የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ ትልቅ ሥልጣን ሊሰጠው ነው


•    ማናቸውም ሕጐችና ውሳኔዎች ከሕገ መንግሥቱ አለመጣረሳቸውን ያያል

ለሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ ሰፊ ሥልጣን የሚሰጥ የሕግ ማሻሻያ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ፡፡
ረቂቅ አዋጁ የጉባዔውን የሥራ አድማስ በማስፋት በማንኛውም የመንግሥት አካል በክልል መንግሥታትም ቢሆን ከሕገ መንግሥቱ የሚቃረኑ ሕጐችና ውሳኔዎች ሲወጡ በመመልከት ለፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲያቀርብ ያስችለዋል፡፡

ጉባዔውን ያቋቋመው የ1993 ዓ.ም. አዋጅ መጠሪያ ‹‹የፌደራሉ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ አዋጅ›› የሚል ሲሆን፣ ይህ አባባል በተለይም ‹‹የፌደራሉ›› የሚለው ቃል የጉባዔውን የሥራ አድማስ በማጥበብ በማንኛውም አካል የወጣ ሕግ ከሕገ መንግሥቱ ቢቃረን የመመልከት ሥልጣን እንደሌለው ተደርጐ እንዲተረጐም ክፍተት መፍጠሩን የረቂቁ መግቢያ ያትታል፡፡

በመሆኑም የአዋጁን መጠሪያ ርዕስ በማስተካከል ‹‹የተሻሻለው የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ አደረጃጀትና አሠራር አዋጅ›› የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ የጉባዔው መቋቋሚያ አዋጅን ማስተካከል ያስፈለገበትን ምክንያት የሚያትተው የረቂቁ መግቢያ፣ በተለይ መንግሥት የነደፈውን የአምስት ዓመት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በማሳካት ረገድ ባለው የማይተካ ሚና በሕገ መንግሥቱ ላይ የጋራ አገራዊ መግባባት የመፍጠር ኃላፊነት በሚገባ መወጣት እንዲችል በማስፈለጉ ነው ይላል፡፡

የጉባዔውን የሥራ አድማስ የሚያሰፋው የአዋጁ ክፍል ሁለት ላይ የተደረገው ማሻሻያ አጣሪ ጉባዔው ማንኛውም ሕግ፣ ልማዳዊ አሠራር፣ የመንግሥት አሠራር፣ እንዲሁም የመንግሥት አካል ወይም የባለሥልጣን ውሳኔ ከሕገ መንግሥቱ ጋር ይቃረናል የሚል ጥያቄ ሲነሳና ትርጉም የሚያስፈልገው መሆኑን ሲያምንበት፣ የደረሰበትን ውሳኔ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲያቀርብ ይፈቅድለታል፡፡

የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄን ሊያቀርቡ ስለሚችሉ ሰዎች ባደረገው ማሻሻያ በፍርድ ቤት በተያዙ ጉዳዮች የተነሳ ጥያቄ ከሆነ ጥያቄው ጉዳዩን በያዘው ፍርድ ቤት ወይም በባለጉዳዩ ሊቀርብ እንደሚችል ረቂቁ ይደነግጋል፡፡ በማንኛውም የአስተዳደር አካል ወይም ባለሥልጣን በተሰጠ የመጨረሻ ውሳኔ ላይ የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ ከተነሳ፣ ጥያቄው በማንኛውም ባለጉዳይ ለአጣሪ ጉባዔው ሊቀርብ እንደሚችል ይደነግጋል፡፡

በተጨማሪም በፌደራል ወይም በክልል ሕግ አውጭ አካል የወጣ ሕግ ላይ ጥያቄ ከተነሳ ማንኛውም አካል ወይም ዜጋ ለአጣሪ ጉባዔው ማቅረብ እንደሚችል ይደነግጋል፡፡ አጣሪ ጉባዔው በቀረቡ የትርጉም ጥያቄዎች ዙሪያ ውይይት ሲያደርግ፣ ውሳኔ ሲሰጥ ወይም የውሳኔ ሐሳብ የሚቀርብበትን ሥርዓት ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ እንዲያካሂድ ማሻሻያ ረቂቁ አካቷል፡፡

የአጣሪ ጉባዔው አባል አጣሪ ጉባዔው እየተመለከተ የሚገኘው ጉዳይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ጥቅሙን እንደሚነካ ካወቀ ጉዳዩን ለጉባዔው ማሳወቅ እንዳለበት፣ ጉባዔውም እንደዚህ ዓይነት የጥቅም ግጭት የሚስተዋልባቸው አባላትን በጉዳዩ ላይ ድምፅ መስጠት እንዳይችሉ ማድረግ እንዳለበት፣ የጥቅም ፍላጐቱን ደብቆ በቀረበው የትርጉም ጥያቄ ላይ የተሳተፈ አባል ከተገኘ በሕግ ተጠያቄ እንዲሆን ረቂቁ ይደነግጋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም አጣሪ ጉባዔው በቀረቡለት የትርጉም ጥያቄዎች ላይ ውሳኔ ከመስጠቱ በፊት ወይም ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ከማቅረቡ በፊት አግባብነት አላቸው ብሎ የሚያምንባቸውን ባለሙያዎች አስተያየት እንዲሰበሰብ ተፈቅዶለታል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ አጣሪ ጉባዔው የሕገ መንግሥት ትርጉም ያሸዋል አልያም አያሻውም ያለበትን ውሳኔ በዝርዝር ለቅሬታ አቅራቢው በጽሑፍ የማሳወቅ ግዴታ ተጥሎበታል፡፡ በፍርድ ቤት የተያዙ ጉዳዮች ላይ የሕገ መንግሥት ጥያቄ ከተነሳ ጉባዔው ወይም የፌዴሬሽን ምክር ቤት የፍርድ ቤቱን ሒደት እንዳስፈላጊነቱ እንዲዘገይ ማድረግ ተፈቅዶላቸዋል፡፡

በ1997 ዓ.ም. የተካሄደውን አገር አቀፍ ምርጫ ተከትሎ ቅንጅት በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ላይ ክስ መሥርቶ የነበረ ቢሆንም፣ ክሱን የተመለከተው ፍርድ ቤት የሕገ መንግሥት ትርጉም ያሻዋል ማለቱን የሚያስታውሱ አስተያየት ሰጪዎች፣ የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ በወቅቱ የሰጠው ምላሽ በፍርድ ቤቱ የቀረበው ጥያቄ ትርጉም የሚያስፈልገው አይደለም በማለቱ፣ ፍርድ ቤቱ ከፍተኛ የፖለቲካ ተፅዕኖ ውስጥ እንዲወድቅ አድርጐት እንደነበር ያስረዳሉ፡፡ አሁን የቀረበው ማሻሻያ ለቅሬታ አቅራቢ ወይም የትርጉም ጥያቄ ለሚያነሱ አካላት ለማሰጠው ምላሽ ተገቢ ምክንያቱን በጽሑፍ እንዲያቀርብ መገደዱ ትልቅ ዕርምጃ ነው ይላሉ፡፡

በሕገ መንግሥት ማርቀቅ ሒደት ላይ ተሳታፊ የነበሩት ፕሮፌሰር አንድሪያስ እሸቴ የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ መታየት ያለበት በጉባዔውና በፌዴሬሽን ምክር ቤት ሳይሆን፣ ገለልተኛ በሆነ የሕገ መንግሥት ፍርድ ቤት ነው በሚል አቋማቸው ይታወቃሉ፡፡

ለዚህ የሚያቀርቡት መከራከሪያ ራሱ መንግሥት ተከሳሽ፣ ዳኛም ራሱ መሆን አይገባውም፡፡ ይህ እንዲሆን መፍቀድ ሕገ መንግሥቱ ለኅብረተሰቡ ተደራሽ እንዳይሆን ያደርገዋል የሚል ነው፡፡

በአሁኑ ማሻሻያ ላይ በዚህ ረገድ የተፈጠረው ልዩ ነገር አጣሪ ጉባዔው ከአዲስ አበባ ውጪ ቢሮዎችን በማደራጀት ለኅብረተሰቡ ቅርብ እንዲሆንና የጥቅም ጉዳይ ያለባቸው የጉባዔው አባላት ጥቅማቸውን በሚነኩ የትርጉም ጥያቄዎች ላይ በድምፅ እንዳይሳተፉ ማድረጉና ጉባዔው የባለሙያዎችን አስተያየት እንዲቀበል መፈቀዱ ነው፡፡ ይህም ሕገ መንግሥቱ ከፀደቀ ከ18 ዓመታት በኋላ የተደረገ አንድ ዕርምጃ ነው ማለት ይቻላል፡፡    

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር