የቀድሞው የደቡብ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽፈራው ሸጉጤ በወቅታዊ ችግሮች ዙሪያ ለመምከርና ጥሩ የሥራ አፈጻጸም ያላቸውን ኢንቨስተሮች ለማበረታታት በጠሩት ስብሰባ ላይ፣ ኢንቨስተሮች በኢትዮጵያ ልማት ባንክ መማረራቸውን አስታውቀዋል፡፡

ኢንቨስተሮች በኢትዮጵያ ልማት ባንክ ተማረሩ

ልማት ባንክ ቅሬታቸውን አልተቀበለም
ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ከአዲስ አበባ 275 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሐዋሳ ከተማ የተሰበሰቡ ኢንቨስተሮች፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለአገር ውስጥ ኢንቨስተሮች ብድር እየሰጠ አይደለም ሲሉ አማረሩ፡፡ 
ሐሙስ ሰኔ 27 ቀን 2005 ዓ.ም. የትምህርት ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት የቀድሞው የደቡብ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽፈራው ሸጉጤ በወቅታዊ ችግሮች ዙሪያ ለመምከርና ጥሩ የሥራ አፈጻጸም ያላቸውን ኢንቨስተሮች ለማበረታታት በጠሩት ስብሰባ ላይ፣ ኢንቨስተሮች በኢትዮጵያ ልማት ባንክ መማረራቸውን አስታውቀዋል፡፡ 
ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ‹‹በትራንስፎርመር እጥረት›› በሚል ምክንያት የኤሌክትሪክ አቅርቦት ችግር እየገጠማቸው መሆኑን በመጥቀስ ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡ 
በተወሰነ ደረጃ በኢትዮ ቴሌኮም በኩልም ችግር መኖሩን የሚጠቅሱት ኢንቨስተሮች በክልሉ በኩልም የመሬት አቅርቦት፣ በዞኖችና ወረዳዎች የመልካም አስተዳደር እጦትና የወሰን ማስከበር ችግሮች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡ 
በደቡብ ክልል ከ1985 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 2005 ዓ.ም. ድረስ 6,150 ኢንቨስተሮች ፈቃድ አውጥተው ቦታ ወስደዋል፡፡ ለስብሰባ የተጠሩት ውጤታማ ናቸው የተባሉ 1,500 የአገር ውስጥና የውጭ አገር ኢንቨስተሮች ናቸው፡፡ 
ኢንቨስተሮቹ የተሰማሩት በእርሻ፣ በአግሮ ኢንዱስትሪ፣ በአገልግሎት መስጫዎችና በኢንዱስትሪ ዘርፍ ነው፡፡ እነዚህ ኢንቨስተሮች ሥራቸውን ለማስፋፋት ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ብድር ቢጠይቁም ሊሰጣቸው እንዳልቻለ፣ በአንፃሩ ባንኩ ለውጭ ኩባንያዎች ከፍተኛ መጠን ያለው ብድር ሲሰጥ መታዘባቸውን በመናገር ምሬታቸውን ገልጸዋል፡፡ 
የኢትዮጵያ ልማት ባንክን እያማረሩ የሚገኙት የደቡብ ክልል ኢንቨስተሮች ብቻ አይደሉም፡፡ በሁሉም ክልሎችና የክልል ከተሞች የሚገኙ የአገር ውስጥ ኢንቨስተሮች ባገኙት አጋጣሚ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የአገር ውስጥ ኢንቨስተሮችን ወደጐን በማድረግ፣ ለውጭ ኢንቨስተሮች ብድር እንደሚፈቅድ በመጥቀስ ቅሬታቸውን ሲያሰሙ ማስተዋል እየተለመደ ነው፡፡ 
እነዚህ ኢንቨስተሮች እንደሚሉት ከሆነ፣ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ለአገር ከሚያመጣው አንዱና ዋነኛው የፋይናንስ አቅም ያለው ኢንቨስተርን ማስገኘት ሲሆን፣ አሁን በሚታየው ሁኔታ ከፍተኛ የአገር ውስጥ ብድር ተሻሚ መሆናቸው ግራ መጋባት ተፈጥሮባቸዋል፡፡ 
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ባህረ የኢንቨስተሮቹን ጥያቄ አይቀበሉትም፡፡ አቶ ኢሳያስ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ቅድሚያ የሚሰጣቸው በተመረጡ የኢንቨስትመንት መስኮች ኢንቨስት ለሚያደርጉ ኢንቨስተሮች ነው፡፡ በዚህ መርህ መሠረትም ብድር እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ባንኩ ቅድሚያ የሚሰጣቸውም ዘርፎች ኢንዱስትሪና ግብርና ሲሆኑ፣ ለአገልግሎት ሰጪ ኢንቨስተሮች ብድር እንደማይሰጥ ገልጸዋል፡፡ አቶ ኢሳያስ ባንኩ ቅድሚያ በሚሰጣቸው ዘርፎች ፕሮጀክቶችን ይዞ መጥቶ ብድር የተከለከለ ካለ መነጋገር እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡
የውጭ ኢንቨስተሮችን በሚመለከት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ላይ የሚሰማሩ ተቋማት በአብዛኛው የሚሰማሩት ባንኩ ቅድሚያ በሚሰጣቸው ዘርፎች እንደሆነ ጠቅሰው፣ እነዚህ የውጭ ኢንቨስተሮች ከባንኩ ብድር የሚሰጣቸው የሚያመርቷቸው ምርቶች ገበያ ስላላቸው የቴክኖሎጂ ሽግግርን ያፋጥናሉ በሚል እሳቤ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ብድር ተጠቃሚ የሆኑ የውጭ ኢንቨስተሮች ቁጥር አነስተኛ ቢሆንም፣ ከፕሮጀክቶቹ ግዝፈት አንፃር ከአገር ውስጥ ኩባንያዎች ጋር ሲነፃፀር ባንኩ ከ50 በመቶ ያላነሰ ብድር ፈሰስ ያደረገላቸው መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር