅበት ወቅት ረቂቆቹን በመመልከት ከሕገ መንግሥቱና ከሌሎች የሰብዓዊ መብቶች ሕጎችና ሰነዶች ጋር የተጣጣሙ እንዲሆኑ የምክር አገልግሎት የመስጠት ኃላፊነት ሰጥቶታል፡፡
በመርሐ ግብሩ ውስጥ የተገለጹትን የክትትልና የግምገማ ተግባራት በበላይነት የሚመራ ‹‹የክትትልና ግምገማ›› ክፍል በፍትሕ ሚኒስቴር ውስጥ እንደሚያደራጅ ያስታወቀው መንግሥት፣ በክልልና በከተማ መስተዳድሮች ተመሳሳይ ክፍሎች በፍትሕ ቢሮዎች ሥር እንደሚደራጁም ጠቁሟል፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ ይህን የድርጊት መርሐ ግብር የሚመራ ‹‹ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሐ ግብር ጉዳይ አስተባባሪ ኮሚቴ›› በፍትሕ ሚኒስቴር ሰብሳቢነት እንደተቋቋመም መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ኮሚቴው ከፍትሕ ሚኒስቴር በተጨማሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር፣ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር፣ የሴቶች የሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርና የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤትን በአባልነት ያዘለ ነው፡፡ 
አቶ ይበቃል መርሐ ግብሩ ከፍተኛ የፖለቲካ ቁርጠኝነት የተስተዋለበት በመሆኑ በፌዴራልና በክልል ደረጃ አፈጻጸሙ ቀላል እንደሚሆን አመልክተዋል፡፡ ነገር ግን አቶ አይተው ከፖለቲካ ቁርጠኝነቱ በተጨማሪ ተገቢ ቁጥጥርና ክትትል በመንግሥት አካላት መካከል ካልተደረገ፣ የድርጊት መርሐ ግብሩን ሙሉ በሙሉ ለመተግበር በጣም አስቸጋሪ እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡ 
http://www.ethiopianreporter.com/index.php/politics/itemlist/user/46-%E1%88%B0%E1%88%88%E1%88%9E%E1%8A%95%E1%8C%8E%E1%88%B9

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር