የሀዋሳ ሀይቅን ከብክለት ለመከላከል የሚያስችል ፕሮጀክት እየተካሄደ ነው

አዋሳ ነሐሴ 3/2005 የሀዋሳን ሀይቅ ከብክለት ለመከላከል በ13 ሚሊዮን ብር ወጪ የሚካሄደው የቆሻሻ ጎርፍ ማጣሪያ ፕሮጀክት ከግማሽ በላይ መከናወኑን የከተማው ማዘጋጃ ቤት አስታወቀ፡፡ በማዘጋጃ ቤቱ የመሰረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ መብራቴ መለሰ ከትናንት በስቲያ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት ከከተማው የተለያየ አቅጣጫ ወደ ሀይቁ የሚፈሰው ቆሻሻ ጎርፍ በጥናት ተለይቶ ሀይቁን ከብከለት ለመታደግ የሚያስችል ፕሮጀክት ተዘጋጅቶ በ2005 አጋማሽ ላይ ወደ ተግባር ተገብቷል፡፡ በጥናቱ መሰረት ከፍተኛ የቆሻሻ ጎርፍ ወደ ሀይቁ የሚገባባቸው በሀዋሳ ዩኒቨርሰቲ ሪፈራል ሆስፒታል፣ አሞራ ገደል፣ ጨምበላላና ጥምቀተ ባህር አካባቢዎች በኩል መሆኑን ተረጋግጧል ብለዋል፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች የሚፈሰው ቆሻሻ ጎርፍ አጣርቶ ንጹህ ውሃን ብቻ ወደ ሀይቁ የሚለቅ ፕሮጀክት ማዘጋጃ ቤቱ ማመቻቸቱን ገልፀዋል፡፡ ለኘሮጀክቱ ማከናወኛ 13 ሚሊዮን ብር ተመድቦ ወደ ስራ የተገባው ሲሆን የዚሁ ኘሮጀክት ግንባታ እስካሁን ከአጠቃላይ ስራው ከ58 በመቶ በላይ መከናወኑን አስረድተዋል፡፡ ስራውም በአራት የተከፈለ ሲሆን የመጀመሪያው ወደ ሃይቁ የሚመጣውን ጎርፍ የሚቀበልና የጉርጓድ ገንዳዎች ሲኖሩት ቀጥሎ ማንኛውንም ባዕድ ነገር ለይቶ እያጣራ ንጹህ ውሃን ብቻ የሚለቅና ፍሰቱን የሚቆጣጠር በመጨረሻም የሚጣራው ቆሻሻ እዚያው ማስቀረት የሚችሉ የተለያዩ የዛፍ ችግኞች በየአካባቢዎቹ የመትከልና የማልማት ስራ መሆኑን አስተባባሪው ተናግረዋል፡፡ ይህም ከከተማ ነዋሪና ከትላላቅ ተቋማት የሚወጣው ባዕድ ነገርና ኬሚካል ወደ ሀይቁ እንዳይገባ በማድረግ ከብክለት ለመከላከልና ደህንነቱን በዘላቂነት ለመጠበቅ የሚያስችል ፕሮጀክት ነው፡፡ የፕሮጀክቱ ስራም በመጪው አመት ጥቅምት ወር ድረስ ለማጠናቀቅ በመፋጠን ላይ እንደሚገኝና ስራውም በግል ተቋራጭ የሚካሄድ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ የከተማው ስያሜና ውበት የሆነው የሀዋሳ ሀይቅ ከፍተኛ ጥልቀቱ 22 ሜትርና ስፋቱም 62 ካሬ ኪሎ ሜትር ይደርሳል፡፡ በውስጡና በዙሪያው የተለያዩ የአሳ ዝርያዎችና ብርቅዬ አእዋፍ የሚገኙበት፣ በመዝናኛነቱም ብዙዎች የሚያዘወትሩትና ለበርካታ ሰዎችም የስራ እድል በመፍጠር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው የተፈጥሮ ሀብት መሆኑን ከከተማው አስተዳደር የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡
http://www.ena.gov.et/Story.aspx?ID=10678&K=1

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር