በሲዳማ ዞን በዘንድሮዉ የበጋ ወራት ከ38 ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት በመስኖ እየለማ ነው፡፡

አዋሳ ጥር 2005 በደቡብ ክልል ሲዳማ ዞን በዘንድሮዉ የበጋ ወራት ከ38 ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት ላይ የተለያዩ ሰብሎችና አትክልትና ፍራፍሬ እየለማ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ ። በዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች በመስኖ እየለማ ካለዉ መሬት ከስድስት ሚልዮን ኩንታል የሚበልጥ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገልጧል ። በመምሪያ የመስኖ ልማትና ተቋማት አስተዳደር ዋና የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ሙሉጌታ ማሞ ሰሞኑን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት በሁለት ዙር በሚካሄደዉ የበጋ መስኖ ልማት ከ530 ሺህ የሚበልጡ አርሶ አደሮች እየተሳተፉ ነዉ ። የመስኖ ልማቱ እየተካሄደ ያለዉ በየአካባቢው የሚገኙ ምንጮችን በማጎልበት፣ አነስተኛ ጉድጓዶችን በመቆፈር፣ ወንዞችን በመጥለፍና በቤተሰብ ደረጃ የኩሬ ውሃ በማሰባሰብ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች እየተካሄደ ባለዉ የመስኖ ልማት እስካሁን ከ12ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በአትክልትና ፍራፍሬ ፣በስራስርና በስራ ስርና በሌሎች ቋሚ ሰብሎች ተሸፍኗል ። ቀደም ሲል አብዛኛው የዞኑ አርሶ አደሮች የዝናብ ወቅትን ጠብቀዉ በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ በማምረት የድካማቸዉ ተጠቃሚ ሳይሆኑ መቆየታቸዉን አመልክተዉ በአሁኑ ጊዜ በዓመት ከሁለት ጊዜ በላይ በማምረት ኑሯቸዉን ማሻሻል ጀምረዋል ። በመልጋ ወረዳ፣ የጉጉማ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደሮች አቡሌ ክፍሌ እና መላኩ አበጀ ከሶስት ዓመታት በፊት እጅግ አስቸጋሪ የኑሮ ደረጃ ላይ እንደነበሩ አስታውሰዉ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ በመጠቀም የመስኖ ልማት ከጀመሩ ወዲህ ኑሮአቸው እየተለወጠ ከመምጣቱም ባሻገር እስከ አገር አቀፍ ድረስ ሞዴል አርሶ አደር በመሆን ለሽልማት መብቃታቸውን ገልጸዋል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር