የፖለቲካ ፓርቲዎች የምረጡኝ ቅስቀሳ ነገ የጀምራል


አዲስ አበባ ፣መጋቢት 3፣2005 (ኤፍ ቢ ሲ) ከአንድ ወር በኋላ በሚካሄደው ምርጫ የሚወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በመገናኛ ብዙሃን የተመደበላቸውን የአየር ሰዓትና የጋዜጣ አምድ በአግባቡ ሊጠቀሙበት እንደሚገባ ብሄራዊ የምርጫ ቦርድ አሳሰበ።
በቀጣዩ ወር በመላ ሃገሪቱ ለሚካሄደው የአካባቢ ምርጫ ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፥ የምረጡኝ ቅስቀሳ ዘመቻ በይፋ ከጀመሩ ትናንት 1 ወር መድፈናቸውን የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ ያመለክታል።
ምንም እንኳን በዚህ ጊዜ ውስጥ ፓርቲዎቹ የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም ፕሮግራምና እቅዶቻቸውን ለህዝብ ማስተዋወቅ የሚችሉ ቢሆንም ፥ ባለፉት ሳምንታት ያነጋገርናቸው አብዛኞቹ ፓርቲዎች ግን ምንም ዓይነት የምረጡኝ ቅስቀሳ አለማድረጋቸውን ተናግረዋል።
ፓርቲዎቹና በተለያዩ መንገዶች የሚያደርጓቸው የምረጡኝ ቅስቀሳዎች እንደተጠበቁ ሆነው ለአንድ ወር የሚቆየው እና በመገናኛ ብዙሃን የሚያደርጉት ቅስቀሳ ነገ ይጀምራል።
ከብሮድካስት ባለስልጣን የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው ፥ ከዚህ ቀደም በነበሩ ልምዶች ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ የፖለቲካ ፓርቲዎች በመገናኛ ብዙሃን የሚመደብላቸውን የአየር ሰዓትም ሆነ የጋዜጣ አምድ አሟጦ ያለመጠቀም ችግር አለባቸው።
ለአብነት ያህል እንኳን በ2002ቱ ምርጫ 23 ያህል ፓርቲዎች ከተመደበላቸው ውስጥ ግማሹን ሳይጠቀሙበት ሲቀሩ ፥ 10 ፓርቲዎች ደግሞ በኤሌክትሮኒክስም ሆነ በህትመት መገናኛ ብዙሃን የተመደበላቸውን የጋዜጣ አምድና የአየር ሰዓት ሙሉ ለሙሉ አልተጠቀሙበትም።
በመሆኑም በፓርቲዎቹ በኩል ይህ ሁኔታ ሊታረም እንደሚገባው ነው የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ነጋ ዱፊሳ የሚናገሩት።
ሃላፊው ፓርቲዎቹ መገናኛ ብዙሃኑን ተጠቅመው መልዕክታቸውን በሚያስተላልፉበት ወቅት የምርጫ ስነ ምግባር ደንቦችን እንዲያከብሩም ጠይቀዋል።
አቶ ነጋ እንዳሉት ፓርቲዎቹ በቅስቀሳ መልዕክታቸው ከሚጠቀሙት ቋንቋ የቃላት አመራረጥ ጀምሮ ፥ የመራጩን ህዝብ በነጻነት የመምረጥም ሆነ የሌላውን ተወዳዳሪ ፓርቲ መብቶች ማክበር ይኖርባቸዋል።
አስተያየታቸውን የሰጡ የፖለቲካ ፓርቲዎችም የተመደበላቸውን የአየር ሰዓትና የጋዜጣ አምድ በአግባቡ ለመጠቀም መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል።
በመጪው ወር በአዲስ አበባና ድሬዳዋ ለሚካሄደው የከተማ አስተዳደር ምክር ቤቶች እና በመላ ሃገሪቱ ለሚካሄደው አካባቢያዊ ምርጫ ፥ በአጠቃላይ 24 የፖለቲካ ፓርቲዎች አራት ሚሊየን በሚጠጉ እጩዎች ይወከላሉ።

Comments

Popular posts from this blog

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር