ኢትዮ ቴሌኮም የኢንተርኔት ፍጥነት ጨምሯል ቢልም ደንበኞች ብሶበታል እያሉ ነው


•    የሞባይል ስልክ ጥራት መጓደል ምሬት እየፈጠረ ነው

ኢትዮ ቴሌኮም በቅርቡ በኢንተርኔት አገልግሎት ግንኙነት ላይ ተፈጥሮ የነበረው ችግር ሙሉ ለሙሉ መፈታቱን ቢገልጽም፣ አሁንም የኢንተርኔት አገልግሎት የጥራት መጓደል እየባሰበት መሆኑን ደንበኞች አስታወቁ፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም በቅርቡ በኢንተርኔት አገልግሎት ፍጥነት ላይ ይደርስ የነበረው ችግር የተፈጠረው በባህር ጠለቅ የፋይበር ኬብል መስመር ላይ በደረሰ ከፍተኛ ብልሽት ሳቢያ እንደሆነ መጥቀሱ ይታወሳል፡፡ 

ይህንኑ ጉዳይ በማስመልከት ትናንት ባወጣው መግለጫ ደግሞ ተፈጥሮ የነበረው ችግር ሙሉ በሙሉ በመቃለሉ ፈጣን የኢንተርኔት አገልግሎት ማግኘት የሚቻል መሆኑን አስታውቋል፡፡ ይህንኑ የኢትዮ ቴሌኮም መግለጫ ተከትሎ ያነጋገርናቸው አንዳንድ ደንበኞች ግን አሁንም የኢንትርኔት አገልግሎት ፍጥነት እንደተባለው የተስተካከለ ሳይሆን፣ እየባሰበት ነው ብለዋል፡፡

በሰሞኑ የኢንተርኔት አገልግሎት ጥራት መጓደል በርካታ ደንበኞች ሲያማርሩ እነደነበር የተገለጸ ሲሆን፣ በተለይ አገልግሎታቸውን በቀጥታ ከኢንተርኔት ጋር ያያያዙ ተቋማት የተፈጠረው ችግር ለኪሳራ ዳርጐናል እስከማለት መድረሳቸው አይዘነጋም፡፡ 

አሁንም ይህ ችግር እየታየ በመሆኑ በአግባቡ የሚፈለገውን አገልግሎት ለመስጠት እንዳላስቻላቸውና ኢትዮ ቴሌኮም አሁንም የኢንተርኔት አገልግሎት የጥራት ደረጃውን ማሻሻል ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡ 

በትናንቱ የኢትዮ ቴሌኮም መግለጫ ግን አፍሪካን ከመካከለኛው ምሥራቅና እስያን ከአውሮፓ ጋር በሚያገናኘው በሜዴትራንያን ባህር ውስጥ በሚያልፈው ኦፕቲካል ፋይበር ኬብል ላይ መጋቢት 13 ቀን 2005 ዓ.ም. የደረሰው ጉዳት ለኢንተርኔት ኮኔክሽን ፍጥነት አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን ይገልጻል፡፡ በዚህም ምክንያት የአገሪቱ ጠቅላላ የኢንተርኔት አቅምን 50 በመቶ እንዲቀንስ ማድረጉን የሚያትተው መግለጫው፣ አሁን ግን በፋይበር ኬብሉ ላይ የደረሰው ጉዳት በመጠገኑ ችግሩ እንደተቃለለ ገልጿል፡፡ 

‹‹ሲኮም የተባለው የቴሌኮም ኩባንያ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ የጥገና ሥራውን ከስምንት ቀናት በኋላ በማጠናቀቁ፣ በአሁኑ ወቅት በኢንተርኔት ኮኔክሽን ፍጥነት ላይ ይደርስ የነበረው ችግር ሙሉ በሙሉ (100 በመቶ) ተወገደ፤›› በማለትም ድርጅቱ በመግለጫው አስታውቋል፡፡ 

ያነጋገርናቸው የኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞች ግን የቴሌ የኢንትርኔት ችግር መጋቢት 13 ቀን 2005 ዓ.ም. ያልጀመረ መሆኑን በማስረዳት፣ ችግሩ ቀደም ብሎ የነበረና ዘላቂ መፍትሔ የተሰጠው አለመሆኑን ነው፡፡ 

ቀድሞም ቢሆን የኢንተርኔት አገልግሎቱ ፍጥነት ብቻ ሳይሆን በተደጋጋሚ ከአገልግሎት ውጭ እየሆነ ማስቸገሩ እየታወቀ ችግሩ ተወግዷል ማለት እንደማይቻልም ያስረዳሉ፡፡ በተለይ በፋይበር ኦፕቲክስና በብሮድባንድ ደረጃ አገልግሎቱን በአግባቡ መጠቀም የተሳናቸው የተያዘው ቀልድ ነው ብለዋል፡፡ 

የኢትዮ ቴሌኮም ኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ማኔጀር አቶ አብዱራሒም አህመድ ግን፣ በኢንተርኔት አገልግሎት ፍጥነት ላይ የተፈጠረው ችግር ሙሉ በሙሉ ተወግዷል የሚለውን እምነታቸውን ይገልጻሉ፡፡ 

እንዲያውም በፋይበር ኬብሉ ላይ በደረሰው ብልሽት የአገሪቱን የኢንትርኔት አገልግሎት የበለጠ ለማሳደግ ተጨማሪ አቅም በመፍጠሩ ችግሩ መወገዱን በአፅንኦት ይናገራሉ፡፡

አልፎ አልፎ ግን በአንዳንድ አካባቢዎች ከፋይበር ኬብል ችግር ውጭ በሆኑ የተለያዩ ምክንያቶች መቆራረጦች ሊኖሩ የሚችሉ ቢሆንም፣ በአገሪቱ የኢንተርኔት አቅም ደረጃ ግን በጥራት አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል መሠረተ ልማት መዘርጋቱን አቶ አብዱራሒም ጠቁመዋል፡፡ 

የኢንተርኔት መቆራረጥ ሊከሰት ከሚችልባቸው ምክንያቶች ውስጥም አንዱ የራሱ የኢንተርኔት ተጠቃሚው የመገልገያ መሣሪያ አቅም ችግር ሊሆን እንደሚችል የገለጹት አቶ አብዱራሒም፣ ሌሎች ምክንያቶችም ሊኖሩ መቻላቸውንም ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡ 

በአሁኑ ወቅት የሞባይል የኢንተርኔት ተጠቃሚዎችን ጨምሮ የኢትዮ ቴሌኮም መደበኛ የኢንትርኔት ደንበኞች ቁጥር 3.6 ሚሊዮን መድረሱን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ 

በሌላ በኩል ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በሞባይል ስልክ አገልግሎት ላይ የተፈጠረው ችግር በርካታ ደንበኞችን እያማረረ ነው፡፡ ደንበኞች በኔትወርክ ችግር ምክንያት በስልክ ጉዳያቸውን መፈጸም እንዳቃታቸው፣ በተደጋጋሚ የአገልግሎት መቋረጥ እንደሚያጋጥማቸውና የመስመር መደበላለቅ እንዳስቸገራቸው እየገለጹ ነው፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም በተደጋጋሚ ችግሩን ለማስወገድ ቃል ቢገባም፣ የሞባይል ስልክ አገልግሎት ጥራት ደረጃ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየወረደ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ድርጅቱ ይህንን የገዘፈ ችግር መፍታት ካልቻለ በሥራቸው ላይ ከፍተኛ ቀውስ እንደሚያጋጥማቸው ለዝግጅት ክፍላችን በተደጋጋሚ ያስታወቁ ደንበኞች ተናግረዋል፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም ካቃተው ለምን ሌላ አማራጭ አይፈለግም በማለት የሚጠይቁ እየበዙ ናቸው፡፡  
    http://www.ethiopianreporter.com/index.php/news/item/1319-%E1%8A%A2%E1%89%B5%E1%8B%AE-%E1%89%B4%E1%88%8C%E1%8A%AE%E1%88%9D-%E1%8B%A8%E1%8A%A2%E1%8A%95%E1%89%B0%E1%88%AD%E1%8A%94%E1%89%B5-%E1%8D%8D%E1%8C%A5%E1%8A%90%E1%89%B5-%E1%8C%A8%E1%88%9D%E1%88%AF%E1%88%8D-%E1%89%A2%E1%88%8D%E1%88%9D-%E1%8B%B0%E1%8A%95%E1%89%A0%E1%8A%9E%E1%89%BD-%E1%89%A5%E1%88%B6%E1%89%A0%E1%89%B3%E1%88%8D-%E1%8A%A5%E1%8B%AB%E1%88%89-%E1%8A%90%E1%8B%8D

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር