መንግሥት ሕዝቡ ለአገሩ ዘብ እንዲቆም ጥሪ አቀረበ

የግብፅ ፖለቲከኞች ከአፍራሽ ድርጊታቸው ይቆጠቡ ብሏል
የግብፅ ፕሬዚዳንት፣ ጠቅላይ ሚኒስትርና ሌሎች የአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተገኙበት ባለፈው ሰኞ በተካሄደው ብሔራዊ የናይል ኮንፈረንስ ላይ ታላቁን የህዳሴ ግድብ በተመለከተ በተንፀባረቀው አፍራሽ መልዕክት የተበሳጨው የኢትዮጵያ መንግሥት፣ “ሕዝቡ ለአገሩ ዘብ እንዲቆም” ሲል ጥሪ አቀረበ፡፡ የግብፅ ፖለቲከኞችም ከአፍራሽ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስቧል፡፡

የግብፅ ፕሬዚዳንት መሐመድ ሙርሲ፣ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ሚኒስትሮችና የፀጥታ ባለሥልጣናት በተገኙበት በተካሄደው በዚሁ ስብሰባ፣ “የህዳሴ ግድቡ በግብፅ ላይ አደጋ በመደቀኑ በኢትዮጵያ ላይ በተለያዩ መንገዶች ተፅዕኖ በመፍጠር የግድቡን ሥራ ለማስቆም እንቅስቃሴ እናደርጋለን፤” በማለታቸው የኢትዮጵያ መንግሥት “አፍራሽ ድርጊት” በማለት አጣጥሎታል፡፡ 
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፣ ማክሰኞ አመሻሽ ላይ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ነበር የመንግሥትን አቋም ግልጽ ያደረጉት፡፡ “በህዳሴው ግድብ ሽፋን የውስጥ ችግርን ለማቃለል የሚደረገው ጥረት የግብፅን ዘላቂ ጥቅም አያስጠብቅም፤” ያሉት አምባሳደር ዲና፣ “ጦርነቶችና ሌሎች አፍራሽ ድርጊቶች ያረጁና ያፈጁ የ21ኛው ክፍለ ዘመን አስተሳሰብ የማይሸከማቸው ጤናማ ያልሆኑ አስተሳሰቦች ናቸው፤” በማለት የግብፅ ባለሥልጣናትን ድርጊት አጣጥለውታል፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ ቀረርቶ ተደናግጣ ግንባታውን ለአንዲት ሰከንድም ቢሆን እንደማታቆም አረጋግጠዋል፡፡ “የግብፅ ወገኖችም ከዚህ አፍራሽ ድርጊት እንዲቆጠቡ፤” ሲሉ አሳስበዋል፡፡ 
“የኢትዮጵያ መንግሥት የግብፅ መንግሥት እየያዘው ባለው መንገድ የዲፕሎማሲ ሥራ እየሠራ ነው ወይ?” በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ መንግሥት አስፈላጊውን ክትትል በማድረግ ላይ መሆኑን ገልጸው፣ እንደነሱ በስሜት የመልስ መልስ መስጠቱ ግን አስፈላጊ ሆኖ አልተገኘም ብለዋል፡፡ 
እንደ እሳቸው አባባል፣ የግብፅ ተቃዋሚዎችና ባለሥልጣናት ያንፀባረቁት ሐሳብ የመንግሥት አቋም ስለመሆኑ በኢትዮጵያ የሚገኙትን የግብፅ አምባሳደር ማብራርያ እንዲሰጡ የጠየቀ መሆኑን፣ ጉዳዩን አጀንዳ ለማድረግ እየተሯሯጡ ያሉት ጥቂት ፖለቲከኞች መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡ 
የውኃ ኤክስፐርቶች ቡድን የግድቡ ሪፖርት ይፋ ከተደረገ በኋላ የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ግንዛቤ እንዲያገኙ መደረጉን፣ እስካሁን የዓረብ አገሮች አምባሳደሮች ቡድንና የቡድን ስምንት የበለፀጉ አገሮች በጉዳዩ ላይ ማብራርያ እንዲያገኙ መደረጉን አስረድተዋል፡፡ 
የዓባይ ግድብን ግንባታ ለማካሄድ የተደረገው የወንዙን የፍሰት አቅጣጫ የመለወጥ ሥራ ምንም አዲስ ነገር እንደሌለውና የግንባታው አንድ አካል መሆኑን የተናገሩት አምባሳደር ዲና፣ የግብፅ ባለሥልጣናት የወቅቱ ድርጊት ግን የግብፅ ሕዝብን የትኩረት አቅጣጫ ለማስቀየስ እንደሆነ አስምረውበታል፡፡ 
ያም ሆኖ ግን፣ “የኢትዮጵያ ሕዝብ ለአገሩ ዘብ መቆም አለበት” ያሉ ሲሆን፣ የሚዲያ ሰዎች ይህንን ግንዛቤ በመፍጠር ሚናቸውን እንዲጫወቱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትን ዝግጅት አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱም፣ አስፈላጊ የሚባሉት የደኅንነትና የዲፕሎማሲ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ 
ካይሮ ላይ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የሠልፍ እንቅስቃሴ ስለመደረጉ በተመለከተው “ከ30 እና 40 የሚያንሱ ናቸው፡፡ እንዲያውም የፀጥታ ኃይሎች ቁጥር ይበዛል፤” ሲሉ የሕዝቡ ጉዳይ አይደለም በማለት አጣጥለውታል፡፡ በሰሞኑ ጉዳይ ከግብፅ ጋር ትብብር ለማድረግ ያልፈለገችውን የሱዳን አቋምን ያደነቁት አምባሳደር ዲና፣ ግብፆችም ከእነሱ መማር አለባቸው ብለዋል፡፡ 

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር