ቴሌቪዥን ያደመቀው ምርጫ


ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ ነበር፡፡ ከአንድ የኢሕአዴግ ደጋፊ ወዳጄ ጋር ወደ አንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች አብረን ሄደን ነበር፡፡
በምርጫ ጣቢያዎቹ ስለተመለከትናቸው ጉዳዮች እያወራን ወደ ቤታችን እተመለስን ሳለን ከሁለት ወንዶች ጋር ፈጠን ፈጠን እያለች የምትጓዝ ሴት ጓደኛዬን ‹‹ደህና ነህ? እንዴት ነህ?›› በማለት ጠጋ ብላ፣ ‹‹አንተ አታውቀኝም እኔ ግን አውቅሃለሁ፤›› ትለዋለች፡፡ ጓደኛዬ ግራ በተጋባ አኳኋን ሰላምታ እየተለዋወጠ ሳለ ጊዜ ሳትሰጠው፣ ‹‹አልመረጥክም አይደለም? እባክህ ቁጥሩ አልሞላልንም፡፡ ጎድሎብናል ሂዱና ምረጡ፤›› ትላለች፡፡ በነገሩ ግራ መጋባቱ የሚያሳብቅበት ጓደኛዬ፣ ‹‹አይ መርጫለሁ›› ይላል፡፡ ‹‹ጓደኛህስ?›› ትለውና እሱም እየቀለደ፣ ‹‹ተይው እሱ አሸባሪ ነው፡፡ ተቃዋሚ ነው፤›› ይላታል፡፡ ‹‹አሃ የእኛ መስሎኝ'ኮ ነው›› የሚለውን ስሜታዊ ንግግሯን ሳትጨርሰው ወደ እኔ እያየች፣ ‹‹ለነገሩ ተቃዋሚም'ኮ ይመርጣል፤›› ትላለች፡፡ ‹‹ምንድን ነው የጎደለባችሁ?›› ብዬ ስጠይቃት፣ ‹‹ቁጥር አልሞላልንም፣ ሰው አልመጣም፤›› በማለት እቅጩን ነገረችን፡፡ ጓደኛዬ የሴትየዋ ንግግር እኔ ጆሮ መድረሱ ትንሽም ቢሆን ያስጨነቀው ይመስል፣ ‹‹አሃ መስማት የምትፈልገውን አገኘህ አይደል?›› እያለ መቀለድ ይጀምራል፡፡

እሑድ ሚያዝያ 6 ቀን 2005 ዓ.ም. በተካሄደው የአካባቢና የከተማ አስተዳደር ምርጫ፣ 31.6 ሚሊዮን መራጮች መመዝገባቸውን የአገሪቱ ምርጫ ቦርድ ያሳወቀ ሲሆን፣ በአጠቃላይ በአገሪቱ 44,509 የምርጫ ጣቢያዎችም ለድምፅ መስጫ አገልግሎት ክፍት ሆነው ውለዋል፡፡ እንዲሁም ደግሞ ለዚሁ ለአካባቢ፣ ለአዲስ አበባና ለድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ምርጫዎች ከፍተኛ ዕጩዎች ያቀረበው ኢሕአዴግ በመሆኑ፣ ብቻውን 3.7 ሚሊዮን ተወዳዳሪዎች አቅርቧል፡፡ እንዲሁም የኢትዮጵያ ሰላማዊ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ 183 ዕጩዎች፣ የመላው ኢትዮጵያ ብሔራዊ ንቅናቄ 85 ዕጩዎች፣ ቅንጅት ለዲሞክራሲና የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ በበኩላቸው 42 ዕጩዎች በማቅረብ ተሳትፈዋል፡፡

የአካባቢ ምርጫ ትርጉም አለው
ይኼው የአካባቢና የከተማ አስተዳደር ምርጫ የመንግሥት ለውጥ የሚደረግበትና እጅግ ከፍተኛ ፉክክር የሚጠበቅበት አይደለም፡፡ ነገር ግን በሁለትና ሦስት ምክንያቶች ምርጫው ትኩረት ሊስቡ የሚችሉ ሁኔታዎች ነበሩት፡፡ አንደኛው የዘንድሮ የአካባቢ ምርጫ ለዝቅተኛ የአስተዳደር እርከን ማለትም ለወረዳ (ክፍለ ከተማ) እና ለቀበሌ ብቻ የሚደረግ አልነበረም፡፡ በኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ጭላንጭል በታየበት በምርጫ 97 ዓ.ም. እጅግ ከፍተኛ ፉክክር የታየበትና በወቅቱ የገዥው ፓርቲ ዋና ተቀናቃኝ ሆነው ብቅ ብለው ከከሰሙ ጠንካራ ጥምረቶች መካከል የነበረው የእዚያው ወቅት ቅንጅት ለዲሞክራሲና ለአንድነት፣ ጠቅልሎ የወሰደው የአዲስ አበባ ምክር ቤት ይታወሳል፡፡

ሁለተኛ በምርጫ 97 የታየው የተቃዋሚዎችና የገዥው ፓርቲ ሞቅ ያለ ፉክክር ምንጩ እዚሁ አዲስ አበባ ነው፡፡ ቀጥሎም የፖለቲከ ሙቀቱ ወደ መላ አገሪቱ ተዛምቶ ነበር፡፡ በመሆኑም ከሁለት ዓመት በኋላ በ2007 ዓ.ም. ለሚካሄደው አምስተኛው ዙር የፖለቲካ ፓርቲዎች ለአገር አቀፍ ምርጫ ያላቸውን ዝግጅት የሚፈትሹበት ነው፡፡ እነዚህ የአካባቢ ምርጫዎች ፓርቲዎቹ ከሕዝብ ጋር ግንኙነት ፈጥረው ለመቆየትም መልካም አጋጣሚ ነበሩ፡፡

ሦስተኛ በቀጥታ ገዥው ፓርቲና ዋናውን የአገር መሪ ለመምረጥ የሚደረግ ሒደት ባይሆንም፣ ከሕዝቡ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው የወረዳና የቀበሌ ተሿሚዎች የሚወከሉበት ነው፡፡ በተለይ ደግሞ በአሁኑ ወቅት ሕዝቡ በታችኛው የአስተዳደር እርከኖች ሙሰኝነት፣ ፍትሕ ማጣትና የመልካም አስተዳደር ዕጦት በመሳሰሉት ከፍተኛ እሮሮና ቅሬታ በሚያሰማበት ወቅት፣ ምናልባት ቅሬታውን የሚገልጽበትና በገዥው ፓርቲ ላይ ‹‹ቢጫ ካርድ›› የሚያሳይበት አጋጣሚ መፍጠር ይቻል ነበር፡፡

አማራጭ የሌለው ምርጫ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤትና የክፍለ ከተማ ምክር ቤት አባላት ምርጫ ባሳለፍነው እሑድ ሲካሄድ፣ በየክፍላተ ከተሞቹ በመዘዋወር ከተመለከትናቸው ውስጥ ‹‹አማራጭ የሌለው ምርጫ›› የሚሰኝ ይመስል ነበር፡፡ በተለይ የክፍለ ከተማ ምክር ቤት አባላት ምርጫ ያለምንም ተቀናቃኝ በኢሕአዴግ ተወዳዳሪነት ብቻ የተጠናቀቀ ነበር፡፡

በተዘዋወርንባቸው የምርጫ ጣቢያዎች በሙሉ ለመታዘብ የቻልነው የምርጫ ወረቀቱ ላይ 30 ብቻ ተወዳዳሪዎች መስፈራቸውን ነበር፡፡ መራጩ ከራሱ ከኢሕአዴግ ዕጩዎች እንኳን አወዳድሮ የሚፈልገውን ለመምረጥ የሚችልበት ዕድል አልነበረም፡፡ እያንዳንዱ ክፍለ ከተማ ሰላሳ ዕጩዎችን የሚያሳልፍ በመሆኑም ሰላሳዎቹም ተያይዘው ያልፋሉ፡፡ የጠየቅናቸው መራጮች እንደሚሉት ደግሞ ለየክፍለ ከተማው ከተወዳደሩ ዕጩዎች ውስጥ ብዙዎቹን የማያውቋቸው ቢሆንም፣ የዕጩዎቹ ቁጥር ከሚፈለገው ጋር መሳ ለመሳ በመሆኑ የሚያውቁትንና ይሠራል የሚሉትን እንኳን ለመምረጥ ዕድል አልነበራቸውም፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት መምረጫ ላይ ኢሕአዴግ፣ ቅንጅት፣ ኢራፓ፣ መኢብን፣ ኢፍዴኃግ የነበሩ ቢሆንም፣ በቁጥር ደረጃ ሲታይ ፍፁም የሚገናኙ አልነበሩም፡፡

በተዘዋወርንባቸው ጣቢያዎች በሙሉ የአመራረጡን ዘዴ የሚያስረዱ ምርጫ አስፈጻሚዎች የተሰየሙ ቢሆንም፣ አብዛኛው መራጭ በትዕግስትና በጥሞና ሲከታተል አይስተዋልም ነበር፡፡ በተለይ ሴቶችና በዕድሜ የገፉት እናቶች ይሻሉ እንደሆን እንጂ ወንዶችና ወጣት ሴቶች ብዙም ትኩረት ሳይሰጡ ወይም እናውቃለን የሚል የአንፈልግም ምልክት በእጃቸው እየሰጡ ይገቡ ነበር፡፡ የምርጫ አስረጂዎችን ጠይቀን እንደተረዳነው መራጮች ለመረዳት ብዙም ፍላጐት አያሳዩም ነበር፡፡ ሆኖም በፍላጐት ቆመው የሚያዳምጧቸው ጥቂቶችም ነበሩ፡፡

 በተዘዋወርንባቸው አብዛኛዎቹ ጣቢያዎች ኢሕአዴግ ሙሉ በሙሉ ታዛቢዎችን ያስቀመጠ ሲሆን፣ ከተቃዋሚዎች ግን በአንድም ጣቢያ ተወካይ አላየንም፡፡

መለስም እንደ ሻቬዝ
የዘንድሮው ምርጫ በቅስቀሳው በኩል ከቀደሙት ጋር ሲነፃፀር የተቀዛቀዘ ነው፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ፖስተር ፈልጐ የማግኘት ዕድሉ ጠባብ ሲሆን፣ የኢሕአዴግን በተራራቀ ቦታም ቢሆን በኤ3 መጠን ፖስተሮች ማግኘት ይቻል ነበር፡፡ በአማካይ ቦታዎች የተለጠፉት ትላልቅ የቅስቀሳ ፖስተሮች ግን ተመራጩ የቬንዙዌላ ፕሬዚዳንት ኒኮላስ ማዱሮ ለምርጫ ቅስቀሳ የሟቹን ፕሬዚዳንት ሑጐ ሻቬዝ ምስልና ሥራ ከተጠቀሙበት ጋር የተመሳሰለ ነበር፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የተለያዩ ፎቶዎች ከተለያዩ የአዲስ አበባ መሠረተ ልማቶች ጋር በማያያዝ ‹‹የመለስን ራዕይ ለማሳካት፣ የጀመራቸውን ለማስቀጠል . . . . ኢሕአዴግን ምረጡ›› የሚሉ ነበሩ፡፡ ከምርጫው ጋር በተያያዘ ግን እያንዳንዱ የክፍለ ከተማ ዕጩ ለኅብረተሰቡ በበቂ መረጃ የተዋወቀበት አካሄድ አልነበረም፡፡

በቴሌቪዥን የደመቀው ምርጫ
ሪፖርተር ጋዜጣ ያሰማራቸው በርካታ ጋዜጠኞች በአዲስ አበባ የተካሄደውን ምርጫ ተንቀሳቅሰው የተመለከቱ ሲሆን፣ በአብዛኛው ምልከታቸው ተመሳሳይ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከንጋቱ ጀምሮ በተለያዩ የምርጫ ጣቢያዎች ጊዜያዊ ስቱዲዮ አቋቁሞ ስለምርጫው መልካምነት ሲዘግብ የዋለ ሲሆን፣ የሪፖርተር ባልደረባዎች ትዝብት ግን የመንግሥት ሚዲያ ካቀረበው ጋር የተለያየ ይመስላል፡፡

በአብዛኛዎቹ የምርጫ ጣቢያዎች (ተዘዋውረን ባየናቸው የቂርቆስ፣ ኮልፌ ቀራንዮ፣ የካ ክፍለ ከተሞች፣ ወዘተ) በምርጫ ጣቢያዎች የተሰላቹ መራጮችና አስመራጮች ተመልክተናል፡፡ አንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች ለቅሶ ቤት እስኪመስሉ ድረስ በተለይ ከረፋድ በኋላ ምንም ድምፅ የሚሰጥ ሰው አይታዩባቸውም ነበሩ፡፡
በአንዳንዶቹ ደግሞ እስከ ረፋዱ 6፡00 ሰዓት ከ600 ተመዝጋቢዎች ውስጥ ሰባት ሰዎች ብቻ ድምፅ የሰጡበትን አጋጣሚ ተመልክተናል፡፡ በሌሎች አካባቢዎችም (ለምሳሌ በየካ ክፍለ ከተማ) እስከ 9፡00 ሰዓት የምርጫ ካርድ ከወሰዱት መካከል ከግማሽ የማይበልጡ ብቻ መርጠዋል፡፡

በተመሳሳይ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ምርጫ ጣቢያ 11 ወረዳ 4 ቀበሌ 05/08 ላይ ካርድ ከወሰዱት 398 መካከል 196 (ወንዶች 88 ሴቶች 108) መምረጣቸውን፣ እንዲሁም ደግሞ በተመሳሳይ አካባቢ ምርጫ ጣቢያ 13 ወረዳ 14 ቀበሌ 39 ላይ በአንድ መዝገብ የምርጫ ካርድ ወስደው ከተመዘገቡት 271 ሰዎች ውስጥ 167 ሰዎች ድምፃቸውን ሰጥተዋል፡፡

ወደ አካባቢው ተዘዋውረን ሒደቱን የተመለከትነው 9፡00 ሰዓት አካባቢ ሲሆን፣ በእያንዳንዱ የምርጫ ጣቢያ ከአሥር ደቂቃ በላይ ቆይታ ያደረግን ቢሆንም፣ በአንዱ ምርጫ ጣቢያ ብቻ ሁለት ሰዎች፣ በአንዱ አንድ ሰው፣ በሌላኛው ምንም መራጭ ሳናይ ሄደናል፡፡ የሪፖርተር ጋዜጣ ትዝብት ይኼ ቢሆንም፣ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ካርድ ከወሰዱት መራጮች መካከል 90 በመቶ በነቂስ ወጥተው መምረጣቸውን ገልጿል፡፡ የቦርዱ መግለጫ በሕዝቡ ውስጥ የተለያዩ ቀልዶች እየተወጡበት ነው፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ‹‹ኢሕአዴግ በጠባብ ልዩነት እየመራ ነው›› የሚል ይገኝበታል፡፡

የኢሕአዴግ ወይስ የሕዝብ ታዛቢዎች?
ምርጫው ምንም ፉክክር የሌለበትና ምርጫ ምርጫ የሚሸት ነገር የሌለው፣ አብዛኛዎቹ መራጮቹም ሆነ አስመራጮች እንዲሁም ታዛቢዎች እጅግ በተሰላቸ መንፈስ የታዩበት ነበር፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች የሕዝብ ታዛቢዎች የኢሕአዴግ አባል መሆናቸውን ራሳቸውም ይገልጹልን ነበር፡፡

የሕዝብ ታዛቢዎች ከማናቸውም የፖለቲካ ፓርቲ ነፃ መሆን እንዳለባቸው የምርጫ አዋጁ ይደነግጋል፡፡ በዚሁ የአካባቢ ምርጫ ኢሕአዴግ በአብዛኛው ሙሉ ለሙሉ የተቆጣጠረው ሒደት በመሆኑ ማጭበርበር አያስፈልገውም ቢባልም፣ አንድም ለሒደቱ ክብር ሲባል ሁለትም በቀጣዩ ዋና አገራዊ ምርጫ መለመድ የሌለበት ባህል መሆን እንዳለበት ተተችቷል፡፡ ተቃዋሚዎች በተለያዩ አካባቢዎች የሚመለመሉ የምርጫ አስፈጻሚዎችና ታዛቢዎች ለገዥው ፓርቲ ቅርበት ያላቸው ናቸው በማለት፣ በገለልተኝነት መታዘብ አይችሉም የሚል ቅሬታ ደጋግመው የሚያነሱ ሲሆን፣ ይኼ በተግባር በአንዳንድ ጥቂት የምርጫ ጣቢያዎች እውነት ሆኖ ተስተውሏል፡፡

የሪፖርተር ጋዜጣ ባልደረቦች ተንቀሳቅሰው በተመለከቱዋቸው የምርጫ ጣቢያዎች በሙሉ አንድም የተቃዋሚ ታዛቢዎች (ተወካዮች) አልነበሩም፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች በተለይ ለአዲስ አበባ ምክር ቤት የተወዳደሩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ያሉ ቢሆንም፣ ከኢሕአዴግና ከሕዝብ ታዛቢዎች ውጪ አንድም የተቃዋሚ ተወካይ አልተመለከትንም፡፡ ከአንዳንድ ተቃዋሚዎች እንደሰማነው ይኼ የሆነው በገንዘብ ማጣት ምክንያት ቢሆንም፣ በተጨባጭ ምርጫውን ችላ ከማለታቸው የመነጨ ይመስላል፡፡

ምርጫ ምንም ሥፍራ ላይኖረው ይሆን?
በአጠቃላይ ከላይ ከጠቃቀስናቸው ጠቀሜታዎች አንፃር የዘንድሮ የአካባቢ ምርጫ እንዲህ በደበዘዘና በደከመ መንፈስ መካሄዱ ለብዙዎች አሳዛኝ ሲሆን፣ ውጤቱም የሚያሳየው ይኼንኑ ነው፡፡ አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች እንደሚገልጹት፣ ወደ ምርጫ ጣቢያ በመሄድ በፈቃዳቸው የተመዘገቡት አብዛኛዎቹ የኢሕአዴግ ደጋፊዎች ናቸው፡፡ ሌሎች ደግሞ ካርድ ውሰዱ በሚል በተደረገባቸው ከፍተኛ ቅስቀሳና ግፊት መሆኑን ይናገራሉ፡፡ አንድ ዕድሜያቸው ከ60 በላይ የሆኑት አዛውንት (መራጭ) እንደገለጹልን፣ የመረጡበት ምክንያት በቀበሌ የሚያገኙት አንዳንድ አገልግሎት እንዳይጎድልባቸው በመፍራት ነው፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ብቻ አድምቆት የዋለው ይኼው ምርጫ ቀልብ የሚስብ ቅስቀሳም ሆነ ክርክር ያልተደረገበት ነበር፡፡ በአብዛኛው ወጥተው ድምፃቸውን የሰጡ የኢሕአዴግ ደጋፊዎች ሲሆኑ፣ ችግረኛ እናቶችም በብዛት ሲመርጡ ተስተውሏል፡፡

ተቃዋሚዎችም ሒደቱን እንደ ቁብ የቆጠሩት አይመስልም፡፡ ተዘዋውረን ያነጋገርናቸው ሰዎች እንደገለጹልን፣ ወደ ምርጫ ጣቢያ ሄደው ድምፃቸውን መስጠት የሚፈልጉት ለገዥው ፓርቲ ያላቸውን ድጋፍ ለማሳየት እንጂ፣ አንዳች ለውጥ ለማምጣት አስበው አይደለም፡፡ የተቃዋሚዎች ዕጩዎች መኖራቸውንም የሚያውቁም በጣም ጥቂቶች ናቸው፡፡

በኮልፌ ቀራንዮ ወረዳ 13 የምርጫ ጣቢያ ውስጥ የተለጠፈው የምርጫው ውጤት እንደሚያመላክተው፣ ለክፍለ ከተማ ምክር ቤት ኢሕአዴግ 30 ዕጩዎች አቅርቦ 289 ድምፅ ሲያገኝ፣ ለአዲስ አበባ አስተዳደር ኢሕአዴግ 257፣ ቅንጅት 13፣ ኢፍዴኃግ 8፣ መኢብን 6፣ ኢራፓ 3 ድምፅ አግኝተዋል፡፡

እንደሚታወቀው፣ ቀደም ሲል 18 ጥያቄዎች አቅርበው ሳይመለስላቸው የቀሩት መድረክ፣ መኢአድና የመሳሰሉ ታቃዋሚ ፓርቲዎች ያሉበት የ33 ተቃዋሚ ፓርቲዎች ስብስብ ከሒደቱ ወጪ ሆኗል፡፡ ከሒደቱ ላለመውጣት ብቻ ሲል አንድ ዕጩ በማቅረብ ተሳትፎ ያደረገው ኢዴፓም ራሱን ከምርጫ ውጭ ማድረጉ የሚታወስ ነው፡፡

ዋናዎቹ ተቃዋሚዎች በምርጫው ተሳትፎ ያደረጉት የፖለቲካ ፓርቲዎች የገዥው ፓርቲ ተለጣፊዎች መሆናቸውን፣ ለምርጫ ቅስቀሳና ለመሳሰሉ የሚሰጣቸውን ገንዘብ ለማግኘት የገቡ እንዳሉም በስፋት ይገልጻሉ፡፡ አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት፣ ከምርጫ 97 በኋላ ኢሕአዴግ ተቃዋሚዎቹን እንዳይንቀሳቀሱ ለማድረግ የወሰዳቸው አስተዳደራዊና ‹‹ሕጋዊ›› ዕርምጃዎች፣ በአገሪቱ ምርጫ ምንም ሥፍራ እንዲያጣ እያደረገ መሆኑን በብዛት ይተቻል፡፡ ተቃዋሚዎችም ኢሕአዴግም ከዚህ ትምህርት ወስደው በጋራ አንድ መፍትሔ ካላመጡ በሚቀጥለው ዋና ምርጫም ከኢሕአዴግ ደጋፊዎች ውጪ ወደ ምርጫ ጣቢያ ዞር የሚል ላይኖር እንደሚችል በስፋት እየተነገረ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በምርጫ ላይ ከፍተኛ ተስፋ መቁረጥ ስለመኖሩ አመላካች ይሆናል ማለት ነው፡፡

(ሔኖክ ያሬድ፣ ምሕረት ሞገስና ታምሩ ጽጌ ለዚህ ዘገባ አስተዋጽኦ አድርገዋል)    

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር