ሕዝብ ‹‹መልካም አስተዳደር በተግባር!›› እያለ ነው

መንግሥት መልካም አስተዳደር መኖር አለበት ይላል ወይ? አዎን! ኢሕአዴግም በጉባዔው ብሏል፣ በውሳኔም አሳልፏል፡፡ በየቀኑ መግለጫ ይሰጥበታል፡፡ መልካም አስተዳደር እውን የማታደርጉ ወዮላችሁ ብሏል፡፡ የመልካም አስተዳደር አለመኖር አደጋንም ገልጿል፡፡
መንግሥትም ብሏል፣ ኢሕአዴግም ብሏል፣ ሕዝብም ሰምቷል፣ አዳምጧል፡፡  ጥያቄው የተባለው፣ የተወሰነውና ቃል የተገባው መልካም አስተዳደር የት አለ የሚል ነው፡፡ የሕዝቡ ጥያቄ ‹‹መልካም አስተዳደር በተግባር!›› ነውና፡፡ በተግባር ያልታየ ነገር ‹‹ላም አለኝ በሰማይ ወተቷንም አላይ›› ነውና፡፡ መንግሥት በፌዴራል ደረጃም በክልል ደረጃም ወደ ተጨባጭና አሳማኝ ተግባር ይግባ፡፡ ይናገር ሳይሆን ያሳይ፡፡ 
በዚህ መሥሪያ ቤት ሕዝቡ መልካም አስተዳደር አላገኘም ከተባለ መንግሥት ያንን መሥሪያ ቤት ገባ ብሎ መመርመርና መፈተሽ አለበት፡፡ በመልካም አስተዳደር መጥፋት ምክንያት ያላግባብና ከሕግ ውጭ የተሰጠ ጥቅም ካለ ውሳኔው ትክክል አልነበረም በማለት፣ የወሰኑት ሰዎችም መጠየቅ አለባቸው ብሎ የማስተካከያና የእርምት ዕርምጃ መውሰድ አለበት፡፡ 
በመልካም አስተዳደር ምክንያት በደል የደረሰባቸው ዜጎች ካሉ ፈትሾ ያላግባብና ከሕግ ውጭ መብታቸው ተጥሷል፣ ተጎድተዋል በማለት የደረሰባቸው በደል እንዳይቀጥል አስተካክሎ፣ አርሞና ይቅርታ ጠይቆ ትክክለኛ ዕርምጃ ሊወስድ ይገባል፡፡ ያኔ ነው ሕዝብ እውነትም መልካም አስተዳደር አለ የሚለው፡፡ እውነትም ለመልካም አስተዳደር ከልብ ቆሟል ብሎ ሕዝብ የሚያምነውና ከጎኑ የሚቆመው፡፡ ስለዚህ ተግባር! ተግባር! አሁንም ተግባር!
መንግሥት ለመልካም አስተዳደር መስፈን እንቅስቃሴ ሲያደርግ ሥራው ቀላልና ፈጣን ይሆንለታል ማለት አይደለም፡፡ ሴረኛ ያደናቅፈዋል፡፡ ሙሰኛና ፀረ መልካም አስተዳደር በተቃራኒው ትግሉን ያፋፍማል፡፡ ኔትወርክ ይዘረጋል፡፡ ለማደናቀፍ የሚራወጠው ይበዛል፡፡ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ 
ይህ ችግር ግን ለመንግሥት አዲስ ሊሆንበት አይገባም፡፡ የሚጠበቅ ነውና ጥቅሙ የሚነካበት ሁሉ መሯሯጡና መወራጨቱ አይቀርም፡፡ ይህ እንደሚኖር በማወቅ ነው በቂና ብቃት ያለው የሰው ኃይል ማሳለፍ ያለበት፡፡ 
መንግሥት ልማቱን ለማቀላጠፍ ‹‹የልማት ሠራዊት›› እንፍጠር እያለ ነው፡፡ እየተንቀሳቀሰም ነው፡፡ አገርን ከጠላት ለመከላከል ‹‹የመከላከያ ሠራዊት›› እንደሚያስፈልግ ሁሉ፣ ልማቱን ለማቀላጠፍ ‹‹የልማት ሠራዊት›› እንደሚያስፈልግ ይገልጻል፡፡ መንግሥት በነካ እጁ ‹‹የመልካም አስተዳደር ሠራዊት›› ይፈጠር ማለት አለበት፡፡ መፍጠርም አለበት፡፡ በአስቸኳይና በብዛት፡፡ 
መልካም አስተዳደርን የሚያበላሽና ዜጎችን የሚበድል በሥልጣን ወንበር ላይ ተቀምጦ እንዲቀጥል ሊፈቀድ አይገባም፡፡ በድሎ ከሆነም ከሥልጣን ማንሳት ብቻም በቂ አይደለም፡፡ ተጠያቂነት መኖሩ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን አንዱ ዋስትና ነው፡፡ መልካም አስተዳደርን የሚረግጡ፣ የዜጎችን መብት የሚጥሱ፣ ሕዝብን የሚያስለቅሱና የሚገፉ ካሉ መጠየቅ አለባቸው፡፡ ጥሩ ሲሠሩ መመስገንና ማደግ እንደሚገባቸው ሁሉ ሲያጠፉም መነሳትና መጠየቅ ይገባቸዋል፡፡ 
ለመልካም አስተዳደር ጉድለት ምክንያት ጉቦና ክፋት ብቻ ናቸው እያልን አይደለም፡፡ አንልምም፡፡ የአቅም ማነስ ተጠቃሽ ነው፡፡ ለሥራው ተመጣጣኝ የሆነ አመለካከትና አቅም አለመኖር መልካም አስተዳደርን ያበላሻል፡፡ በመሆኑም የአቅም ግንባታ ያስፈልጋል፡፡ የአቅም ግንባታ በኮንፈረንስና በስብሰባ ብቻ ይገኛል ብሎ መጠበቅ ግን የዋህነት ነው፡፡ 
ከመነሻው አቅም ያለው ያስፈልጋል፡፡ በዚያ ላይ ሥልጠና ያስፈልጋል፡፡ በሥራ ገበታ ላይ ክትትልና ቁጥጥር እያደረጉና ጉድለትን እያሳዩ ማሠልጠንም ያስፈልጋል፡፡ ይህ የማያቋርጥ ሒደት መሆን ይገባዋል፡፡ 
ከመጀመሪያው የመሥሪያ ቤቶች አወቃቀርና የኃላፊነት ድልደላ ሲካሄድም ልዩ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ ከመጀመሪያው ስላልታሰበበትና ጥናት ስላልተካሄደበት መሥሪያ ቤቶች የተሰጣቸውን ኃላፊነት ማከናወን አቅቶዋቸው ዜጎች ሲንገላቱ ማየት የተለመደ ነው፡፡
ለማሳያ ያህል አንድ ቀላልና አጭር ማሳያ እንጥቀስ፡፡ የኢትዮጵያ የጋዜጣና የመጽሔት አሳታሚዎች ማኅበር ለመመሥረት ስምምነት ተደርጎ አስፈላጊው ሰነድ ሁሉ ተዘጋጀ፡፡ ፈቃድ ይሰጣል ለተባለው ለማኅበራት ምዝገባ አካል ቀረበ፡፡ ዛሬ ነገ እየተባለ አምስት ወራት ካለፉ በኋላ፣ ይቅርታ እኛ አንመዘግብም ፈቃድ አንሰጥም ተብሎ ወደ ንግድ ማኅበራት ምዝገባ አካል ተመራ፡፡ ከአምስት ወራት በኋላ ወደ ንግድ ሚኒስቴር ሲኬድ ወደ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሂዱ ተባለ፡፡ ወደ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሲኬድ የለም ተነጋግረናል ወደ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ተመለሱ ተባለ፡፡ ንግድ ሚኒስቴርም ተነጋግረናል ወደ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሂዱ አለ፡፡ ይኼው አንድ ዓመት ሞላው፡፡ ይህ ማኅበር የሚመዘግበውና የሚፈቅድለት አካል አጥቶ እስካሁን ተቀምጧል፡፡ ይኼ ቀላል ማሳያ ነው፡፡ ከዚህ የበለጡ ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ ዜጎችን የሚያስመርሩ፡፡
መሥሪያ ቤቶች ትክክለኛ ሥራቸውና ኃላፊነታቸው በዝርዝርና በሕግ ሳይሰጣቸው ኃላፊነት ተሰጥቷችኋል ይባሉና በተግባር አያሳዩትም፡፡ በዚህ ምክንያት ዜጎች ይንከራተታሉ፡፡  የመልካም አስተዳደር ጉድለት በአገርና በሕዝብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ ነው፡፡ ሕዝባዊ አመኔታን ይሸረሽራል፡፡ ዜግነትን ጥርጣሬ ውስጥ ይከታል፡፡ ሙሰኞችን ይፈጥራል፣ ያጠናክራል፣ ኢንቨስትመንት ያዳክማል፣ የውጭ አገር ዜጎች ወደ አገራችን እንዳይመጡ ይገፋል፣ የመንግሥትን ገቢ ይቀንሳል፣ ልማትን ይገታል፡፡ ኧረ ስንቱ!
እናስ?
እናማ ብዙ ተነግሯል፣ ብዙ መግለጫ ወጥቷል፣ ብዙ ቃለ ምልልስ ተደምጧል፡፡ ቃላት በዙ ተግባር ጠፋ፡፡ 
ስለዚህ? 
መልካም አስተዳደር በተግባር! 

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር