የኢትዮጵያ ቡና ከዓለም ገበያ እየራቀ መሆኑ ሥጋት ፈጥሯል

የኢትዮጵያ ቡና ከዓለም አቀፍ ገበያ እየራቀ መጥቶ፣ ከነጭራሹ ሊወጣ የተቃረበበት ጊዜ ላይ እንደሚገኝ ለዘርፉ ቅርብ የሆኑ ተዋንያዎች የሚስማሙበት ሀቅ ነው፡፡ 
ኢትዮጵያ ለዓለም ቡናን ያበረከተች አገር ከመሆኗ ባሻገር እጅግ ተወዳጅ የሆነ ቡና የምታመርት አገር ናት፡፡ ዓለም አቀፍ የቡና ገዥዎች ይህንኑ የጣዕም ልዩነት በመረዳት የኢትዮጵያን ቡና ለመግዛት ከፍተኛ ፍላጎት ቢኖራቸውም፣ በቢሮክራሲ ውጥንቅጦች ምክንያት ቡናውን ማግኘት እንዳልቻሉ እየተናገሩ ነው፡፡ 
በቡና ግብይት ላይ ያለው ውጣ ውረድ ከፍተኛና ገዥዎች የማይተማመኑበት ደረጃ ላይ እየደረሰ በመሆኑ፣ በዓለም አቀፍ ገበያ በጣዕሙ ተወዳዳሪ የማይገኝለት የኢትዮጵያ ቡና ዋጋ እያጣ መምጣቱ የሚያስቆጭ ወቅታዊ ጉዳይ ሆኗል፡፡ የችግሩ ምንጮች በዋነኛነት የመንግሥት የቡና ግብይት አቀንቃኞቹ የንግድ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ድርጅት እንደሆኑ የዘርፉ ተዋናዮች ያምናሉ፡፡ 
የቡና ግብይት ተዋናዮች እንደሚሉት፣ የችግሩ ምንጮች በእነዚህ ሁለት መንግሥታዊ ተቋማት የተወለዱ ችግሮች ናቸው፡፡ በመጀመሪያ የንግድ ሚኒስቴር የቡና ግብይት ዘርፍ የሥራ ኃላፊዎች የቡና ግብይት ሁኔታን በሚገባ አለመረዳታቸው ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የሥራ ኃላፊዎች የግብይት ሁኔታውን ቢያውቁም፣ የመወሰን አቅም የሌላቸው በመሆኑ ነው፡፡ ‹‹እነዚህ አካላት ግን ያሉባቸውን የተወሰኑ ችግሮች ለማረም አልሞከሩም፤›› ይላሉ የተበሳጩት የቡና ግብይት ተዋናዮች፡፡ በምርት ገበያ በኩል አሉ ከሚባሉት ችግሮች መካከል አንዱ የቡና ልኬት (ሚዛን) ችግር ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ቀደም ባሉት ዓመታት በቡና ግዥ ሒደት የቡና ገለፋት በ20 በመቶ ታሳቢ ተደርጎ በግዥ ሒደት ቅናሽ ይደረግ ነበር፡፡ አሁን ባለው የምርት ገበያ የሽያጭ ሒደት ግን ቀድሞ የነበረው አሠራር እንዲቀር በመደረጉ፣ ቡና ከአቅራቢዎች ገዝተው የሚልኩ ኤክስፖርተሮች መቸገራቸውን ይገልጻሉ፡፡ 
በዘርፉ በተፈጠሩ ችግሮች ምክንያት በዚህ ዓመት ወደ ዓለም ገበያ መላክ ከነበረበት ቡና መካከል ከ150 ሺሕ ሜትሪክ ቶን በላይ ቡና በአገር ውስጥ ይገኛል፡፡ ከዚህ ቡና ውስጥ 60 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ቡና ነቀምት ከተማና ሲዳማ ዞን ውስጥ እንደሚገኝ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ 
የተጠናቀቀውን የሰኔ ወር ጨምሮ ወደ ውጭ የተላከው ቡና 170 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ሲሆን፣ ከዚህ ቡና የሚገኘው ገቢ 800 ሚሊዮን ዶላር እንደማይበልጥ ምንጮች ይገልጻሉ፡፡ የተላከው ቡና መላክ ከነበረበት ከማነሱም በላይ ለቡናው የሚሰጠው ዋጋም በዓለም ተወዳጅ ቡና ላላት አገር የማይመጥን ነው በማለት የሚከራከሩ በርካቶች ናቸው፡፡ ምክንያቱም ኬንያ 40 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ቡና ልካ ከ500 ሚሊዮን ዶላር በላይ ስታገኝ፣ ኢትዮጵያ 170 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ቡና ልካ ያገኘችው ከ800 ሚሊዮን ዶላር አይበልጥም ይላሉ፡፡ 
ይህ ሁኔታ ኢትዮጵያ በ2005 በጀት ዓመት ከቡና ዘርፍ ለማግኘት ያቀደችውን 1.3 ቢሊዮን ዶላር እንዳይሳካ ከማድረጉም በላይ፣ በቡና ዘርፍ ለሚተዳደሩት 21 ሚሊዮን ዜጐች ከፍተኛ ሥጋት ፈጥሯል፡፡ 
ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ከምትልካቸው የወጪ ንግድ ዕቃዎች ግንባር ቀደም ድርሻ የሚወስደው ቡና፣ በቶን አምስት ሺሕ ዶላር ይሸጥ ነበር፡፡ አሁን ባለው ገበያ ግን ከ2,400 እስከ 2,500 ዶላር እየተሸጠ ይገኛል፡፡ 
መንግሥት በበጀት ዓመቱ ይገኛል ብሎ ያቀደው ገቢ፣ በዋጋ መውረድ ምክንያት ብቻ ሳይሆን በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ ወራት በመንግሥት በኩል በቀረበ አዲስ የቡና አላላክ ሥርዓት ምክንያት ቀውስ ውስጥ ገብቶ ነበር፡፡ የቡና ዋጋ ቢወርድም ግን ከታቀደው የበለጠ ጭማሪ በመላክ ማካካስ ይቻል እንደነበር ነጋዴዎች ይናገራሉ፡፡
በሚቀጥለው የ2006 በጀት ዓመትም የቡና ዋጋ ወደነበረበት ላይመለስ እንደሚችል ሥጋታቸውን የሚገልጹ ቢኖሩም፣ መገመት ግን እንደሚያስቸግር የሚገልጹም አልታጡም፡፡ የሌሎች አገሮች የቡና ዋጋ ከኢትዮጵያ የተሻለ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ ቡና ጣዕም ከሌሎች የተሻለ ሆኖ በየጊዜው በዘርፉ በሚፈጠረው የአሠራር ሳንካዎች ምክንያት ዋጋውን እያጣ መምጣቱ እየተነገረ ነው፡፡
መንግሥት አገር ውስጥ ቡና የመላክ ፈቃድ ያላቸው ኩባንያዎችን በሙሉ በሚቀጥለው ዓመት ወደ ውጭ የሚልኩትን የቡና መጠን እንዲያሳውቁ ጥያቄ አቅርቧል፡፡ የንግድ ሚኒስቴር ከነጋዴዎቹ በሚሰበሰበው መረጃ ላይ ተመሥርቶ የራሱን ትንታኔ ከሠራ በኋላ በበጀት ዓመቱ የሚላከውን የቡና መጠንና የሚገኘውን ገቢ ያቅዳል፡፡ በዚህ መሠረት በዚህ ሳምንትና በሚቀጥለው ሳምንት የመጀመሪያዎቹ ቀናት የቡና ነጋዴዎች በዓመቱ ለመላክ የሚያቅዱትን የቡና መጠን እንደሚያሳውቁ ይጠበቃል፡፡ 
የእነዚህ ሁሉ ችግሮች ማዕከል የሆነው ንግድ ሚኒስቴር፣ በቡና ነጋዴዎች ማኅበር የቀረቡለትን ችግሮችና የመፍትሔ ሐሳቦች በእስካሁኑ ቆይታ ማስተናገድ አልቻለም፡፡ ምላሽ ባለመስጠቱም በርካታ የቡና ነጋዴዎች ተስፋ እየቆረጡ ከመመጣታቸውም በላይ ችግሩ ለቡና ኮንትሮባንድ በሰፊው በር መክፈቱን እየተናገሩ ነው፡፡
የዘርፉ ተዋናዮች መርካቶን ‹‹ደረቅ ወደብ›› የሚል ስያሜ የሰጡት ሲሆን፣ ቀደም ሲል ለውጭ ገበያ የሚቀርበው ቡና በመርካቶ ለአገር ውስጥ ገበያ በሰፊው ቀርቧል፡፡ ‹‹መርካቶ ላይ ያለው ቡና አውሮፓም ሆነ አሜሪካ የለም፤›› ሲሉ የቡና ነጋዴዎች የኤክስፖርት ቡና መርካቶ ላይ በሰፊው ለግብይት መቅረቡን ይገልጻሉ፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ቡና በኮንትሮባንድ ወደ ኬንያና ወደ ሱዳን እየተላከ በመሆኑ፣ የቡና መገኛና የቡና ጣዕም ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ በሒደት ከዓለም ገበያ ውስጥ እየወጣች እንደሆነ የዘርፉ ተዋናዮች እምነት ሆኗል፡፡
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ የምትታወቅበት ቡና ችግር ውስጥ በመግባቱ፣ ኢትዮጵያ ከዓለም የቡና ግብይት እንድትወጣ እየተጫናት መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡ መንግሥት ጣልቃ ገብቶ አንዳች ማሻሻያ ካላደረገ፣ ነጋዴዎች ከቡና ግብይት ውስጥ ሊወጡ እንደሚችሉም እየገለጹ ነው፡፡   

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር