የሀዋሳ ዩኒቨርሰቲ ተማሪዎች ለታላቁ የህዳሴው ግድብ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገለጹ

አዋሳ ግንቦት 10/2005 የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ ለመገንባት የላቀ አስተዋጾኦ ያለውን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ስራን ለማፋጠን በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የሀዋሳ ዩኒቨርሰቲ ተማሪዎች ገለጹ፡፡ የዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች ህብረት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ለህዳሴው ግድብ ድጋፍ ለማሰባሰብ ላለፉት ስምንት ወራት ሲያደርግ የቆየውን ሀገራዊ የንቅናቄ ፕሮግራም አስመልክቶ ትናንት ማምሻውን የሎተሪ ማውጣት፣ የሽልማትና የኪነ ጥበብ ዝግጅቶችን አቅርቧል፡፡ የህብረቱ ፕሬዝዳንት ተማሪ ወንደወሰን እንዳለ እና የክለብ ኢኒሼቲቭ ተጠሪ ተማሪ ብሩክ በቀለ እንደገለጹት የግድቡ ግንባታ መሰረት ከተጣለበት ጊዜ አንስቶ የሀዋሳ ዩኒቨርሰቲ ሁሉም ተማሪዎች በእኔነት ስሜት በስራው ላይ የራሳቸውን አሻራ ለማሳረፍ ድጋፍ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ አስተባባሪ ኮሚቴዎችን አቋቋሙው በዋናው ግቢና በአምስቱም የዩኒቨርስቲው ካምፓሶች ለተማሪዎች ተደራሽ በመሆን ባደረጉ እንቅስቀሴ ከቀለባቸው በመቀነስና ከሎቶሪ ሽያጭ 200 ሺህ የሚጠጋ ብር አሰባስበዋል፡፡ በሀዋሳ ከተማና አካባቢው በሚገኙ ትምህርት ቤቶችና ኮሌጆች ተዘዋውረው በመቀሳቀስ ስለግድቡ አላማና ፋይዳ ያለውን ግንዛቤ የማስፋት ስራ ማከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡ እስከ ህዳሴው ግድብ ግንባታ ቦታ ድረስ በመሄድ ባዩት ስራ ከፍተኛ ኩራት እንደተሳማቸውንና በትምህርት ላይ እያሉም ሆነ ተመርቀው ከወጡ በኋላ ከገንዘብ ባሻገር በየሰለጠኑበት መስክ ለሀገራቸው ልማትና ፈጣን እድገት የበኩላቸው ለመወጣት ትልቅ መነሳሳት እንደፈጠረላቸው አስረደተዋል፡፡ ተማሪ ታደለ ቤዛና ተማሪ ፌቨን አብረሃም በበኩላቸው አባይ ወንዝ ላይ የሚገነባው የህዳሴው ግድብ የሁሉም ዜጋ ሀገራዊ ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ በራሳቸው በኩል የዩኒቨርስቲውን ተማሪዎችና ሌሎችን ማህበረስብ በማስተባበር ጭምር በጋራ እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸው ወደፊትም ማንም ቀስቃሽ ሳያስፈልጋቸው ለሀገሪቱ ልማት በሚበጀው ሁሉ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡ የሀገሪቱን መልካም ገጽታ ለመገንባታ የላቀ አስተዋጾኦ ያለውን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ስራን ለማፋጠን በሚደረገው ጥረት በገንዘብ ፣ በዕውቀትና በጉልበት ጭምር የበኩላቸውን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ዩኒቨርሰቲው ተማሪዎች ገልጸዋል፡፡ በክብር እንግድነት የተገኙት የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝድንት ዶክተር ዮሴፍ ማሞ በህዳሴው ግድብ ግንባታ ላይ የድርሻቸውን ለመወጣት ተማሪዎቹ ያለማንም ቀስቃሽ ከሁሉም ቀድመው በፍጹም ሀገራዊ የፍቅር ስሜት ያሳዩት ተነሳሽነትና የሰጡት ድጋፍ አርኣያነት ያለው የሚያኮራ ተግባር መሆኑንና ለዚህም አድናቆታቸውን በመግለጽ አመስግነዋል፡፡ የፌዴራልና የክልል የስራ ሃላፊዎች፣ የዩነቨርሰቲው አመራሮችና ተማሪዎች በተገኙበት በዚሁ ዝግጅት ላይ ለፕሮግራሙ መሳካት የላቀ አስተዋጾኦ ላደረጉ ግለሰቦችና ደርጅቶች የምስክር ወረቀት ተስጥቷል፡፡ የሎቶሪ እጣት ማውጣትና የተለያዩ የኪነ ጥበብ ስነ ስርዓቶች ቀርበዋል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር