ኢኮኖሚውን ወደ አንድ ትሪሊዮን ብር የሚያሳድገው በጀት ለፓርላማ ቀረበ

-ሚኒስትር ሱፊያን ለመጀመርያ ጊዜ ጠንካራ ቁጥጥር ገጠማቸው
-ለመንገድ 29.1 ቢሊዮን ብር ለመከላከያ 7.5 ቢሊዮን ብር ተይዟል
የኢትዮጵያን አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) ወደ አንድ ትሪሊዮን ብር የሚያደርሰው የ2006 ዓ.ም. ረቂቅ በጀት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ፡፡ በጀቱን ያቀረቡት የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር አቶ ሱፊያን አህመድ ከፓርላማው ጠንካራ ቁጥጥር ገጥሟቸዋል፡፡ 

ሚኒስትሩ የአገሪቱን የዓምናና የዘንድሮ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ጥሩና በአስደሳች ሁኔታ ውስጥ መሆኑን፣ እንዲሁም ያሉበትን ፈታኝ ችግሮች በቅድሚያ በመዳሰስ ያለውን በጎ ኢኮኖሚያዊ ሒደት ለማጠናከርና ችግሮችን ለመቅረፍ ለተወጠኑ ግቦች ይረዳል ያሉትን የ2006 ዓ.ም. ረቂቅ በጀት አቅርበዋል፡፡ 
በዚህም መሠረት የአገሪቱ የቀጣይ ዓመት በጀት 154 ቢሊዮን 903 ሚሊዮን ብር እንደሚሆን ከዚህ ውስጥም 32.53 ቢሊዮን ብር ለመደበኛ ወጪ፣ 64.32 ቢሊዮን ብር ለካፒታል ፕሮጀክቶች፣ 43.05 ቢሊዮን ብሩ ለክልል መንግሥታት ድጎማ፣ እንዲሁም ቀሪው 15 ቢሊዮን ብር ለምዕተ ዓመቱ ግቦች ማጠናከሪያ ወጪዎች መሸፈኛ እንደሚውል አብራርተዋል፡፡ 
የተጠቀሰው የቀጣይ ዓመት ረቂቅ በጀት ከዘንድሮው ጋር ሲነፃፀር በ12.3 በመቶ ብልጫ ያለው ሲሆን፣ ከረቂቅ በጀቱ ውስጥ ከፍተኛውን የ41.5 በመቶ ድርሻ የያዘው የፌዴራል መንግሥት የካፒታል ፕሮጀክቶች ወጪ ነው፡፡ 
ለካፒታል ፕሮጀክቶች የተመደበው 64.32 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ቅድሚያ ትኩረት የተሰጣቸው ነባር ፕሮጀክቶች እንዲሆኑ የተወሰኑ አዳዲስ ፕሮጀክቶች ብቻ እንዲካተቱ በማድረግ፣ ከአገሪቱ የገንዘብ አቅም ጋር እንዲጣጣም መደረጉን ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡ 
የተጠቀሰው የካፒታል ፕሮጀክቶች በጀት ከዘንድሮው ዓመት በጀት ጋር ሲነፃፀር 18.1 በመቶ ጭማሪ ያሳየ ሲሆን፣ ከተያዘው ጠቅላላ የካፒታል በጀት ውስጥ 95.4 በመቶ የሚሆነው ትልቁ ድርሻ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ዘርፎች ለሚካሄዱ ፕሮጀክቶች ቅድሚያ የሰጠ መሆኑን ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡ 
ከፍተኛ ትኩረት ከተሰጣቸው የካፒታል ፕሮጀክቶች ውስጥ በቀዳሚነት የሚጠቀሰው የመንገድ ልማት ዘርፍ ነው፡፡ በመሆኑም ይህንን ዘርፍ ለሚመራው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን 29.07 ቢሊዮን ብር ተመድቧል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የትምህርት ዘርፍ ሲሆን፣ ለትምህርት ሚኒስቴር የካፒታልና መደበኛ ወጪዎች 22.5 ቢሊዮን ብር ተመድቧል፡፡ በሦስተኛ ደረጃ በረቂቅ በጀቱ ትኩረት ያገኘው መከላከያ ሚኒስቴር ሲሆን፣ 7.5 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ በጀት ተመድቦለታል፡፡ 
ለ2006 ዓ.ም. ከቀረበው አጠቃላይ በጀት ውስጥ 105.919 ቢሊዮን ብር ከአገር ውስጥ ምንጮች ይገኛል ተብሎ የሚታሰብ ሲሆን፣ ከዚሁ ውስጥ ከግብር ይሰበሰባል ተብሎ የታሰበው 100.3 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ታክስ ካልሆኑ ሌሎች የአገር ውስጥ ገቢዎች ደግሞ 5.587 ቢሊዮን ብር ይሰበሰባል ተብሎ ታቅዷል፡፡ 
ሌላው በጀቱ ታሳቢ ያደረገው 22.822 ቢሊዮን ብር የሚገኘው ከውጭ አገር ብድርና ዕርዳታ ሲሆን፣ ለመሠረታዊ አገልግሎቶች አሰጣጥ ከልማት አጋሮች ይገኛል ተብሎ የሚጠበቀው 9.5 ቢሊዮን ብርና ከዕዳ ስረዛ ይገኛል ተብሎ የሚጠበቀው 98 ሚሊዮን ብርም ለተረቀቀው በጀት የገቢ ምንጮች ናቸው፡፡ 
ከላይ እንደተጠቀሰው ለአጠቃላይ በጀቱ የገቢ ምንጮች የአገር ውስጥ የገቢ ምንጮች፣ የውጭ ብድርና ዕርዳታ እንዲሁም የዕዳ ቅነሳ ሲሆኑ፣ በአጠቃላይ 138.304 ቢሊዮን ብር የሚሆነውን የበጀቱን አካል ይሸፍናሉ፡፡ የተቀረው 16.6 ቢሊዮን ብር በበጀት ጉድለትነት የተያዘ ሲሆን፣ ይህንን የበጀት ጉድለት የዋጋ ንረትን በማያስከትል ሁኔታ ከአገር ውስጥ ብድር ለመሸፈን ታቅዷል፡፡ 
የአገሪቱ አጠቃላይ ምርት በ2006 ዓ.ም. መጨረሻ አንድ ትሪሊዮን ብር የሚደርስ በመሆኑ፣ የበጀት ጉድለቱ የጠቅላላ አገራዊ ምርቱ 1.6 በመቶ ብቻ ነው የሚሆነው፡፡ በመሆኑም በዋጋ ንረት ላይ ተፅዕኖ እንደማያሳድር ይታመናል ሲሉ አቶ ሱፊያን ገልጸዋል፡፡ 
የፌዴራል ዋና ኦዲተር ከወር በፊት ለፓርላማው ባቀረበው ሪፖርት አገሪቱ የምትመድበው በጀት ለምዝበራ የተጋለጠ መሆኑን፣ ባደረገው የናሙና ጥናት መሠረትም በ2004 በጀት ዓመት ሒሳብ ውስጥ 6.5 ቢሊዮን ብር ኦዲት ሊደረግ ባለመቻሉ ለምን እንደዋለ ማወቅ መቸገሩን መግለጹ ይታወሳል፡፡ 
ሚኒስትር ሱፊያን በበጀት መግለጫ ሪፖርታቸው ላይ ይህንን ጉዳይ በማንሳት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጉዳዩን የሚያጠና በአምስት ከፍተኛ ኃላፊዎች የሚመራ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየገመገመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሥራው ከተጠናቀቀና መወሰድ የሚገባቸው ዕርምጃዎች ከተለዩ በኋላ ጉዳዩን የተመለከተ ሪፖርት ለፓርላማው እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል፡፡ 
ከዚህ በኋላ ለውይይት መድረኩ የተከፈተ ሲሆን፣ ሚኒስትር ሱፊያን ከዚህ ቀደም አይተውት የማያውቁት የሚያሰኝ ጠንካራ ቁጥጥር ከፓርላማው ገጥሟቸዋል፡፡ 
የኦዲት ሪፖርቱ መንግሥት የሚበጅተው በጀት ለምዝበራ እየተጋለጠ መሆኑን በበቂ ማስረጃ አቅርቧል፡፡ በመሆኑም ዕርምጃ ለመውሰድ በቂ ማስረጃ አለ፡፡ ነገር ግን ዕርምጃ የመውሰድ ልፍስፍስነት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ላይ ይታያል በሚል በሚኒስትሩ ላይ ወቀሳ ተሰንዝሮባቸዋል፡፡ 
ወቀሳውን የሰነዘሩት የምክር ቤቱ የመንግሥት ወጪ አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ እሸቱ ተሾመ ናቸው፡፡ “እያንዳንዱ ተቋምና ግለሰብ ኃላፊ የነደፈውን ፕሮግራም ለማስፈጸም የወሰደውን ገንዘብ በአግባቡ ሥራ ላይ ማዋል እንዳለበት፣ ይህንን ካላደረገ በሕግ እንደሚጠየቅ ሕጉ ያስቀምጣል፡፡ ይህንን ተግባራዊ እያደረግን ነው የሚል እምነት የለኝም፤” ብለዋል አቶ እሸቱ፡፡ 
“ጂአይዜድ ተብሎ የሚጠራው ተቋም ይዟቸው የነበሩ የዩኒቨርሲቲ ግንባታ ፕሮጀክቶች አሁንም አላለቁም፡፡ የሚያልቁበት መንገድም አልተቀመጠም፡፡ የመማር ማስተማር ሒደቱ በዚህ ምክንያት እየተጎዳ ነው፡፡ የውኃ መጠጥ ፕሮጀክቶቻችንና ግድቦቻችን በተያዘላቸው ጊዜ አያልቁም፡፡ ከተመደበላቸው በጀት በላይም እየወሰዱ ነው፡፡ በጥራት እየተሠሩ አይደለም፤” ሲሉ አክለዋል፡፡ “ይህን እያየን በጀት እየመደብን መሄድ የለብንም፡፡ ወደ ዕርምጃ መግባትና አፈጻጸማችንን ማሳደግ ይኖርብናል፤” ሲሉ መክረዋል፡፡ 
“የዋና ኦዲተሩን ሪፖርት በተመለከተ አጣሪ ቡድን አቋቁመናል የተባለው ነገር የኦዲት ሪፖርቱን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ከሆነ ተገቢ ነው ብዬ አላስብም፡፡ ይህ ከሆነ በሕግ ነፃ መረጃ ለማቅረብ መብት የተሰጣቸው ተቋሞቻችንን እንዳንጋፋ እፈራለሁ፤” ሲሉ ተቃውሟቸውን ገልጸዋል፡፡ 
“መረጃ ለመሰብሰብ ከሆነም በቂ መረጃ በእጃችን አለ፡፡ ስለዚህ የቡድኑ ሥራ መታወቅና ጥንቃቄ መደረግ አለበት፤” ሲሉ አቶ እሸቱ አስረድተዋል፡፡ 
“የከሰም ተንዳሆ የስኳር ፕሮጀክት አሁንም በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር በጀት ተይዞለታል፡፡ ይኼ ፕሮጀክት መቼ ነው የሚያልቀው?” በማለት ረቂቅ በጀቱ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ አቶ እሸቱ በማስረጃ አስደግፈው ጠይቀዋል፡፡ 
“ክቡር ሚኒስትሩ ይህ ፕሮጀክት የፈጀውን ዓመት ብዛት ያውቃሉ፡፡ ይህ ምክር ቤት ግልጽ መረጃ ሊቀርብለት ይገባል፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ይህ ፕሮጀክት ከታቀደው በጀት እስከ 300 በመቶ በላይ ወስዷል፤” ሲሉ ተከራክረዋል፡፡ 
ሌሎች አባላትም በየዓመቱ ለተመሳሳይ ተግባር በጀት እየተያዘ መሆኑን በመጥቀስ ረቂቅ በጀቱን ለመሞገት ቢሞክሩም፣ በምክትል አፈ ጉባዔዋ ዕድል ተነፍገዋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በቀጣይ ፕሮግራም በዝርዝር ይታያል የሚል ነው፡፡ 
አንድ ሌላ የምክር ቤቱ አባል በበኩላቸው በዋና ኦዲተሩ ሪፖርት ላይ የተቋቋመው የሚኒስቴሩ አጣሪ የተባለው ኮሚቴ ለፓርላማው ሪፖርቱን ካላቀረበ ይህ በጀት ሊፀድቅ አይገባም ብለዋል፡፡ 
ሚኒስትር ሱፊያን የሰጡት ምላሽ ጠቅለል ያለ ሲሆን ምክር ቤቱ በዚህ ደረጃ መንቀሳቀሱን ግን ደግፈዋል፡፡ 
የተነሱት ችግሮች መኖራቸው እውነት መሆኑን ነገር ግን አብዛኛው በጀትና ፕሮጀክቶች በሕግና በአግባቡ እየዋሉ ናቸው፡፡ ፕሮጀክቶችም በጥራት እየተሠሩ ነው በማለት የተወሰኑ ሕፀፆች አጠቃላዩን ሥዕል እንዳያበላሹ መጠንቀቅ ተገቢ ነው ብለዋል፡፡ 
ረቂቅ በጀቱ እስከ ሰኔ ወር መጨረሻ ድረስ ውይይት ከተደረገበት በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በሚገኙበት የፓርላማው ጉባዔ የሚፀድቅ መሆኑን የምክር ቤቱ ሥነ ሥርዓት ደንብ ያስረዳል፡፡ 

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር