ጥቂት ስለ ሲዳማ ቡና እግር ኳስ ክለብ


ሲዳማ ቡና 

ሙሉ ስም ፡ ሲዳማ ቡና ስፖርት ክለብ 
ምስረታ ፡ 1999
ስታዲየም ፡  ይርጋለም ስታዲየም ሀዋሳ ስታዲየም
የክለቡ የወቅቱ አሰልጣኝ ፡ ታረቀኝ አሰፋ  ዳኜ

ክለቡ ያገኛቸው ክብሮች ፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሊግ ሻምፒዮን 2001
ሲዳማ ቡና በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ፕርሚየር ሊግ እየተሳተፈ ያለ ክለብ ነው፡፡ ክለቡ ከተመሰረተ ጥቂት አመታት ብቻ ቢቆጠሩም በብሔራዊ ሊግ ሻምፒዮን ሆኗል፡፡ በፕሚየርሊጉም ጥሩ ተፎካካሪ እየሆነ ይገኛል፡፡

ምስረታ 

ሲዳማ ቡና ስፖርት ክለብ የተመሰረተው በ 1999 ዓ/ም ነበር በደቡብ ክልል ክለቦች ሻምፒዮና ላይ ሲዳማ ዞንን በመወከል ሥስት ክለቦች ይሳተፋሉ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ዳራ ከነማ ነበር፡፡ ዳራ በውድድሩ ለፍፃሜ በመድረስ ውጤታማ ይሆናል፡፡ ይህም ክልሉን በመወከል ሀዋሳ ላይ ወደተካሄደው የኢትዮጵያ የክልል ክለቦች ሻምፒዮና ከተሳተፉ አራት ቡድኖች አንዱ ለመሆን አበቃው፡፡ በዚህ ውድድር ቀዳሚዎቹን አራት ደረጃዎች የሚይዙ ቡድኖች ወደ ብሔራዊ ሊግ ሲያልፉ ዳራም ሦስተኛ ደረጃን አግኝቶ ስለነበር ብሔራዊ ሊጉን ተቀላቀለ፡፡ እናም ዳራ ከተማን ብቻ ይወክል የነበረው ክለብ መላውን የሲዳማ ዞንን እንዲወከል በማሰብ ሲዳማ የሚለውን ስያሜ አገኘ፡፡

ሲዳማ ቡና በብሔራዊ ሊግ
ሲዳማ ቡና ሁለት አመት በብሔራዊ ሊግ አሳልፏል፡፡ በመጀመሪያው አመት ቆይታው በ 2000 አራተኛ ደረጃን ይዞ ነው ያጠናቀቀው፡፡ በሁለተኛው አመት 2001 ውድድሩ በሁለት ምድብ ተከፍሎ ሲካሔድ በምድብ ሁለት የነበረው ሲዳማ በመጨረሻው ጨዋታ ከአየር ሀይል ጋር ያለ ግብ በመለያየት ከምድቡ ከሜታ አቦ ቢራ ቀጥሎ ሁለተኛ ደረጃን አግኝቷል፡፡ በዚህ ጨዋታ ቢሸነፍ ኖሮ ይህን ደረጃ አያገኝም፡፡ በቀጣይ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ለማለፍ ከየምድባቸው የመጀመሪያዎቹን ሁለት ደረጃዎች የያዙ አራት ቡድኖች  መካከል የአንድ ዙር ውድድር ተደረገ፡፡ ሻሸመኔ ከነማ፤ ደደቢትንና ሜታአቦ ቢራን በማሸነፍ ዘጠኝ ነጥብ የሰበሰበው ሲዳማ ቡና የብሔራዊ ሊግ ሻምፒዮን በመሆን ዓመቱን አጠናቀቀ፡፡ አጥቂውን ሰዳት የሱፍንና አሰልጣኙን ታረቀኝ አሰፋን በኮከብነት አስመርጧል፡፡

ሲዳማ ቡና በፕሪሚየር ሊግ
ሲዳማ ቡና ለመጀመሪያ ጊዜ በተሳተፈበት የ 2002 ፕሪሚየር ሊግ እንደመጀመሪያው ጥሩ ሊባል የሚችል ውጤት አስመዝግቧል፡፡ ከሻምፒዮኑ ቅ/ጊዮርጊስ ጋር በመጀመሪያው ጨዋታ አዲስ አበባ ላይ አቻ መለያየቱ መከላከያን በይርጋለም ላይ 4 ለ 2 ማሸነፍ ከጠንካራ ክለቦች ጋር ያሳየውን ፉክክር ያመለክታል፡፡

የሲዳማ ቡና መሰረት
ሲዳማ ቡና ከሌሎች ክለቦች በተለየ ሁኔታ የፋይናንስ ምንጪን የዞኑን ህዝብ በማድረግ ይታወቃል፡፡ በአለም እውቅና በተሰጠው ቡና ስም የተሰየመው ይኸው ክለብ በዞኑ ህብረተሰብ ከፍተኛ የፋይናንስ ድጋፍ ይደረግለታል፡፡ ክለቡን በበላይነት የሚመራው የሲዳማ ዞን  ስፖርት ምክር ቤት ሲሆን  ክለቡ ሙሉ በሙሉ የሚንቀሳቀሰው ከሕብረተሰቡ በሚሰበሰብ ገንዘብ ነው፡፡ ከአርሶ አደሩ ጀምሮ ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል አመታዊ መዋጮ ያደርጋል፡፡ በየአመቱ በሚካሔድ የገቢ ማሰባሰቢያም ውጤታማ ሆኗል፡፡ በ 2001 የብሔራዊ ሊግ ዋንጫ ማንሳቱን ተከትሎ ባደረገው የገቢ ማሰባሰቢያ ከ 8 ሚሊዮን ብር በላይ ማሰባሰቡ ለዚህ ማሳያ ይሆናል፡፡ እናም ሲዳማ ቡና በዚህ ረገድ ያለው ልምድ ለሌሎች ክለቦችም በአርአያነቱ የሚጠቀስ ነው፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር