የአውሮፓ ኅብረት የፓርላማ ቡድን በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት አሳሳቢ ነው አለ

-    የቃሊቲን እስር ቤት እንዳይጎበኝ መከልከሉን ገለጸ 

ለሦስት ቀናት በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደረገው የአውሮፓ ኅብረት ፓርላማ የሰብዓዊ መብቶች ንዑስ ኮሚቴ በአገሪቱ ውስጥ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት አሳሳቢ ደረጃ መድረሱን አስታወቀ፡፡ ጋዜጠኞችና የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት በአስቸኳይ እንደፈቱም ጠይቋል፡፡
ከሐምሌ 8 እስከ 10 ቀን 2005 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደረገው የአውሮፓ ኅብረት የልዑካን ቡድን፣ በኢትዮጵያ የነበረውን ጉብኝት ካጠናቀቀ በኋላ ሰሞኑን በሒልተን ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነበር ይህንን የገለጸው፡፡ 

እንደ ቡድኑ ድምዳሜ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና ዕንባ ጠባቂ ተቋም መቋቋማቸውና በቅርቡ የፀደቀው አገራዊ የሰብዓዊ መብት መርሐ ግብር የሚበረታታ ዕርምጃ መሆኑን ገልጾ፣ መንግሥት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየፈጸመ መሆኑን አስረድቷል፡፡ 

ከመንግሥትና ከተቃዋሚ ተወካዮች እንዲሁም ከሲቪል ማኅበረሰብ አካላት ጋር ሰፋ ያለ ምክክርና ውይይት ያደረገው ቡድኑ፣ በአገሪቱ ዲሞክራሲ ማበብ ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ ተብሎ የሚተመንባቸው ነፃ ሚዲያና ሲቪክ ማኅበረሰባት በከፍተኛ ደረጃ እንዳይሠሩ የተደረጉ መሆናቸውን ገልጿል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ፀረ ሽብረተኝነት አዋጁን ጨምሮ የአገሪቱን የፖለቲካ ድባብ አፍነው ይዘውታል ያሉዋቸው ሕጎች እንዲከለሱ ቡድኑ መንግሥትን ጠይቋል፡፡ ለዚህም በእስር ላይ የሚገኙት የተቃዋሚ ፓርቲዎች አባላትና ጋዜጠኞች ሐሳባቸውን በነፃነት የመግለጽ መብታቸውን በመጠቀማቸው ለእስር የተዳረጉ መሆናቸውን በመግለጽ፣ በአስቸኳይ እንዲፈቱ መንግሥትን ጠይቋል፡፡

እስረኞችን በመጎብኘት የመጀመርያ መረጃ ለማግኘት አቅዶ እንደነበረ ያስታወቀው ቡድኑ፣ ቃሊቲ እስር ቤትን እንዳይጎበኝና እስረኞችን እንዳያነጋግር በመንግሥት በመከልከሉ ከፍተኛ ቅሬታ እንዳደረበት አስታውቋል፡፡ መንግሥት የእስረኞች አያያዝን እንዲያሻሽል ጠይቋል፡፡ በ2007 ዓ.ም. ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀውን አምስተኛውን አገር አቀፍ ምርጫ፣ መንግሥት ለዲሞክራሲያዊ መርሆች ያለውን ቁርጠኝነት ለማረጋገጥ እንደ አንድ ትልቅ አጋጣሚ እንዲጠቀምበት የመከረ ሲሆን፣ ከዚህ በፊት ምርጫዎች ሲከናወኑ የገጠሙ እክሎችንም ለማስተካከል ከወዲሁ እንዲሠራ ጠይቋል፡፡ 

ቡድኑ ከአፍሪካ ኅብረት አካላት ጋር ባደረገው ምክክር ኅብረቱ ሰላምንና ፀጥታን በማረጋገጥ ረገድ ያደረገው ጥረት ያደነቀ ሲሆን፣ አባል አገሮች ለፈረሙዋቸው የሰብዓዊ መብት ሰነዶች ተግባራዊነት ምን ያህል ቁርጠኛ መሆናቸውን መከታተል እንዳለበት አስገንዝቧል፡፡ ኅብረቱ በቅርቡ ለኬንያ መሪዎች በተቆረጠው የክስ ዋራንት ምክንያት ከዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት ጋር ቅራኔ ውስጥ መግባቱ የሚታወስ ሲሆን፣ ቡድኑ ኅብረቱ ከፍርድ ቤቱ ጋር በትብብር እንዲሠራ ጥያቄ አቅርቧል፡፡ 

የአውሮፓ ኅብረት ቀደም ሲል የኢትዮጵያ መንግሥትን በምርጫና በሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ ግንባር ቀደም ወቃሽ የነበረ ቢሆንም፣ ለተወሰነ ጊዜ መግለጫ ከማውጣትና አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቦ እንደነበር ይታወሳል፡፡  

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር