የፍትሕ ስባቷና ተደራሽነቷ

የፍትሕ ተደራሽነትን (Access to justice) የፅንሰ ሐሳብ ትንተናና በአገራችን ያለውን አተገባበር መፈተሽ ለባለድርሻ አካላት (ለሕዝቡ፣ ለመንግሥት የፍትሕ አካላት እንዲሁም በመብት ላይ ለሚሠሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች) ያለው አስተዋጽኦ ሰፊ ነው፡፡
የፍትሕ ተደራሽነት የፍትሕ ፅንሰ ሐሳብ አካል ተደርጎ የሚወስድ ሲሆን፣ በራሱም የግለሰቦች መብት ነው፡፡

የፍትሕ ተደራሽነት ባልተረጋገጠበት ሁኔታ ባለመብት መሆን ትርጉም ያጣል፡፡ በሕግ የተቀመጡ መብትና ግዴታን አለማወቅ (ወይም ለማወቅ የሚያስችል ሁኔታ አለመኖር)፣ ቢታወቅም የሕግ ባለሙያ ዕርዳታ ባለማግኘት ወይም የዳኝነት ሥልጣን ያላቸው አካላት ተደራሽነት ባለመረጋገጡ መብትን አለመጠየቅ ወይም ለተጣሰ መብት ሕጋዊ መፍትሔ አለማግኘት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነው፡፡ ለመሆኑ በአገራችን ያሉ ሕጐች ለግለሰቦች የፍትሕ ተደራሽነት መብት ዋስትና ይሰጣሉ? የመብቱ አፈጻጸምስ በተግባር ምን ይመስላል? የሚሉትን ነጥቦች በፌዴራል ደረጃ መዳሰስ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ነው፡፡

የፍትሕ ተደራሽነት መብት ትርጉም
በፅንሰ ሐሳብ ደረጃ የፍትሕ ተደራሽነት መብት የፍትሕ ፈላጊውን ማዕከል በማድረግ ሰፋ ያለ ትርጉም ይሰጠዋል፡፡ የፍትሕ ተደራሽነት አንድን አጋጣሚ ብቻ የሚመለከት ሳይሆን፣ ፍትሕ ፈላጊው መብቱን ለማስከበር ተገቢ የሆነ መፍትሔ ለማግኘት የሚከተለውን ሒደት በሙሉ ያጠቃልላል፡፡ ግለሰቦች በተለይ ለመብት ጥሰት የተጋለጡ ሰዎች የደረሰባቸውን ኢፍትሐዊነት ለማወቅ የሚያስችላቸውና ኢፍትሐዊነቱ የሕግ የበላይነትን ወይም ሕግን መሠረት አድርጐ እንዲታረም በመንግሥት ተቋማት ውስጥ መፍትሔ የሚያገኙበትን ሒደት የፍትሕ ተደራሽነት መብት ልንለው እንችላለን፡፡

የፍትሕ ተደራሽነት በውስጡ ብዙ መብቶችን የሚያካትት ቢሆንም፣ በዚህ ጽሑፍ ምልከታ የሚደረግበት የሕግ ተደራሽነት (Access to law)፣ በጠበቃ (በሕግ ባለሙያ) የመታገዝ (Access to council) እና የፍርድ ቤት ተደራሽነት (Access to court) መብትን ይሆናል፡፡ የሕግ ተደራሽነት በአገሪቱ የሚወጡትን ሕጎች ኅብረተሰቡ የሚያገኝበትንና መብትና ግዴታውን የሚረዳበትን ሥርዓት ይመለከታል፡፡ ሕግ ተደራሽ ነው የሚባለው ሕጉ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ሊያገኘው የሚችለው ሲሆን፣ በቃላቱና በፅንሰ ሐሳብ አጠቃቀሙ ቀላልና ለመገንዘብ የማያስቸግር ሲሆን ነው፡፡  የሕግ ተደራሽነት በአግባቡ ባልተረጋገጠበት ሁኔታ ግለሰቦች በወጣው ሕግ ግዴታ እንዲፈጽሙ መጠየቅ ተገቢ አይሆንም፡፡ ሕግን አለማወቅ ይቅርታ አያሰጥም የሚለው የሕግ መርህ መሠረት የሚያደርገው፣ ኅብረተሰቡ በአገሪቱ የወጡትን ሕጎች በሙሉ ለማወቅ የሚችልበት ሁኔታ በመፈጠሩ ነው፡፡

በሕግ ባለሙያ የመታገዝ መብት ደግሞ አንድ ተጠርጣሪ ወይም የፍትሐ ብሔር ወይም የአስተዳደር ሙግት ተሳታፊ የሆነ ግለሰብ ለጉዳዩ የሚረዳውና ብቃት ያለው የሕግ ምክር በክፍያ ወይም ያለክፍያ ለማግኘት የሚችልበት አግባብ ነው፡፡ የሕግ ባለሙያ ምክር የማግኘት መብት በአብዛኛው ከወንጀል ጉዳይ ጋር በተገናኘ መታየቱ የተለመደ ቢሆንም፣ ወንጀል ነክ ባልሆኑ ጉዳዮችም መብቱ ተፈጻሚ ይሆናል፡፡ የፍትሐ ብሔር ጉዳዮች ምንም እንኳ እንደ ወንጀል ጉዳይ ሕይወትንና ነፃነትን የሚያሳጡ ባይሆንም፣ የንብረት መብትንና ማኅበራዊ ጥቅሞችን አደጋ ውስጥ የመክተት ውጤት ስለሚኖራቸው በፍትሐ ብሔር ጉዳይ የሕግ አማካሪ ዕርዳታ ማግኘት ጠቃሚ መብት መሆኑ ችላ ሊባል አይገባም፡፡ የፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕጎች ውስብስብነትና ጠበቃ መቅጠር ከሚችሉ ተሟጋቾች ጋር ያለውን ሚዛን ማጣት መመልከት የመብቱ አስፈላጊነትን የበለጠ ለመረዳት ያስችላል፡፡

ሌላው የፍትሕ ተደራሽነት መብት አካል የፍርድ ቤት ተደራሽነት ሲሆን፣ ፍርድ ቤቶች በጂኦግራፊያዊ አወቃቀራቸው፣ በመስተንግዶአቸውና በሚከተሉት አሠራር ሁሉ ለሕዝቡ የቀረቡ እንዲሆኑ የሚጠይቅ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የፍርድ ቤቶች በየአካባቢው መቋቋም፣ መደበኛ ያልሆኑ የዳኝነት አካላት ውሳኔዎች በፍርድ ቤቶች እንደገና የሚታዩበት ሁኔታ መኖር፣ የዳኝነት ክፍያ አለመጋነን፣ አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ሲሆን አስተርጓሚዎች የሚመደቡበት ሁኔታ ካለ ወዘተ የፍርድ ቤቶች ተደራሽነት መረጋገጡን አመላካች መስፈርቶች ይሆናሉ፡፡ ፍርድ ቤቶች ለሕዝቡ ተደራሽ ካልሆኑ መደበኛ ያልሆነ የዳኝነት ሥርዓት ስለሚነግስ የግለሰቦችን ሰብዓዊ መብት በዓለም አቀፍ መስፈርት መሠረት ማስከበር አዳጋች ይሆናል፡፡ በተጨማሪም የፍርድ ቤቶች ተደራሽነት ካልተረጋገጠ ሕዝብ በፍርድ ቤቶች ላይ ያለውን መተማመን የሚቀንሰው ይሆናል፡፡

የፍትሕ ተደራሽነት የሕግ መሠረት
የፍትሕ ተደራሽነት መብት በግልጽ ወይም በትርጉም በዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብቶች ስምምነት፣ በፌዴራሉና በክልሎች ሕግጋተ መንግሥት እንዲሁም በዝርዝር አዋጆችና ደንቦች ላይ ተደንግጎ እናገኘዋለን፡፡ የሰብዓዊ መብቶች ዓለም አቀፍ መግለጫ በአንቀጽ 10 ‹‹ማንም ሰው በመብቶችና ግዴታዎች እንዲሁም በተከሰሰበት ማንኛውም ወንጀል ውሳኔ ለማግኘት ሙሉ የእኩልነት መብቱ ተጠብቆ ነፃ በሆነና አድልዎ በሌለበት ፍርድ ቤት ሚዛናዊና ይፋ የሆነ ፍርድ የማግኘት መብት፤›› እንዳለው ይደነግጋል፡፡ ድንጋጌው የፍርድ ቤት ተደራሽነት መብትን በግልጽ የሕግና የሕግ ባለሙያ የማማከር መብትን በአንድምታ ዕውቅና ሰጥቷል፡፡ ሚዛናዊ የፍርድ ሒደት የሚኖረው ግለሰቦች በግልጽ በሚታወቅ ሕግ የተከሰሱበትን ነገር አውቀው በሕግ ባለሙያ እገዛ ከተከራከሩ መሆኑ አከራካሪ አይሆንም፡፡

የዚሁ ሰነድ አንቀጽ 8 ‹‹ማንም ሰው በሕገ መንግሥትም ሆነ በሌላ ሕግ የተሰጡትን መሠረታዊ መብቶች የሚጥስ ድርጊት በተፈጸመበት ጊዜ ሥልጣን ላላቸው የአገሩ ፍርድ ቤቶች አመልክቶ ውጤታማ መፍትሔ የማግኘት መብት አለው፤›› በማለት ለፍትሕ ተደራሽነት መብት ጥበቃ ይሰጣል፡፡ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃል ኪዳንም በተመሳሳይ መልኩ በአንቀጽ 14 የፍትሕ ተደራሽነትን በምልዓት የሚያስከብሩ ዘርዘር ያሉ መርሆችን አካቷል፡፡ አንቀጽ 14 (መ) ‹‹…ራሱ በተገኘበት የመዳኘት፣ ራሱን በግል ወይም በመረጠው ጠበቃ በኩል የመከላከል፣ ጠበቃ ከሌለው የሕግ አማካሪ ዕርዳታ የማግኘት መብት እንዳለው የማወቅ ትክክለኛ ዳኝነት የሚጓደል ሆኖ ሲታይና የገንዘብ አቅሙ የማይፈቅድ ሲሆን፣ ሳይከፍል ጠበቃ የማግኘት መብቱ….›› እንዲከበርለት ይደነግጋል፡፡

የፌዴራሉ ሕገ መንግሥት ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነቶችን ዕውቅና ከመስጠት ባለፈ በአንቀጽ 37 ‹‹ፍትሕ የማግኘት መብት›› በሚል ርዕስ ማንኛውም ሰው በፍርድ ሊወሰን የሚገባውን ጉዳይ ለፍርድ ቤት ወይም ለሌላ በሕግ የዳኝነት ሥልጣን ለተሰጠው አካል የማቅረብና ውሳኔ ወይም ፍርድ የማግኘት መብት አለው፤›› በማለት ለፍትሕ ተደራሽነት መብት የሕግ መሠረት ይጥላል፡፡ በተጨማሪም ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 19, 20 እና 21 ላይ ከወንጀል ጉዳይ ጋር በተያያዘ ለተያዙ ሰዎች፣ ለተከሰሱ ሰዎች እንዲሁም በጥበቃ ሥር ላሉ ሰዎች የፍትሕ ተደራሽነት መብትን በማካተት ዘርዘር አድርጎ አስቀምጧል፡፡

አንቀጽ 20 የተከሰሱ ሰዎች ‹‹በመረጡት የሕግ ጠበቃ የመወከል ወይም ጠበቃ ለማቆም አቅም በማጣታቸው ፍትሕ ሊጓደል የሚችልበት ሁኔታ ሲያጋጥም ከመንግሥት ጠበቃ የማግኘት መብት አላቸው፤›› በማለት ደንግጓል፡፡ በዚህ ድንጋጌ መሠረት በመንግሥት ወጪ ጠበቃ እንዲቆምለት የሚጠይቀው ሰው ክስ የቀረበበት፣ አቅም የሌለው መሆን ሲገባው በፍርድ ቤቱ እይታ ‹‹ፍትሕ ሊጓደል የሚችልበት ሁኔታም›› ሊያጋጥም ግድ ይላል፡፡ መብቱ ለተከሰሱ ሰዎች ብቻ መሰጠቱ የተያዙ ሰዎችና በጥበቃ ሥር ያሉ ሰዎች በመንግሥት ወጪ ጠበቃ እንዲቆምላቸው መጠየቅ የማይችሉ መሆኑን ያመለክታል፡፡ የደቡብ አፍሪካ ሕገ መንግሥት ግን ፍትሕ የሚጓደል መሆኑ እስከተረጋገጠ ድረስ ለተያዙም ሆነ በጥበቃ ሥር ላሉና በፍርድ ለታሰሩ ሰዎች በመንግሥት ጠበቃ (Assigned counsel) የመጠቀም መብት ያጎናጽፋል፡፡

የፍርድ ቤቶች ተደራሽነትን በተመለከተ ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 78 በፌዴራልና በክልሎች ሦስት እርከን ደረጃ ያላቸው ፍርድ ቤቶች እንደሚቋቋም ከመግለጹ በተጨማሪ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ሆነ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በአገሪቱ በሙሉ ወይም በከፊል እንዲደራጅ በሁለት ሦስተኛ ድምፅ ሊወሰን ይችላል በማለት ለፍርድ ቤቶች ጂኦግራፊያዊ ተደራሽነት መሠረት የሚጥል ድንጋጌ ይዟል፡፡ ይህ ካልሆነም ክልሎች የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትንና የከፍተኛ ፍርድ ቤትን ሥልጣን በውክልና የተሰጣቸው መሆኑን ይደነግጋል፡፡ በዚህ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ መሠረት በተወሰኑ ቦታዎች የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የተቋቋሙ ሲሆን፣ የተወሰኑ ክልሎች ደግሞ የፌዴራል ጉዳይን በውክልና በማየት ላይ ይገኛሉ፡፡

 በአዋጅ ቁጥር 322/1995 የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በአፋር፣ በቤኒሻንጉል፣ በጋምቤላ፣ በሶማሌና በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የተቋቋመ ሲሆን፣ በተግባር በአግባቡ እየተሠራበት ስለመሆኑ ጥናት ይፈልጋል፡፡ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ሥልጣን በውክልና የተሰጣቸው ክልሎች የፌዴራል ጥናት ጉዳዮችን ሲዳኙ የፍርድ ቤቱ ቋንቋ የፌዴራሉ የሥራ ቋንቋ ይሆናል ወይስ የክልሉ የሥራ ቋንቋ የሚለው ሌላው ሊጠና የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡ የሆኖ ሆኖ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች በተቋቋሙበት ቦታ ፍርድ ቤቶች በአግባቡ የማይሠሩ ከሆነና በውክልና መሠረት ጉዳዮችን የሚመለከቱ ፍርድ ቤቶች የሚጠቀሙት የክልሉን የሥራ ቋንቋ በሆነ ጊዜ የፍርድ ቤቶቹ ተደራሽነት ጥያቄ ውስጥ ይገባል፡፡

የክልሎች ሕግጋት መንግሥት የፍትሕ ተደራሽነትን በተመለከተ ከፌዴራሉ ጋር ተመሳሳይ ድንጋጌዎችን የያዙ በመሆናቸው በዝርዝር መዳሰሱ አላስፈለገም፡፡ ከሕገ መንግሥት ውጪ ያሉት ሕጎችን ምልከታ እናድርግ፡፡ ከሕገ መንግሥቱ በፊት ሥራ ላይ ለዘመናት የነበሩት የሥነ ሥርዓት ሕጎች የግለሰቦችን በሕግ አማካሪ የመጠቀም መብትን ዕውቅና ይሰጣሉ፡፡ የፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 57 አቤት ባዩ ራሱ እንዲቀርብ ፍርድ ቤት ካላዘዘ በቀር በማንኛውም ፍርድ ቤት አቤቱታ ለማቅረብ፣ ለመከራከር፣ ነገሩን ለማስረዳት በነገረፈጅ፣ በተወካይ ወይም በጠበቃ እንዲከራከር መወከል እንደሚችል ደንግጓል፡፡ ይህ ድንጋጌ ተፈጻሚነቱ ጠበቃ ለመቅጠር በሚቻሉ ሰዎች እንጂ ለማይችሉ ባለመሆኑ የፍትሕ ተደራሽነት ላይ የተወሰነ ገደብ አለው፡፡ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጉም በአንቀጽ 65 የተያዘ ወይም የታሰረ ወይም በጊዜ ቀጠሮ ያለ ሰው ጠበቃውን የመጥራትና የማማከር መብት እንዳለው ቢደነግግም፣ በመንግሥት ወጪ ሊቆም ስለሚችል ጠበቃ የሚለው ነገር ባለመኖሩ በፍትሕ ተደራሽነት መብት አፈጻጸም ክፍተት አለው፡፡ ምክንያቱም የፍትሕ ተደራሽነት መብት ጠበቃ መቅጠር በሚችል ሰው ሚዛን ከሚለካ ይልቅ መቅጠር ባልቻለውና ሕጉ በፈጠረለት ድጋፍ የሚለካ በመሆኑ ነው፡፡

የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ጠበቆች የሥነ ምግባር ደንብ ቁጥር 57/1992 በአንቀጽ 49 ነፃ የሕግ አገልግሎት ስለመስጠት (Pro Bono Publico Service) ይደነግጋል፡፡ በዚሁ መሠረት ማንኛውም ጠበቃ በነፃ ወይም በአነስተኛ ክፍያ በዓመት ቢያንስ የ50 ሰዓት የሕግ አገልግሎት መስጠት አለበት፡፡ አገልግሎት የሚሰጠውም የመክፈል አቅም ለሌላቸው ሰዎች፣ ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች፣ ለሲቪል ድርጅቶች፣ ለማኅበረሰብ ተቋማት ፍርድ ቤት የጥብቅና አገልግሎት እንዲያገኙ ለሚጠይቃቸው ሰዎች፣ ሕግን፣ የሕግ ሙያንና የፍትሕ ሥርዓቱን ለማሻሻል ለሚሠሩ ኮሚቴዎችና ድርጅቶች ነው፡፡
ይህ ድንጋጌ ለፍትሕ ተደራሽነት ያለው ጠቀሜታ ሰፊ ቢሆንም፣ በተግባር ያለውን አፈጻጸም የሚገዛ መመርያ ባለመኖሩ ተፈጻሚነቱን መገምገም አስቸጋሪ ነው፡፡ ሆኖም አንዳንድ ጠበቆች አገልግሎቱን እንደሚሰጡ ጸሐፊው በተሞክሮው ያውቃል፡፡

በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ጠበቆች ፈቃድ አሰጣጥና ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 199/2000 መሠረት የፍትሕ ሚኒስቴር ከሚሰጣቸው ሦስት ፈቃዶች ውስጥ አንዱ የሆነው ልዩ የጥብቅና ፈቃድ ለፍትሕ ተዳራሽነት ያለው ሚና ከፍ ያለ ነው፡፡ ይህ ፈቃድ የሚሰጠው የኅብረተሰቡን አጠቃላይ መብትና ጥቅም ለማስከበር ለሚሟገት፣ በቂ የሕግ ትምህርትና ልምድ ላለው፣ ከደንበኞቹ ምንም ዓይነት ክፍያ የማይቀበል የተመሰከረለት ሥነ ምግባር ላለው ኢትዮጵያዊ ሲሆን፣ የጥብቅና ፈቃድ ያለው መስፈርቶቹን ካሟላ ደግሞ ለሚኒስቴሩ በማሳወቅ አገልግሎቱን መስጠት ይችላል፡፡ ይህ ፈቃድ ለተፈጥሮ ሰው እንጂ በሕግ ሰውነት ለተሰጣቸው ተቋማት የሚሰጥ ባለመሆኑ ለመብት ጥሰት የተጋለጡ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ጥቅም ለማስከበር የተቋቋሙ ድርጅቶች በዚህ ፈቃድ ሊጠቀሙ የሚችሉበት አግባብ የለም፡፡ ልዩ የጥብቅና ፈቃድ በማውጣት ለኅብረተሰብ ጥቅም ጥብቅና መቆም በብዛት ያልተለመደ ሲሆን፣ ፍርድ ቤቶች አካባቢ ከተለጠፉ ማስታወቂያዎች ለመረዳት እንደተቻለው ፍትሕ ሚኒስቴር ልዩ የጥብቅና ፈቃድ እንዲኖር፣ እንዲስፋፋም ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑን ነው፡፡

የተከላካይ ጠበቆች ቢሮ በሙሉ ጊዜ ተቀጣሪ የሕግ ባለሙያዎች ነፃ የሕግ ምክርና ጥብቅና የሚሰጥበት አሠራር ነው፡፡ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 25/1996 አንቀጽ 16(2) (በ) የፌዴራል የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት የተከላካይ ጠበቆች ቢሮን ያደራጃል በሚል ደንግጓል፡፡ በዚህ መሠረት ቢሮው በፌዴራል ፍርድ ቤት የተቋቋመ ሲሆን፣ በወንጀል የተከሰሱ ሰዎች ሊወስዱት ስለሚገባው ዕርምጃ መምከርና በወንጀል ችሎት ተከሳሾችን ወክሎ በመቅረብ ይከራከራል፡፡ ይህ ቢሮ ያሉት ባለሙያዎች ቁጥር ማነስ፣ ጠንከር ያለ የአስተዳደርና የቁጥጥር ሥርዓት አለመኖር እንዲሁም አገልግሎቱ በከባድ ወንጀል ለተከሰሱ በዳኞች ጥያቄ መሠረት የሚሠራ ብቻ እንጂ በባለጉዳዮቹ ጥያቄ አለመሆኑ የሚሰጠው አገልግሎት የፍትሕ ተደራሽነትን በማረጋገጥ ረገድ አነስተኛ ሆኗል፡፡

በበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት አዋጅ ቁጥር 621/2001 አገር በቀል የበጎ አድራጎት ድርጅቶች የፍትሕ ሥርዓቱን ለመርዳት፣ የግለሰቦች ሰብዓዊ መብት በተለይም የሴቶች፣ የሕፃናትና የአካል ጉዳቶኞች መብት እንዲከበር ለመሥራት እንዲችሉ ተደንግጓል፡፡ ይህ የሕግ ማዕቀፍ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች የፍትሕ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ሥራዎች (የፓራ ሌጋል ሥልጠናና የሕግ ምክርን ጨምሮ) ላይ እንዲሳተፉ ቢፈቅድም፣ በአዋጁ መሠረት እነዚህ ድርጅቶች የበጀታቸውን 90% (ዘጠና በመቶ) ከአባላት መዋጮና ከአገር ውስጥ ምንጭ ማግኘት ስለሚጠበቅባቸው በበጀት እጥረት ምክንያት አገልግሎቱን ለመስጠት ይቸገራሉ፡፡

አዋጁ ከመወጣቱ በፊት በመብት ላይ የሚሠሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት በአንድነትና በነጠላ በመላው ኢትዮጵያ ነፃ የሕግ ምክር፣ የፓራ ሌጋል ሥልጠናና በፍርድ ቤት የውክልና አገልግሎት ይሰጡ ነበር፡፡ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር፣ አክሽን ባለሙያ ማኅበር ለሕዝብ፣ የኢትዮጵያ ጠበቆች ማኅበር፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ፋኩልቲ የቀድሞ ተማሪዎች ማኅበር ተጠቃሽ ነበሩ፡፡ ከአዋጁ መውጣት በኋላ የተወሰኑት አወቃቀራቸውን በመለወጥ የተዋቀሩ በመሆኑ ሌሎች ደግሞ በበጀት እጥረት ምክንያት አገልግሎቱን እንደቀድሞው ለመስጠት አለመቻላቸው፣ በፍትሕ ተደራሽነት ላይ የራሱ አሉታዊ አስተዋጽኦ አሳድሯል፡፡

ለአብነት ያህል የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበርን ብንወስድ ቀደም ሲል አዲስ አበባና ድሬዳዋን ጨምሮ በአምስት ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥታት ባሉት ቅርንጫፎች፣ በተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች በሚገኙ ፈቃደኛ አባላት የፓራ ሌጋል ሥልጠና፣ የሕግ ምክርና በፍርድ ቤት የመወከል ሥራዎችን ይሠራ ነበር፡፡ በተጨማሪም በነፃ የስልክ መስመር 940 ለማንኛውም የኅብረተሰብ ክፍል የሕግ ምክር በመስጠት የፍትሕ ተደራሽነትን ረዘም ያለ መንገድ ወስዶት ነበር፡፡ ከአዋጁ መወጣት በኋላ ግን ከ70 በመቶ በላይ ሠራተኞቹን በመቀነስ የሚሰጣቸው የሕግ ምክርና የውክልና አገልግሎት በቁጥር የቀነሰ ከመሆኑ ሌላ በነፃ የስልክ መስመር የሚሰጠውን አገልግሎት አቋርጧል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ማኅበሩ ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጋር በመተባበር የነፃ ምክር አገልግሎት እየሰጠ ቢሆንም፣ ጥንካሬው የቀድሞውን ያህል አይደለም፡፡

ከነፃ የሕግ ምክር አገልግሎት ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከተወሰኑ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሕግ ፋኩልቲዎች ጋር በመተባበር በመስጠት ላይ ነው፡፡ የአገልግሎቱ ስፋት ጥራትና ቀጣይነት ራሱን የቻለ ጥናት የሚፈልግ ቢሆንም፣ ቢያንስ በበጎ አድራጎት ድርጅቶች አዋጅ ምክንያት የተፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት የሚያስችል ሥራ በመሆኑ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡

ከፍትሕ ተደራሽነት መብት ጋር የሚስተዋሉ ችግሮች
ከዚህ በላይ እንደተመለከትነው፣ የፍትሕ ተደራሽነትን መብትን የሚያረጋግጡ ሕጎች መኖራቸው መልካም ቢሆንም፣ ሕጎቹ የተወሰነ ክፍተቶች ይታይባቸዋል፡፡ የሥነ ሥርዓት ሕጎቹ የፍትሕ ተደራሽነትን በሕግ አማካሪ መታገዝን በመፍቀድ የሚያረጋግጡ ቢሆንም፣ ሕጎቹ በሕግ ቴክኒካዊ ቃላት (Legal jargons) የተሞሉና ውስብስብ መሆናቸው ለኅብረተሰቡ ተደራሽ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል፡፡ እንኳን ሙያውን የማያውቀው ሕዝብ ባለሙያዎች እንኳን የሥነ ሥርዓቱን ሕግ በመተርጎም ረገድ ልዩነት ያላቸው መሆኑ፣ ተደራሽነት ማጣትን ሰፊ ያደርገዋል፡፡

ሌሎቹም መሠረታውያን ሕጎች ቢሆን ሕዝቡ ሊረዳቸው በሚያስቸግሩ ቃላት የተሞሉ በመሆኑ መብትና ግዴታን የሕግ ባለሙያ ጠይቆ ካልሆነ በቀር አንብቦ መረዳት ያስቸግራል፡፡ ሕጎቹ ከወጡ በኋላም ቢሆን በበቂ ኮፒ በየቦታው የማይገኙ መሆኑ፣ ሕጉ ለመታተም የሚወስድበት ጊዜ ረዥም በመሆኑና በዚህ ጊዜ ሳይቀር ኅብረተሰቡ ሳያውቀው ተፈጻሚነት ያለው መሆኑ ተደራሽነቱን ይፈታተናል፡፡ የሕጎች የመግዣ ዋጋ ከፍተኛ መሆኑ፣ ኅብረተሰቡ ሕጉን የሚያውቅበትን ሁኔታ የሚፈጥሩ አሠራሮች በመንግሥት አለመሥራታቸው፣ አብዛኛው በገጠር አካባቢ የሚኖር ኅብረተሰብ ማንበብና መጻፍ የማይችል መሆኑ የሚወጡ ሕጎች ተደራሽነት አናሳ እንዲሆን አድርጓል፡፡ በተግባር እንደምናስተውለው እንኳን ኅብረተሰቡ አንዳንድ የሕግ ባለሙያዎች ዳኞችን ጨምሮ የወጡትን ሕጎች በሙሉ ለማወቅ ይቸገራሉ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የሕግ ያህል ውጤት ያላቸው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት ውሳኔዎች በፍጥነት አለመታተማቸው፣ የስርጭታቸው ማነስና የውሳኔዎቹ መብዛት የሕግ ተደራሽነት ላይ አሉታዊ አስተዋጽኦ አለው፡፡

ከሕግ ባለሙያ ተደራሽነት ጋር በተያያዘ የሚነሱ ችግሮች ብዙ ናቸው፡፡ የሕግ ባለሙያ እጥረት መኖሩ በተለይ በገጠራማው የኢትዮጵያ አካባቢ፣ የጠበቆች የክፍያ ዋጋ የኅብረተሰቡን አቅም ያላገናዘበ መሆኑ፣ በአንዳንድ ጠበቆች የሚስተዋሉ የሥነ ምግባር ጉድለቶች መኖራቸው፣ የጠበቆች ነፃ የሕግ ምክር አገልግሎት የመስጠት ግዴታቸውን አለመወጣታቸው፣ ፍትሕ ሚኒስቴርም ለመቆጠጠር የሚያስችል ሥርዓት አለመዘርጋቱ፣ የተከላካይ ጠበቃ ቢሮ በአግባቡ ተደራጅቶ አለመሥራቱ፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች የሕግ ምክር አገልግሎት መዳከሙ ተጠቃሽ ችግሮች ናቸው፡፡

የፍርድ ቤቶች ተደራሽነት በተመለከት በፌዴራልም ሆነ በክልሎች የተለያየ እርከን ያላቸው ፍርድ ቤቶች የተቋቋሙ ቢሆንም፣ የጂኦግራፊያዊ ተደራሽነቱ እንከን የለውም ለማለት አይቻልም፡፡ ብዙ ርቀት ተጉዘው የክልሎች ጠቅላይ ፍርድ ቤቶችን አገልግሎት የሚያገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ቀላል አይደሉም፡፡ የፌዴራል ፍርድ ቤቶችን በውክልና የሚያስችሉ የክልል ፍርድ ቤቶችም በክልሉ ቋንቋ በማስተናገድ የሚፈጠሩ ተደራሽነትን የሚያሳጡ ችግሮች መኖራቸውን ጸሐፊው አስተውሏል፡፡ የፍርድ ቤቶች የችሎት አስተዳደርም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ለደንበኞች በተለይም ለሕፃናት ምቹ (Client friendly) አልነበሩም፡፡ ፍርድ ቤት ለመቅረብ በማሰብ የሚጨነቅ፣ ችሎት ቆሞ የሚንቀጠቀጥ፣ ክርክሩን በአግባቡ ለማስተላለፍ የሚቸገር ተሟጋች የሚስተዋለው በዚሁ ምክንያት ነው፡፡

የፍትሕ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ምን ይደረግ?
የፍትሕ ተደራሽነት (Access to justice) ለብዙ መብቶች መከበር ወሳኝ ነው፡፡ የፍትሕ ተደራሽነት መብት ካልተከበረ ሰዎች መብትና ግዴታቸውን አያውቁም፤ ቢያውቁም አይጠይቁም፤ ቢጠይቁም አርኪ መፍትሔ አያገኙም፡፡ የፍትሕ ተደራሽነት መብት ከተረጋገጠ ግን ግለሰቦች መብቶቻቸውን በአግባቡ ያስከብራሉ፤ በፍትሕ ሥርዓቱም ላይ ያላቸው መተማመን ይጨምራል፡፡ ይህን ለማድረግ በፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ ያሉ አካላት (ፍትሕ ሚኒስቴር፣ ፍርድ ቤት) ሰፊ ሥራ መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡

ግልጽ ፖሊሲ መቅረፅ፣ የፍትሕ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በሕግ የቀመጡ ግዴታዎችን መፈጸም፣ መመርያዎችን ማውጣት፣ ባለሙያዎችን በስፋት አሠልጥኖ ማሰማራት ይጠበቃል፡፡ ሕዝቡ ሕጉን እንዲያውቅ በቀላሉ እንዲደርሰው ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ መንግሥትና የአገር በቀል በጎ አድራጎት ድርጅቶች ደግሞ እርስ በርሳቸው በሚያደርጉት ስምምነት (Bi-lateral Agreement) ለፍትሕ ተደራሽነት ፕሮጀክት ገንዘብ ቢያፈላልጉና ቢሠሩ መልካም ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሕግ ባለሙያ ቤቶች ማኅበር ተጀምሮ የተቋረጠው የሕግ ምክር አገልግሎት በነፃ የስልክ መስመር የመስጠት አገልግሎት በፍትሕ ሚኒስቴር ቢቀጥልስ ምን ይለዋል?

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን የሕግ ጠበቃና አማካሪ ሲሆኑ፣ በኢሜይል አድራሻቸው getukow@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር