ኮኤ ፉሺ ! . . . ሃኮ ፉሺ ! . . . “በሲዳማ ዞን አርቤጎና ውስጥ በአገር ሽማግሌዎች የተከወነ የፍትሃዊ ምርጫ ሂደት”

በሲዳማ ዞን አርቤጎና ውስጥ በአገር ሽማግሌዎች የተከወነ የፍትሃዊ ምርጫ ሂደት ተመክሮ እንካችሁ…
ምርጫው ሊካሄድ ሁሉም ነገር ተዘጋጅቷል… አስመራጮች… ታዛቢዎች… ጸጥታ አስከባሪዎች… ሽማግሌዎችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ቦታ ቦታቸውን ይዘዋል…. መራጩ ህዝብም የምርጫ ካርዱን እንደያዘ ተሰልፎ ይጠባበቃል… ምርጫው ይጭበረበራል፣ ኮሮጆው ሊቀየር ይችላል ብለው የሰጉት የአገር ሽማግሌዎች የራሳቸውን የፍትሃዊ ምርጫ መላ ዘይደዋል… ሁሉም ነገር መጠናቀቁን ሲያረጋግጡም ተነሱ…
ለጸጥታ አስከባሪዎችም አሏቸው: ”ቴኔ ኮሮጆ ሃዺ !” … በደምሳሳው ሲተረጎም ”ይህን ኮሮጆ ወዲያ አንሱት!”… ”ኮሮጆውን ውሰዱት!” እንደማለት ሊሆን ይችላል…
በመቀጠልም የለበሷቸውን ረጃጅም ቡሉኮዎች (ጋቢዎች) ለሁሉም ግልጽ በሆነ መሃል ቦታ ላይ አነጠፏቸው… ለፍትህና ለሃቅ ቆሙ… ለመራጩ ህዝብም አሉት…
”ኮኤ ፉሺ !…”
”ሃኮ ፉሺ !…”
በግርድፉ ሲተረጎምም :
” እዚህ አድርግ! … እዚችው ጣል !” 
” እዚህ አስቀምጥ! … እዚችው ቁጭ አድርግ !” … እንደማለት ሊሆን ይችላል …
ሕዝቡ በሽማግሌዎቹ እምነት አለውና አላንገራገረም!… የፓርቲዎች አርማ ያለበትን ወረቀት ወስዶ… ሚስጥራዊ ክፍሏ ውስጥ ገብቶ… የሚመርጠው ምልክት ላይ የ X ምልክቱን አኑሮ… ወረቀቱን እያጣጠፈ ወደ ውጭ ይወጣል… ወደ ተዘረጋው ቡልኮ ላይ ሁሉም እያዩት ወርውሮ ይሄዳል… ሽማግሌዎቹም በንቃት ይጠባበቃሉ… ድንገት የሚያንገራግር… ከሂደቱ የሚያፈነግጥ ሲገኝም ሽማግሌዎቹ ይገስጹታል…
”ኮኤ ፉሺ !…”
”ሃኮ ፉሺ !…” … ይሉታል… ”እዚህ አድርግ! … እዚችው ጣል!” … ወይ ፍንክች!… እያሉ ይመልሱታል…
እንዲሁ ቀኑን ሙሉ ”ኮኤ ፉሺ !… ”ሃኮ ፉሺ !…” እንዳሉ ይውሉና ምርጫው ይጠናቀቃል… የድምጽ ቆጠራውም በሽማግሌዎቹ ዳኝነት ይከወናል… ኮሮጆ የሚባል ነገር ለምርጫው ቅንጣት አስተዋጽኦ ሳያደርግ ይውላል… ለማጭበርበር የተዘጋጁ ኮሮጆዎች ከነበሩም ውሃ በላቸው… በውጤቱም ባለ ዶሮ ምልክቱ የተቃዋሚ ፓርቲ ሲአን (ሲዳማ አርነት ንቅናቄ) አሸነፈ… ባለ ንብ ምልክቱ ተፎካካሪም ሽንፈቱን አምኖ ተቀበለ… ምንም መፈናፈኛ የለማ!…
መራጩ ሕዝብም አለ:
”ቢኒቾ ኢሽ !…”
”ሉኪቾ ሊሽ !…”
ሲተረጎምም…
”ንቧን ወደዚያ !…
ዶሮዋን ወደዚህ !…
እንደማለት ይሆናል… ንብ በሲዳምኛ ቢኒቾ ሲሆን ዶሮ ደግሞ ሉኪቾ ነው… ቋንቋውን በደንብ የምታውቁ ትርጓሜውን ብታርሙኝ ደስታዬ ነው …
”ኮኤ ፉሺ !…”
”ሃኮ ፉሺ !…” የሚሉ ሃቀኛ ዳኞች አያሳጣን አቦ!…
ሽማግሌዎቻችንን እድሜያቸውን ያርዝምልን !!!
”ቢኒቾ ኢሽ !…”
”ሉኪቾ ሊሽ !…”
በሰላም የተሞላ የሳምንት መጨረሻ ይሁንላችሁ!
አብዲ ሰዒድ

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር