በሀዋሳ ከተማ ዘንድሮ ከ33 ሺህ በላይ ወጣቶችና ሴቶች የስራ ዕድል ተጠቃሚ ሆኑ

አዋሳ ሰኔ 24/2005 በሀዋሳ ከተማ በዘንድሮ የበጀት አመት ከ33 ሺህ በላይ ወጣቶችና ሴቶች የቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል ተጠቃሚ መሆናቸውን የከተማ አስተዳደር ንግድና ኢንዱስትሪ መምሪያ አስታወቀ፡፡ በመምሪያው የኢንተርፕራይዞች ልማት ድጋፍ ማዕቀፍ አፈጻጸምና ክትትል ዋና የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ኤፍሬም አለማየሁ ሰሞኑን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት ወጣቶችና ሴቶች የሥራ እድል ተጠቃሚ የሆኑት በማኒፋክቸሪንግ፣ በኮንስትራክሽን ፣ በከተማ ግብርና፣ በአገልግሎትና በንግድ ስራ ዘርፎች ተደራጅተው በተደረገላቸው ሁለገብ ድጋፍ ነው፡፡ ከተጠቃሚዎች መካከል 11ሺህ 612 ሴቶች መሆናቸውን አስተባባሪው ገልፀዋል፡፡ የሥራ እድል ተጠቃሚ የሆኑት እነዚሁ ወጣቶችና ሴቶች ከ17 ሚሊዮን 500 ሺህ ብር በላይ እንዲቆጥቡ መደረጉንም አመልክተዋል፡፡ በመምሪያው የኢንተርፕራይዞች ልማት ዋና የስራ ሂደት አሰተባባሪ አቶ ውቤ ቤላሞ በበኩላቸው ከ18 ሺህ 600 ለሚበልጡ አንቀሳቃሾች የንግድ ስራ አመራር፣ የቴክኒክ ሙያ ፣ የምክር አገልገሎት፣ የተስማሚ ቴክኖሎጂ መሳሪያዎች ድጋፍ መሰጠቱን ጠቁመው ከስድስት ሚሊዮን ብር በላይ የብድር ገንዘብ በመከፋፈል እንዲጠናከሩ መደረጉን ገልጸዋል፡፡ ለሌሎች 7 ሺህ 772 አንቀሳቃሾች ደግሞ ከ186 ሚሊዮን ብር በላይ የገበያ ትስሰርና ገቢ እንዲያገኙ መደረጉን በመምሪያ የማምረቻ ማዕከላት ግንባታ ማስተዳደርና የገበያ ልማት ዋና የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ አለማየሁ አብርሀም አስረድተዋል፡፡ የተፈጠረው የገበያ ትስሰርና ገቢውን ያገኙት ምርትና አገልግሎታቸውን የሚያስተዋውቁበትና የሚሸጡበት ባዛርና አውደርኢ በማዘጋጀት፣ በኮብል ስቶንና በሌሎችም የግንባታ ስራዎች ቅድሚያ ዕድል እንዲያገኙ በመደረጉ ነው ብለዋል፡፡ በተጨማሪም 18 ሺህ 526 ካሬ ሜትር የመሸጫና የመስሪያ ቦታ የተመቻቸላቸው ከመሆኑም በላይ ቀደም ብሎ በከተማው የተለያዩ አካባቢዎች ከ51 ሚሊዮን ብር በላይ ከተገነቡ 41 ዘመናዊ የመሸጫና የማምረቻ ማዕከላት መካከል 21ዱ መብራት፣ ውሃና ሌሎችም መሰረተ ልማት ተሟልቶላቸው ለአገልግሎት መብቃታቸውን አስታውቀዋል፡፡ በአጠቃላይ በበጀት አመቱ ውስጥ በከተማው ከ33 ሺህ በላይ ወጣቶችና ሴቶች የቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል ተጠቃሚ በመሆን ኑሯቸውን በማሻሻል ላይ እንደሚገኙ አስተባባሪዎቹ አመልክተዋል፡፡ ከተጠቃሚዎች መካከል ወጣት ታምራት ሀይለማሪያምና ሊዲያ አያሌው በሰጡት አስተያየት ከከተማው አስተዳደር ባገኙት የብድር ገንዘብ፣ የገበያ ትስስርና የመስሪያ ቦታ ድጋፍ ከሌሎች ጓደኞቻቸው ጋር ተደራጅተው በቆዳ ውጤቶች ማምረትና ሽያጭ ላይ ተሰማርተው በመንቀሳቀስ ውጤታማ መሆናቸው ገልጸዋል፡፡ በከተሞች ድህነትና ስራ አጥነትን ለመቀነስ መንግስት በዘረጋው የጥቃቅና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ፕሮግራም ቀደም ባሉት አመታት በሀዋሳ ከተማ ስራ አጥ የነበሩ ሌሎች በርካታ ወጣቶችና ሴቶች በተመሳሳይ ተጠቃሚ በመሆን ከፍተኛ ንብረትና ሀብት በማፍራት ለተሻለ ህይወት መብቃታቸውን የስራ ሂደቶቹ አስተባባሪዎች ተናግረዋል፡፡
http://www.ena.gov.et/Story.aspx?ID=9052&K=1

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር