አርቲስቲክ ማተሚያ ድርጅት አዳዲስ አገልግሎቶችን እየሠጠ ነው


አርቲስቲክ ማተሚያ ድርጅት የምስጢራዊ ህትመት፣ የማማከር፣ ጥገና፣ የግራፊክ ዲዛይንና ፕሌት ቀረፃ እንዲሁም የህትመት ቴክኖሎጂ ሥልጠና አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኝ አስታወቀ።
ድርጅቱ የተመሰረተበትን 82ኛ ዓመቱንና የሐዋሳ ቅርንጫፍ የተቋቋመበትን ስድስተኛ ዓመት ምስረታ በዓልን እንዲሁም የደንበኞች ቀንን በሐዋሳ ከተማ አክብሯል ።
በከተማዋ ሌዊ ሆቴል ከደንበኞች ጋር የፓናል ውይይት ባካሄደበት ወቅት የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተካ አባዲ እንደተናገሩት፤ ድርጅቱ በኢትዮጵያ ብቸኛው የህትመት ቴክኖሎጂ ሥልጠና በመስጠት ላይ የሚገኝ ተቋም ነው ።
ድርጅቱ በእስካሁኑ ሂደት ወደ 500 ያህል ሠልጣኞችን ያስመረቀ ሲሆን፤ ሁሉም ምሩቃን ወደ ሥራው ዓለም ተቀላቅለዋል። በጥቃቅንና አነስተኛ ለተደራጁ ምሩቃን ድርጅቱ የማሽንና የሌሎች መሳሪያዎች ድጋፍ ያደርጋል።
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ ድርጅቱ ከአዳዲስ አገልግሎቶች መካከል የምስጢራዊ ህትመት አገልግሎትን ጀምሯል። በእስካሁንም ሂደት ከሠራቸው ምስጢራዊ ህትመቶች መካከል የደቡብና የሐረሪ ክልልን እንዲሁም የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮዎች ፈተናን ለአብነት ጠቅሰዋል። ይህንንና ሌሎችንም ምስጢራዊ ህትመቶችን በቀጣይ አጠናክሮ እንደሚቀጥልበት አመልክተዋል።
ድርጅቱ የግራፊክ፣ የዲዛይንና የፕሌት ቀረፃ አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኝ የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በተለይም በሰዓት እስከ አንድ ሺ ድረስ ፕሌት ማውጣት የሚችል ማሽን መግዛቱን ተናግረዋል።
ማተሚያ ድርጅቱ ለተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የማማከርና የጥገና አገልግሎት እንደሚሰጥ ጠቁመው፤ የበርካታ ዩኒቨርሲቲዎችን ማተሚያ ማሽኖች ለመጠገን የሚያስችሉ የጥገና ስምምነት መፈራረሙን ገልጸዋል። በቅርቡም የጥገና ሥራው እንደሚጀመርም ነው የጠቆሙት።
ድርጅቱ 82 ዓመትን ያስቆጠረ አንጋፋ ተቋም መሆኑን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የእድሜውን ያህል ግን አላደገም ብለዋል። በአሁኑ ወቅት የልማት ሠራዊትን በማደራጀት እና አንድ ለአምስት አደረጃጀትን በማዋቀር ውጤታማ ሥራ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
እርሳቸው እንደተናገሩት፤ አርቲስቲክ ጋዜጦችን ወደማተሙ ለመግባት በዝግጅት ላይ ይገኛል። ለእዚህም ጥናት እየተካሄደ ሲሆን፤ ጀምሮ ላለማቋረጥና ጋዜጦችን በጥራት ለማተም የሚያስችለውን እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛል። በሁለት ዓመት ውስጥ ለእዚሁ ሥራ የሚሆኑ ማሽኖችን በማስገባት ሥራውን የሚጀመር ይሆናል
የአርቲስቲክ ማተሚያ ድርጅት የሥራ አመራር ቦርድ አቶ አደባባይ አባይ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ በአገሪቱ እየታየ ላለው የማተሚያ ቤቶች መስፋፋትና እድገት መሰረቱ ሕገ መንግሥቱ ነው። የህትመት ኢንዱስትሪ ከፖለቲካ፣ ከኢኮኖሚና ማህበራዊ እድገት ጋር የተቆራኘና እድገትን ለማስቀጠል አቅም ያለው በመሆኑም ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ነው ።
ድርጅቱ ቅርንጫፉን በሐዋሳ መክፈቱ የክልሉን የህትመት አገልግሎት ደረጃ ለማሳደግና ለማስፋፋት እንዲሁም አገሪቱን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።
በእለቱ የተገኙት የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ተወካይ አቶ መርክነህ ያዕቆብ እንደተናገሩት፤ ለሰላም፣ ለዴሞክራሲ፣ ለመልካም አስተዳደርና ለልማት የህትመት ኢንዱስትሪ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው።ይህንንም የክልሉ ሕዝብም ሆነ የከተማዋ ነዋሪ ጠንቅቆ ያውቀዋል።
በክልሉ መዲና ድርጅቱ ቅርንጫፉን መከፈቱ እና በአሁኑ ሰዓት ደግሞ ለማስፋፋት ያቀረበው ጥያቄ የልማት አጀንዳ እንደመሆኑ በከተማው አስተዳደር በኩል አዎንታዊ ምላሽ እንዳለ አረጋግጠዋል።በክልሉም ሆነ በመዲናዋ ከፈጣን እድገት ጋር ተያይዞ የመጣ ከፍተኛ የህትመት ገበያ መፈጠሩንም አቶ መርክነህ ጠቅሰው፤ ቅርንጫፉ መከፈቱ እንግልትን እንዲሁም ተጨማሪ ወጪን በመቀነስ ረገድ ድርሻው ከፍተኛ ነው ብለዋል።
ከፓናሉ ተሣታፊ ደንበኞች መካከል ብዙዎቹ አስተያየት የሰጡ ሲሆን፤ ድርጅቱ ለደንበኞች የሚሰጠው መስተንግዶ አርኪመሆኑን ገልፀዋል። የደቡብ ጀምበር ደረጃ ሁለት አነስተኛ መለስተኛ የሕዝብ ማመላለሻ ባለንብረቶች ማህበር ሥራ አስኪያጅ አቶ አባተ ተሾመ ለኮሚሽን አገልግሎት የሚውል ደረሰኝ የሚያሳትሙት በሐዋሳ አርቲስቲክ እንደሆነ ጠቁመው፤ መልካም የሆነ የሥራ ግንኙነት እንዳላቸው ተናግረዋል።
አርቲስቲክ ማተሚያ ድርጅት ለኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን የማህበሩ የአመራር አባል አቶ አበረ አዳሙ ጠቁመው፥ ድርጅቱ በቀጣይ ጋዜጦችን የማተም ዕቅዱን ተግባራዊ እንዲያደርግ ሞክረ ዋል።
በዕለቱ ማምሻው ላይ በሐዋሳ ቪዥን ሆቴል ለድርጅቱ ግንባር ቀደሞች የሽልማት ሥነሥርዓት የተካሄደ ሲሆን፤ የሠራተኞች ትውውቅም ተከናውኗል። የላቀ አፈፃፀም በማሳየት ግንባር ቀደም ሆነው ከተሸለሙት መካከል ወይዘሮ ሃይማኖት ተከስተ እና አቶ ታምራት ረታ የሚጠቀሱ ሲሆን የተሰጣቸው የምስክር ወረቀትና ሽልማት ለበለጠ ሥራ የሚያነሳሳቸው እንደሆነ ገልጸዋል።
በዕለቱ ልዩ ተሸላሚ በመሆን በሠራተኞቹ አማካይነት የተሸለሙት ደግሞ ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ተካ አባዲ ናቸው። ደንበኞችና ባለድርሻ አካላትም ተሸልመዋል።http://www.ethpress.gov.et/addiszemen/index.php/addiszemen/news/1657-2013-02-04-05-14-41

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር