ኢኮኖሚውና ቢዝነሱ ‹‹ግሉኮስ›› ያስፈልገዋል

ኢኮኖሚያችንና የቢዝነስ እንቅስቃሴያችን እየፈዘዘ ነው፡፡ ቀዝቀዝ ብሏል፡፡ አተነፋፈሱ ጥሩ አይመስልም፡፡የገንዘብ እንቅስቃሴ እንደነበረው አይደለም፡፡ ክፍያዎች እየዘገዩ ናቸው፡፡
በባንኮችና በደንበኞች መካከል ጠንካራ ግንኙነት የለም፡፡ ባንኮቹ በተለይም የግል ባንኮች እየተዳከሙ ናቸው፡፡ በዚህ ምክንያት የገንዘብ እንቅስቃሴ ሙትት እያለ ነው፡፡ በውጭ ምንዛሪ ችግርና እጥረት ምክንያት በጣም የሚያስፈልጉ ዕቃዎች እንደተለመደው ከውጭ እየገቡ አይደለም፡፡ በጥቂቱ የመጡ ካሉም ዋጋቸው የማይቻል እየሆነ ነው፡፡ 
መንግሥት ራሱ የሚያስፈልገውን ፋይናንስ በሚፈልገው መጠንና ፍጥነት እያገኘ አይደለም፡፡ በፕሮጀክቶች ሒደትና አተገባበር የሚፈለገውን ያህል ዕድገት እያረጋገጠ አይደለም፡፡ ይህ ማለት ዕድገት ቆመ አይደለም፡፡ ዕድገት አሁንም አለ፡፡ በተፈለገው ጊዜ ሊዳሰስና ሊጨበጥ የሚፈለገው የገንዘብ መጠን ግን በእጁ እየገባ አይደለም፡፡ 
የውጭ ኢንቨስተሮች አስፈላጊውን ፈጣን መስተንግዶና አስተዳደር እያገኘን አይደለም እያሉ እያማረሩ ነው፡፡ የጀመርነው ኢንቨስትመንት ተቋረጠ፣ አሸንፋችኋል ከተባልን በኋላ እንደገና ጨረታ ይወጣል ተባልን፣ አቁሙ ተብለናል፣ መልስ የሚሰጠን አጣን እያሉ እያማረሩ ናቸው፡፡
ገንዘብ መደበቅና ማሸሽ እየተለመደ ነው የሚል አጀንዳ ወደ መድረክ እየመጣ ነው፡፡ ባንክ ከማስቀመጥ ይልቅ በእጅ መያዝ እየተመረጠ ነው፡፡ አገር ውስጥ ከማስቀመጥ ይልቅ ውጭ መላክ ተመራጭ ሆኗል እየተባለ ነው፡፡
አገር ውስጥ ባለው የውጭ ምንዛሪ ክምችት ላይ ተጨማሪ ጉልበት ሊፈጥር የሚገባው የውጭ ምንዛሪ ግኝትም ውጭ እንዲቀር እየተደረገ ነው፡፡ የገባ ካለም በጥቁር ገበያ እንደገና እንዲወጣ እየተደረገ በመሆኑ አገሪቱ ተጠቃሚ መሆን አልቻለችም፡፡ 
እኔ ንፁህና ሕግ አክባሪ ነኝ ብሎ ከመተማመን ይልቅ ‹‹በሙስና ተጠርጥረው ታሰሩ››  የሚል ዜና በሰማ ቁጥር እየተደናገጠ ሥራ የሚያቆምና የሚደናበር ነጋዴም አለ፡፡ ግማሹ በራሱ ስለማይተማመን ሌላው ደግሞ ‹‹ዝሆኖች እንዲታሰሩ ተወሰነ›› የሚል ዜና ሰምታ፣ ‹‹ዝሆን አለመሆኔን እስኪያጣሩ ድረስ ቢያስሩኝስ?›› ብላ እንደሰጋችው ‹‹ጥንቸል›› የሚሆን አለ፡፡ ይኼ ሁሉ ተደማምሮ አነሰም በዛም የቢዝነስ መቀዝቀዝ እያስከተለ ነው፡፡
በዓለም ደረጃ ያለው የኢኮኖሚ ቀውስ አሁንም ባለመፈታቱ በአገራችን ላይም የተወሰነ መቀዛቀዝን አስከትሏል፡፡ ከኢኮኖሚው ቀውስ በተጨማሪ ዓለም ወደ ፖለቲካዊ ቀውስም እየገባ ነው፡፡ ይህም የራሱ ጫና አለው፡፡
በአጠቃላይ ሲታይ ይበልጥ እየተነቃቃና እየተጠናከረ እንዲሄድ የምንፈልገው ኢኮኖሚያችንና ቢዝነሳችን ፈዘዝና ቀዝቀዝ እያለ ነው፡፡ ግሉኮስ ያስፈልገዋል፡፡ 
መንግሥት ለዚህ ችግር ልዩ ትኩረት ይስጥ እንላለን፡፡ በውስጡም ግልጽ ውይይት ያድርግ፡፡ የውጭ ኢንቨስትመንት በተፈለገው ፍጥነት፣ በሚፈለገው ሕግ አክባሪነትና በሚፈለገው ከሙስና የፀዳ መስተንግዶ እያደረግኩለት ነው ወይ? በማለት መንግሥት ራሱን ይገምግም፡፡ ‹‹አበረታች›› የሚባለውን ቃል ይተውና ደካማና ጠንካራ ጎኑን ይፈትሽ፡፡
በግል ባንኮች ያለውን ችግርም መንግሥት ይመርምር፡፡ ሊያስረዳ የሚችለውን ያስረዳ፡፡፡ ሊያበረታታ የሚችለውን ያበረታታ፡፡ ሊቀይር የሚችለውን ፖሊሲና አሠራር ይቀይር፡፡ ያስተካክል፡፡ 
መንግሥትን በፀረ ሙስና ትግልህ ጠንክር ተጠናከር እንለዋለን እንጂ ተደራደር አንለውም፡፡ አሁንም ፀረ ሙስና ትግሉ ተጠናክሮ ይቀጥል እንላለን፡፡ 
ፀረ ሙስና ትግሉ በአንድ በኩል እየተጠናከረ በሌላ በኩል ደግሞ ሀቀኛውንና ታታሪውን የግል ባለሀብት መንግሥት ሊመክር፣ ሊያበረታታና ሊያጠናክር ይገባዋል፡፡ ከማያስፈልግ አሉባልታ፣ ፍርኃትና ጥርጣሬ በመላቀቅ ተጠናክሮ እንዲወጣና የድርሻውን እንዲጫወት መገፋፋት አለበት፡፡
መልካም አስተዳደርን እውን የማድረግ የቤት ሥራ አሁንም በመንግሥት ጠረጴዛ ላይ ተቀምጧል፡፡ ቢዝነስን እያዳከመው ያለው አንዱና ዓቢይ ችግር የመልካም አስተዳደር ዕጦት ነው፡፡ 
አቤት የሚባልበት እየጠፋ ነው፡፡ የውሳኔ ሰጪ ያለህ ቢባል መልስ አይገኝም፡፡ ፋይሎች የሚያያቸውና የሚያነባቸው አጥተዋል፡፡ ችግሩ እየቀጠለ በመሆኑ መንግሥት ቆራጥና ደፋር ዕርምጃ መውሰድ አለበት፡፡ ከውጭ መግባት ያለበት የውጭ ምንዛሪ እዚያው እንዳይቀር ወይም በጓዳ መጥቶ በጓዳ እንዳይወጣ ፖሊሲውንና አሠራሩን ይፈትሽ፡፡ 
በርካታ ዕርምጃዎች ሊወሰዱ ይገባል፡፡ መንግሥት ከባለሙያዎችና ከባለጉዳዮች ጋር እየተመካከረ በአስቸኳይ መፍትሔ ለማፈላለግ መታገል አለበት፡፡ እየደከመ ያለው ድባብ አስቸኳይ እገዛ ካልተደረገለት ወደ መቆም ሊያመራ ይችላል፡፡ ዘላቂ መፍትሔ እያሰቡ የኢኮኖሚው ሕይወት እንዳይጠፋ ‹‹ግሉኮስ›› እየሰጡ መራመድ ያስፈልጋል፡፡
http://www.ethiopianreporter.com/index.php/editorial/item/3153-%E1%8A%A2%E1%8A%AE%E1%8A%96%E1%88%9A%E1%8B%8D%E1%8A%93-%E1%89%A2%E1%8B%9D%E1%8A%90%E1%88%B1-%E2%80%B9%E2%80%B9%E1%8C%8D%E1%88%89%E1%8A%AE%E1%88%B5%E2%80%BA%E2%80%BA-%E1%8B%AB%E1%88%B5%E1%8D%88%E1%88%8D%E1%8C%88%E1%8B%8B%E1%88%8D

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር