ሕዝብ ‹‹ችግር ፈቺ አካልን ያየህ ወዲህ በለኝ›› እያለ ነው!

በተደጋጋሚ እንደምንገልጸው በአሁኑ ጊዜ መንግሥት የሙስና ወንጀልን ለመከላከልና ሙሰኞችን ለመቅጣት አዎንታዊ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው፡፡ መቋጫው ለፍርድ ቤት የሚተው ቢሆንም ጅምሩ የሚያበረታታ ነው፡፡
ብቃት የላቸውም፣ ሌላ ሥራ ቢሠሩ ወይም ሌላ ኃላፊነት ቢሰጣቸው ይሻላል ተብለው የሚነሱትንና የሚዛወሩትንም እያስተዋልን ነን፡፡ እንቅስቃሴው የሚመዘነው በውጤቱ ቢሆንም ደፈርና ፈጠን ብሎ ዕርምጃ ለመውሰድ መራመዱ ራሱ በአዎንታ የሚታይ ነው፡፡ 

ይህንን የመንግሥት እንቅስቃሴ በትኩረት እየተከታተለ ያለው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ከእንቅስቃሴው ጋር በተያያዘ ለመንግሥት አንድ ግልጽና ግልጽ የሆነ ጥያቄ እየቀረበ ነው፡፡ ‹‹እነዚህ ሙሰኞች፣ ወንጀለኞች፣ ብቃት የለሽ ሹሞች በሥልጣን ላይ በነበሩበት ጊዜ የፈጸሙብኝ በደል መፍትሔ ያገኛል ወይ?›› የሚል ግልጽ ጥያቄ ነወ፡፡

ሙሰኞችም፣ አቅመ ቢሶችም፣ አስመሳዮችም፣ ፀረ ሕዝቦችም ሌሎች ሌሎች ወንጀለኞችም ሥራቸውን በሚገባ አልሠሩም ሲባል ትርጉሙ ግልጽ ነው፡፡ ሕግ ጥሰዋል፣ የሕዝብ ጥያቄ አልመለሱም፣ የሕዝብ ቅሬታ አልተቀበሉም፣ በሕዝብ የተሰጣቸውን ኃላፊነት አልተወጡም ማለት ነው፡፡ ይህ ማለትም በእነሱ ምክንያት ሕዝብ በደል ደርሶበታል ማለት ነው፡፡ 

በመሆኑም እነሱ ከሥልጣናቸው ሲነሱ፣ ሲታሰሩና ሲጠየቁ ለመሆኑ የፈጸሙት ምንድነው? ያደረሱት በደል ምንና ምን ያህል ነው ተብሎ ይመረመራል? የፈጠሩትን ችግር የሚፈታ ዕርምጃ ይወሰዳል? ወይስ እነሱ ይነሳሉ፣ በደልም ይረሳል፣ ሰሚ እንዳጣ ይቀጥላል ማለት ነው?

መንግሥት እየወሰደው ካለው ዕርምጃ ጎን ለጎን ‹‹ችግር ፈቺ አካል›› ማቋቋም አለበት፡፡ ችግርና አቤቱታ እየመረመረ መፍትሔ የሚሰጥ ቡድን ወይም አካል ሊያቋቋም ይገባል፡፡ አለበለዚያ ‹‹ጉልቻ ቢቀያየር ወጥ አያጣፍጥም›› እያለ ሕዝብ ተስፋ ሊቆርጥ ነው፡፡

ሁሉም አቤቱታ ትክክል ነው ሁሉም አቤት ባይ ሀቀኛ ነው እያልን አይደለም፡፡ ጥፋተኛ አቤት ባይና አመልካችም ሊኖር ይችላል፡፡ ነገር ግን በእርግጥ የተበደለና ፍትሕ ያጣ ዜጋም በየቀኑና በየቦታው አቤት እያለ ሰሚ አጥቷል፡፡ እንኳን መፍትሔ ሊሰጡ የዜጋን አቤቱታና ማመልከቻ ለማንበብ ደንታውም ፍላጎቱም የሌላቸው አሉ፡፡ ለውሳኔና ለፊርማ የተዘጋጁ ደብዳቤዎች ጠረጴዛቸው ላይ ተቀምጠውላቸው ሳያነቡና ሳይፈጽሙ የሚቀልዱ ሞልተዋል፡፡ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ፋይሎች ጠረጴዛቸው ላይ እንደተቀመጡ ሳይወስኑባቸው ወደ ሌላ ሹመት የተዛወሩም አሉ፡፡
ስለዚህ ጥያቄው አሁንስ የሕዝብ አቤቱታ ይደመጣል ወይ? አሁንስ የሕዝብ እንባ ይታበሳል ወይ? አሁንስ ፍትሕ ያጣ ፍትሕ ያገኛል ወይ? አሁንስ መብቱ የተረገጠ ዜጋ መብቱ ይከበርለታል ወይ? አሁንስ የተጣሰና የተረገጠ ሕግ ይከበራል ወይ?

የመንግሥት ቀጣይ እንቅስቃሴ የሚመዘነው በዚህ ይሆናል፡፡ ወንጀለኛ ሲነሳ ወንጀል የተፈጸመበት ዜጋ ፍትሕ ያገኛል ወይ? ለሚለው ጥያቄ በሚሰጠው ምላሽ መንግሥት ይመዘናል፡፡ 

በሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለው በደል መታየትና መፈታት ያለበት ግን አጥፊው ከቦታውና ከሥልጣኑ ላይ ሲነሳ ብቻ መሆን የለበትም፡፡ በሥልጣኑ ላይ እያለም ሥራውን በተገቢው መንገድ እያከናወነ መሆኑን የሚከታተልና የሚቆጣጠር አካል መኖር አለበት፡፡ የበላይ አካልም፣ ሕጋዊ አካልም፣ ተቆጣጣሪ አካልም፡፡ 

በብዙ መሥሪያ ቤቶች ቀልድ በዝቷል፡፡ ቢሮ የማይገቡ ባለሥልጣናት ሞልተዋል፡፡ ገብተውም ፋይል የማያዩና የማይፈርሙ ባለሥልጣናት አሉ፡፡ በአስመሳይነት ሰርስረው ገብተው መንግሥትና ሕዝብን አጋጭተው መንግሥትን ለመጣል የሚሯሯጡ አሉ፡፡ የራዕይ፣ የህዳሴ፣ የሌጋሲና የዓባይ ግድብ መፈክርን እያሰሙ በውስጣቸው ግን እነዚህን ለማፍረስ ያዙኝ ልቀቁኝ የሚሉ አሉ፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ሕዝብ ችግሩን የሚፈታለት ያጣል፡፡ ብሶት ይበራከታል፡፡ 

በእንደዚህ ዓይነት አካሄድ መንግሥት መቀጠል የለበትም፡፡ እንደጀመረው ደፈርና ጠንከር ብሎ ለሕዝብ አቤቱታዎች ምላሽ ለመስጠት ቀንና ሌሊት ሊሯሯጥ ይገባል፡፡ አገርንና ሕዝብን በእጅጉ እየጎዳ ነውና፡፡ 

በመሬት ይዞታ ኃላፊዎች በደል ደረሰብን ብለው ብዙ ሰዎች ያለቅሳሉ፡፡ በመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ ኃላፊዎች መብታችን ተገፈፈ ብለው ብዙ ኢትዮጵያዊያን አቤት ይላሉ፡፡ በወረዳ፣ በክፍለ ከተማና በአስተዳደሩ ንብረቴ ፈረሰ፣ ተነጠቅኩ፣ ታገደብኝ ብሎ የሚያነባው ብዙ ነው፡፡ ለእኔ የተሰጠ የማዕድን ቦታ ለሌላ ተሰጠ ብለው ኡኡ የሚሉ የውጭ ኢንቨስተሮችም ብዙ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት ማድረግ አስቸጋሪ ነው የሚል አቤቱታ በውጭ ኢንቨስተሮች እየተደመጠ ነው፡፡

 በአገራችን ኢንቨስት ለማድረግ ብለን መጥተን አልተስተናገድንም፣ ለኪሳራ ተዳረግን የሚሉ ዳያስፖራ ኢትዮጵያዊያን ብዙ ናቸው፡፡ በትራንስፎርመር ተከላ አለመካሄድ ምክንያት ፋብሪካዎች ሥራ መጀመር አልቻለም የሚሉ ባለሀብቶች ብዙ ናቸው፡፡ በኤሌክትሪክ መቆራረጥ ማሽኖቻችን ተቃጠሉ፣ ጋዩ የሚሉ ባለሀብቶች ብዙ ናቸው፡፡ መንግሥት ውላችንን አፈረሰ ብለው የሚያዝኑ በርካታ ናቸው፡፡ 

ይህ ሁሉ ተደማምሮ የኢትዮጵያውያንን መንፈስና እምነት እየነካና እየጎዳ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ችግር ኢንቨስትመንትን እያደናቀፈ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ችግር ሕዝብ በሕገ መንግሥቱ እንዳይተማመን እያደረገ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ተደማምሮ ዋስትናዬና ከለላዬ ምንድነው? የሚል ጭንቀትና ተስፋ መቁረጥ እያስከተለ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ተደማምሮ ሥራ ላቁም፣ ወደ ውጭ ልመለስ የሚል አስተሳሰብ እያስከተለ ነው፡፡ 

ይህንን ሁሉ ነው እያሳሰበን ያለው፡፡ ሕዝብ በአገሩ እንዲኮራ፣ ሕዝብ አገሩን እንዲያለማ፣ ሕዝብ በሕገ መንግሥቱ፣ በሕጉና በመንግሥቱ እንዲተማመንና እንዲኮራ መንግሥት የሕዝብ አቤቱታን የሚያዳምጥ፣ የሚከታተል፣ የሚመረምርና የሚፈታ አሠራርና መዋቅር ይፍጠር፡፡  በአስቸኳይ፡፡

ሕዝብ ‹‹ችግር ፈቺ አካልን ያየህ ወዲህ በለኝ›› እያለና እየተማፀነ ነውና፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር