ፕላምፕኔት የተሰኘውን ምግብ ለገበያ ያቀረቡ የንግድ ተቋማት እርምጃ ተወሰደባቸው


አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 9 ፣ 2005 (ኤፍ ቢ ሲ) የሃዋሳ ከተማ ጤና መምሪያ የምግብ እጥረት ላጋጠማቸው ህጻናት በነጻ የሚሰጠውን "ፕላምፕኔት" የተሰኘ ምግብ ለገበያ ባቀረቡ 25 የንግድ ተቋማት ላይ ህጋዊ እርምጃ እየወሰደ ነው።
ምግቡን መንግስት ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር ከፍተኛ ወጪ እያደረገበት ለታለመላቸው ህጻናት እንዲደርስ የሚያደርግ ሲሆን ፥ የሚቀርበውም በጤና ተቋማት በኩል በነጻ እና በባለሙያ ትዕዛዝና ክትትል ብቻም ይሰጣል።
ይሁን እንጂ በሃዋሳ ከተማ ይህ ህይወት አድን ምግብ ከታለመለት ዓላማ ውጪ እየዋለ መሆኑን ፥ በመምሪያው የጤናና ጤና ነክ አገልግሎቶችና ግብዓቶች ስርዓት ቁጥጥር ዋና የስራ ሂደት ባለቤት አቶ ዘመን ለገሰ ተናግረዋል።
በተለያዩ መንገዶች ከየጤና ተቋማቱ እየወጣ ለንግድ እየቀረበ በመሆኑ ፥ ዛሬን ጨምሮ ሰሞኑን መምሪያው ይህን ምግብ ለገበያ በሚያቀርቡ የንግድ ተቋማት ላይ ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ተገዷል።
አቶ ዘመን እንዳሉት ወደ እርምጃ የተገባው በተለያዩ መንገዶች በተደጋጋሚ ፥ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ቢሰጥም ለውጥ ሊመጣ ባለመቻሉ ነው።
አስቀድሞ እርምጃ ተወስዶባቸው ዳግም ወደ ህገ ወጥ ስራው ላለመግባት ፥ መተማመኛ ፈርመው የንግድ ተቋሞቻቸው የተከፈቱላቸው እንዳሉም ነው ያስረዱት።
በዚህ ህገ ወጥ ስራ ውስጥ ተሳትፈዋል በሚል ተጠርጥረው በፍርድ ሂደት ላይ የሚገኙ ሁለት የህክምና ባለሙያዎችም አሉ ነው ያሉት አተ ዘመን።
ከጉዳዩ አሳሳቢነት አንጻር የጤና መምሪያው በከተማዋ የንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮን ጨምሮ ፥ ዘጠኝ ያህል ባለድርሻ አካላትን ያካተተ የህብረተሰብ ጤና ተቆጣጣሪ ግብረ ሃይል ማቋቋሙን በዛብህ ማሞ ዘግቧል።

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር