ለሥርዓትና ለተቋማት ግንባታ ቅድሚያ ትኩረትና ርብርብ ይደረግ!!

ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን መሆን፣ ለልማት፣ ለሰላምና መረጋጋት፣ ለአገር ህልውናና ደኅንነት እጅግ በጣም ወሳኝ መሆኑ በተደጋጋሚ መነገሩ ቢሰለችም፣ አሁንም እንደገና ቅድሚያ ርብርብና ልዩ ትኩረት ለሥርዓትና ለተቋማት ግንባታ ይሰጥ እንላለን፡፡
አገራችን ኢትዮጵያ እንዴት መኖርና መንቀሳቀስ እንዳለባት የሚመራ ሕገ መንግሥት አላት፡፡ ሕገ መንግሥቱን ሥራ ላይ ለማዋል የወጡ በርካታ ሕጎች አሉ፡፡ አዋጆቹንና ሕጎቹን ሥራ ላይ ለማዋል ይበጃል የተባሉ ደንቦችና መመርያዎችም በብዛት አሉ፡፡ ከየት ጀምረን የት እንድረስ በማለት የተለያዩ ዕቅዶች ወጥተዋል፡፡ የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድም አለ፡፡ ህዳሴውን እውን ያደርጋሉ ተብለው የተቀመጡ ራዕዮችም አሉ፡፡

እነዚህን ሥራ ላይ የሚያውላቸው ግን ማን ነው? ሥራ ላይ የሚውሉትስ እንዴት ነው? ሥራ ላይ በትክክል መዋላቸውና አለመዋላቸው የሚታወቀውስ እንዴት ነው? ዋስትናቸው ምንድን ነው?

ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ስንሞክር ነው በኢትዮጵያ ተቋማት ያልተገነቡ መሆናቸውን፣ ሥርዓት ተፈጥሮላቸውና ሥርዓቱን ተከትለው የማይሠሩ መሆናቸው በግልጽ የሚታየው፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የመንግሥትና የግል ባንኮችን የሚከታተልና የሚቆጣጠር አካል ነው የሚል ሕግ አለ፡፡ እንደ ተቋም ይህን ኃላፊነት እንዲወጣ ሕግ ያስገድደዋል፡፡ በተግባር ግን ይህን ይፈጽማል? ደፈር ብሎ እንትን የተባለ ባንክን ይቆጣጠራል፤ ያዛል፡፡ ፈርቶ ደግሞ እንትን የተባለ ባንክን ለመቆጣጠር ይሽመደመዳል፡፡ አንዱ ባንክ ዞር በል ሲለው ያዙኝ ልቀቁኝ ይላል፡፡ ሌላው ባንክ ዞር በል ሲለው እውነትም በፍርኃት ዞር ይላል፡፡ እንደ ተቋም አይንቀሳቀስም፡፡ ወጥ ሥርዓት አይከተልም፡፡

መሬት የሚሰጠውና የሚቀማው ማዘጋጃ ቤት ነው፡፡ ሕግን ተከትሎ፡፡ ይህ ሕግ ነው፡፡ በተግባር ግን እንደዚህ ነው? በጎን ለእከሌ ስጥ ሲባል ይሰጣል፡፡ በቴሌፎን የእከሌን ቀማ ሲባልም ይቀማል፡፡ ያልተገነባ መሬት ቀማ ሲባል እከሌን በሁለት ዓመት ውስጥ አልገነባህም ብሎ ይቀማል፡፡ እከሌ ደግሞ አሥራ ስድስት ዓመት ሙሉ ዝምታ ወርቅ ነው ሲል ብቻ ሳይሆን፣ ዝምታ ወርቅ ያሳጣል ሲል ይስተዋላል፡፡ አንድ ዓመት ከተማዋን ያፀዳል፡፡ ሁለት ዓመት ማፅዳቱን ይረሳዋል፡፡ አቶ እከሌ ማዘጋጃ ቤቱን ሲመሩት አሠራሩ እንደዚህ ነው አቶ እከሌ ሲመሩት ግን አሠራሩ እንደዚያ ነው፡፡ እንደ ተቋም ከመንቀሳቀስ ይልቅ እንደ አቶ እከሌ ንብረትና ጥረት ይንቀሳቀሳል፡፡ ሥርዓት ተከትሎ በወጥነት ከመሥራት ይልቅ አሠራሩ ‹‹እንደ ሰው›› እና ‹‹ገጠመኝ›› ይሆናል፡፡ እንደ ተቋም አይንቀሳቀስም፤ ወጥ ሥርዓት የለውም፡፡

የፍትሕ አካላትም እንደዚሁ እንደ ተቋም መንቀሳቀስ አቅቷቸዋል፡፡ አንድን ጉዳይ ሕግ ነው ብለው ይይዙታል፡፡ በሌላው ጉዳይ ደብዳቤ ሲጻፍላቸውና ስልክ ሲደወልላቸው ይተውታል፡፡ እዚህ ያስከስሳል ያሉትን እዚያ አያስከስስም ይላሉ፡፡ እዚህ መብት ነው ያሉትን እዚያ መብት አይደለም ይላሉ፡፡ ዳኛ እከሌ አላየውም ያሉትን ዳኛ እከሊት አየዋለሁ እንጂ ይላሉ፡፡ እንደ ተቋም መሆኑ ቀርቶ እንደ ዳኛው ፍላጎት እየሆነ ነው፡፡ ሕጉ እንደሚለው መባል ቀርቶ ‹‹ገንዘቡ›› እንደሚናገረው ሆኗል፡፡ እንደ ተቋም ስለማይንቀሳቀስ ሥርዓትና ሕግ ከመከተል ይልቅ ‹‹ስልክ›› እና ‹‹ገንዘብ›› የሚያሽከረክሩት እየሆነ  ነው፡፡

ፖሊስ ራሱ ሲታይና ሲፈተሽም እንደ ተቋም በመንቀሳቀስ ሥርዓት ይዞ የመሥራት ችግር አለበት፡፡ በራሱ ድክመትና በሚደርስበት ጫና ምክንያት አንዱን ወንጀል ይከታተላል ሌላውን ወንጀል ለመከታተል ይፈራል፡፡ በአንዱ ላይ ማስረጃ ለማግኘት ቀንና ሌሊት ይሯሯጣል፡፡ በሌላ ጉዳይ ላይ ማስረጃ ተከምሮ፣ ተዘጋጅቶና ተቀናጅቶ ቢሰጠውም ‹‹ጥሪ አይቀበልም›› ይላል፡፡ በአንድ ጉዳይ ጀግና ይሆናል፡፡ በሌላ ጉዳይ ፖሊስ ራሱ ጰርጳራና ፈሪ ሆኖ ሲርበተበት ይታያል፡፡ በአንድ ጉዳይ ‹‹ሕግ እንደሚለው›› ይልና በሌላ ጉዳይ አቶ እከሌ እንደሚሉትና ‹‹እንደሚሰጡት›› ይላል፡፡ እንደ ተቋም እንዲህ አልሠራችሁም ይህን ሥርዓት አልተከተላችሁም በማለት ተከታትሎ ሕግ ማስከበርና ሲገባው፣ በሕግ የተፈጠረ ተቋም መሆኑንና ሕግና ሥርዓቱን ይረሳና እንደ ባለሥልጣን ፍላጎት የሚንቀሳቀስና ‹‹እንደ ባለገንዘብ›› ትዕዛዝ የሚሽከረከር ይሆናል፡፡

የትምህርት ተቋማትም እየተበላሹ ናቸው፡፡ ከጥንት ከጥዋቱ ጀምሮ ይታወቅና ይተገበር የነበረው ‹‹ፈተና ያለፈ ያልፋል›› የሚለው እየቀረ ማለፍም በትውውቅና በጉቦ እየሆነ ነው፡፡ ምደባና ቅጥርም እንደዚሁ፡፡ ደመወዝ፣ ዕድገትና ስኮላርሺፕ ሳይቀር እንደ ተቋም ማስተናገድና መወሰን እየቀረ ግንኙነት፣ ጥቅማ ጥቅምና መሰል ጉዳዮች ወሳኝ ሚና እየተጫወቱ ናቸው፡፡ የትምህርት ተቋማት ብዛት መጨመሩ ቢያስደስተንም ጥራት መጓደሉ በእጅጉ እያሳሰበን ነው፡፡ እንደ ተቋም የጠነከሩና ሥርዓት ተከትለው የሚጓዙ መሆናቸው ቀርቶ ማስመሰልና ማግበስበስ እየታየባቸው ነው፡፡ ኧረ ተው የሚልም ጠፍቷል፡፡ ‹‹ተቋም›› እና ‹‹ሥርዓት›› ያየህ ወዲህ በለኝ እያሉ ናቸው፡፡

በፌዴራልና በክልል ደረጃ በርካታ መሥሪያ ቤቶች አሉ፡፡ የመንግሥት ብቻ ሳይሆኑ የግልና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም፡፡ ግን! ነገር ግን! ብዛት እንጂ ጥራት እየጎደላቸው ነው፡፡ ጠንካራ ተቋም ሆነው ራሳቸውን ችለው ቆመው ከመንቀሳቀስ ይልቅ እንደ ባለሥልጣኑ ፍላጎትና አመለካከት የሚንቀሳቀሱ ናቸው፡፡ ሕግና መመርያ ጥሰው እንደ ባለሥልጣን ፍላጎት የሚንቀሳቀሱ ናቸው፡፡ ግልጽና ግልጽ በሆነ መንገድ እየታየ ነው፡፡

የሚያሳዝነው ፓርላማው ራሱም እንደ ተቋም መንቀሳቀስ እያቃተው ነው፡፡ ፓርላማው የግል ቴሌቪዥን ጣቢያ እንዲቋቋም ሕግ አውጥቷል፡፡ በተግባር ግን ዞር በል ተብሏል፡፡ ዞር በልማ አልባልም እኔ ያወጣሁት ሕግ ተግባር ላይ መዋሉ ግዴታ ነው ከማለት ይልቅ ተገልብጦ ዞር በል ያለውን ሲፈራ ይታያል፡፡ የመንግሥት መገናኛ ብዙኀን ተጠሪነታቸው ለፓርላማ ነው የሚል ሕግ ቢኖርም፣ አቶ እከሌ ሲያዛቸውና ሲያሽከረክራቸው እያየ ፓርላማው አንዲት ቃል ትንፍሽ አይልም፡፡ ፓርላማው ራሱ እንደ ተቋም በሥርዓት መጓዝ እየተሳነው ነው፡፡

ችግሩ ከባድና ብዙ ነው፡፡ መንግሥት ለተቋማት ግንባታና ለሥርዓት ግንባታ ልዩ ትኩረትና ርብርብ ያድርግ፡፡ ተቋም ካልተገነባና ሥርዓት ከሌለ በሹም ፍላጎትና ወኔ የሚንቀሳቀሱ መሥሪያ ቤቶች ብቻ ይዘን እንቀራለን፡፡ እንደዚህ ዓይነት አካሄድም የኢንቨስተሮችን አመኔታ ያሳጣል፡፡ የሕዝብን ሕገ መንግሥታዊ መብትና ግዴታ ይረግጣል፡፡ የተቆጣጣሪ አካላት፣ የሕግ አውጪና ተርጓሚ አካላት ሚና ወደ ዞር በል ይቀየራሉ፡፡

የልማትና የዴሞክራሲ ራዕዮች ከአስተማማኝነት ወደ ገጠመኝነት ይቀየራሉ፡፡ ይህ አደገኛ ነው፡፡

ለዕድገት፣ ለዴሞክራሲ፣ ለሰላም፣ ለህልውናና ለደኅንነት ጠንካራ ተቋማትና ጠንካራ ሥርዓት የግድ ይላል፡፡ በተግባር ግን ደክመናል፡፡ ለተቋማት ግንባታና ለሥርዓት ግንባታ ልዩ ትኩረትና ርብርብ ይደረግ!

http://www.ethiopianreporter.com/editorial/294-editorial/8778-2012-12-08-08-40-09.html

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር