ከኃላፊነት የተነሱ የቤቶች ኤጀንሲ ባለሥልጣናት ያወጧቸው መመርያዎች ታገዱ

ከመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ በተነሱት ከፍተኛ አመራሮች የሥልጣን ዘመን የወጡ መመርያዎችና የመሠረታዊ የሥራ ሒደት ለውጥ ትግበራዎች እንዲታገዱ ትዕዛዝ  ተሰጠ፡፡
የወጡት መመርያዎችና የመሠረታዊ የሥራ ሒደት ለውጥ ጥናቶችን ተግባራዊ ለማድረግ የተሠሩ ሥራዎች በሙሉ እንዲታገዱ ትዕዛዝ የሰጠው የከተማ ልማት፣ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ነው፡፡ ሚኒስቴሩ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት መመርያዎቹ የወጡበት መንገድና የመሠረታዊ የሥራ ለውጡ ተጠንቶ እንዲቀርብለት ጨምሮ አዟል፡፡
ምንጮች እንደገለጹት፣ ኤጀንሲው መመርያ በማውጣት በኩል ያለው ሥልጣን ጥያቄ ውስጥ ገብቷል፡፡ የመሠረታዊ የሥራ ሒደት ለውጥ (ቢፒአር) ጥናት የተገበረው ሚኒስቴሩን ሳያማክርና ሚኒስቴሩ ሳያፀድቀው ነው ተብሏል፡፡ 
በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ፊርማ ከሥልጣናቸው የተነሱት የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ ሥራ አስኪያጅ አቶ ተፈሪ ፍቅሬ፣ ምክትል ሥራ አስኪያጆች አቶ ኃይሉ ሐደሬና አቶ ገብሩ ባይልብኝ፣ እንዲሁም የቤቶች አስተዳደር የሥራ ሒደት ባለቤት የነበሩትና ተቀይረው ወደ ጥቃቅንና አነስተኛ ኤጀንሲ የተዛወሩት አቶ ኪዳኔ ሥዩም ናቸው፡፡ 
በእነዚህ ከፍተኛ አመራሮች የሥልጣን ዘመን ከወጡት መመርያዎች ውስጥ እጅግ አነጋጋሪ ሆኖ የቆየውና እስካሁን ትኩሳቱ ያልበረደው የአከራይ ተከራይ፣ የቤቶች አሰጣጥ፣ የጥገናና ፈቃድ አሰጣጥ መመርያዎች ይጠቀሳሉ፡፡
በተለይ የአከራይ ተከራይ መመርያ ወጥቶ ተግባራዊ በሆነበት ወቅት በተለያዩ የከተማዋ ክፍሎች ቀውሶች መፈጠራቸው አይዘነጋም፡፡ ይህ መመርያ የወጣበት ምክንያት በወቅቱ እንደተገለጸው፣ ከኤጀንሲው ቤቶች የተከራዩ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት ሸንሽነው ለሌሎች ነጋዴዎች አከራይተዋል፡፡ ይህ አሠራር የኤጀንሲውን ሕግጋት ይፃረራል በሚል ነው፡፡ በወቅቱ በተወሰደው መጠነ ሰፊ ዕርምጃ በርካታ ቅሬታዎችና አለመግባባቶች ተፈጥረው እንደነበር አይዘነጋም፡፡
በወቅቱ የተወሰደውን ዕርምጃ በመቃወም በርካታ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት ይመለከታቸዋል ላሏቸው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ቅሬታ ሲያሰሙ ቆይተዋል፡፡ የጉዳዩ አካሄድ ፈሩን የሳተ መሆኑን ዘግይቶ የተረዳው የከተማ ልማት፣ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ይህ መመርያ እንዲታገድና የአቤቱታ አቅራቢዎች ጉዳይ ተመርምሮ ማስተካከያ እንዲደረግ አዟል፡፡
በዚህ መሠረት የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ ተጠባባቂ ሥራ አስኪያጅ ሆነው የተሾሙት አቶ ኃይለ ማርያም ዓለምሰገድ፣ በማዕከል ደረጃና በቅርንጫፎች እስከ ነሐሴ 15 ቀን 2005 ዓ.ም ድረስ የአቤቱታ አቅራቢዎች ጉዳይ እንዲጣራ ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡ በመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ ብልሹ አሠራር ሰፍኗል በሚል የበጀት ዓመቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ጠንከር ያለ ግምገማ ሲካሄድ ቆይቷል፡፡ በግምገማው ወቅት የኤጀንሲው ኃላፊዎች የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ለሠራተኞቻቸው እንዲሰጥ የሚፈቀደውን መኖርያ ቤት በተከራዩ ግለሰቦች ስም ማዞር፣ የአከራይ ተከራይ መመርያን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የግል ጥቅም ማሳደድ፣ በአገልግሎት አሰጣጥ፣ በመልካም አስተዳደር ችግሮችና ተቋሙን ተናብቦና ተባብሮ በመሥራት በኩል ችግር ተፈጥሯል የሚል ነው፡፡
የኤጀንሲው ከፍተኛ አመራሮች በእነዚህ ጉዳዮች ቢገመገሙም በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጻፈው ደብዳቤ  ግን አመራሮቹ በሥራ ላይ በነበሩበት ጊዜ ምሥጋና አቅርቦ ከማሰናበት በስተቀር ያለው ነገር እንደሌለ ምንጮች ተናግረዋል፡፡
ከእነዚሁ ጉዳዮች ጋር ባልተለየ መንገድ በመሠረታዊ የሥራ ሒደት ለውጥ ትግበራ ከፍተኛ ችግር ተፈጥሯል ተብሏል፡፡ በጊዜያዊና በቋሚ የሥራ መደቦች ሠራተኞች በሚመደቡበት ወቅት ከሠራተኞች ተቋውሞ ተነስቷል፡፡ “የመሠረታዊ የሥራ ሒደት ለውጥ ትግበራ ሳይንሳዊ መንገድ ያልተከተለ ነው፤” ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ በኤጀንሲው ውስጥ ለ25 ዓመታት የሠሩ ሰው የቢፒአር አተገባበሩን በሕገ ወጥነት ይፈርጁታል፡፡ “ግማሹ መኪና ሲከፋፈል፣ ግማሹ ደመወዙን ሲያሳድግ፣ ግማሹ የሞባይል ካርድ ሲከፋፈል፣ እኛ ለአምስት ዓመታት ያለ አንዳች የደመወዝ ጭማሪ እየኖርን ነው፤” ሲሉ እኚሁ ሠራተኛ የኤጀንሲውን ብልሹ አሠራር በትዝብት ይገልጻሉ፡፡ 
የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ አሁን እስካለበት አደረጃጀት ድረስ ከመድረሱ በፊት በተለያዩ መዋቅሮችና የስም ለውጦች ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ኤጀንሲው የተቋቋመው የቻለው ሐምሌ 19 ቀን 1967 ዓ.ም የከተማ ቦታና ትርፍ ቤት የመንግሥት ንብረት ባደረገው አዋጅ ቁጥር 47/67 መሠረት ነው፡፡ በዚህ አዋጅ በርካታ ውርስ ቤቶችን ሲያስተዳድር የቆየው ኤጀንሲው ለረዥም ጊዜ በሥራ አመራር ቦርድ እየተመራ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ኤጀንሲው ከዚህ አሠራር ውጭ ሆኖ ተጠሪነቱ ለከተማ ልማት፣ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ነው፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር