በሃዋሳ ከተማ ከ11 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የትራፊክ ኮምፕሌክስ ህንፃ እየተገነባ ነው

ሃዋሳ ሐምሌ 2/2005 በደቡብ ክልል ሃዋሳ ከተማ ከ11 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የአሽክርካሪ ብቃት ምዘና የሚደረግበት ዘመናዊ የትራፊክ ኮምፕሌክስ ህንፃ ግንባታ ከ85 በመቶ በላይ መጠናቀቁን የክልሉ ትራንስፖርት ቢሮ ገለጸ፡፡ በአርባምንጭ፣ በሆሳዕናና በሚዛን አማን ከተሞች ከ30 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ ተጨማሪ የትራፊክ ኮምፕሌክስ ግንባታ ለማካሄድ አሰፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁም ተገልጿል፡፡ በቢሮ የአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ዋና የስራ ሂደት አስተባበሪ አቶ ውቤ ለሳ ሰሞኑን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት የክልሉ መንግስት በመደበው ወጪ የተጀመረው የተቋሙ ግንባታ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ ግንባታው ከሶስት ወር በኋላ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ አገልግሎት ይሰጣል ብለዋል፡፡ በክልሉ በየጊዜው የሚከሰተው የትራፊክ አደጋ በአብዛኛው የአሽክርካሪዎች ብቃት ማነስ ነው ያሉት አስተባባሪው ይህንና የቀድሞውን የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ችግር በመቅረፍ ቀልጣፋ የአሽከርካሪዎች ምዘናን የሚያረጋግጥ ግልፅና ውጤታማ አሰራር ለመዘርጋት እንደሚያስችል የስራ ሂደቱ ባለቤት ተናግረዋል፡፡ በሃዋሳ ከተማ እየተገነባ የሚገኘው የአሽከርካሪዎች ምዘና የትራፊክ ኮምፕሌክስ ተቋም በኮምፒውተር መረጃ ኔትወርክ የተገናኙ የመቆጣጠሪያ መሳሪያዎችና ዘመናዊና አዲስ የመፈተሻ ቴክኖሎጂ ይገኙበታል ብለዋል፡፡ አሰራሩን በክልሉ ሁሉም አከባቢዎች ተደራሽ ለማድረግ የክልሉ መንግስት በመደበው 30 ሚሊዮን ብር በአርባምንጭ፣ በሆሳዕናና በሚዛን አማን ከተሞች የአሽከርካሪ ብቃት ምዘና የሚደረግባቸው ዘመናዊ የትራፊክ ኮምፕሌክስ ግንባታ ለማስጀመር ዝግጅቱ መጠናቀቁንና በሁለቱ ከተሞች ከያዝነው ወር ጀምሮ ስራው መጀመሩን ጠቁመዋል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር