የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ተጠናቀቀ



የክልሎችን የ2004 እቅድ አፈጻጻም ማጠቃለያና የ2005 እቅድ ዝግጅትና ፈጻሚ ማዘጋጀት ስራዎችን በመፈተሽ ስብሰባውን የጀመረው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ባለፈው አመት የገጠር ልማትን በተመለከተ በተፋሰስ፣ በመስኖና በሰብል ልማት ስራዎች አፈጻጻም የነበረው አንጻራዊ ልዩነት እንደተጠበቀ ሆኖ በሁሉም ክልሎች የተሻለ እንቅስቃሴና ውጤት መታየቱን አረጋግጧል፡፡


ይኸው አበረታች እንቅስቃሴ በ2005 የአርሶ አደሩን ምርታማነትና አጠቃላይ ሀገራዊ ምርትን ለማሳደግ የሚደረገው ርብርብ አዎንታዊ ድርሻ እንዳለው ገምግሟል፡፡ በማህበራዊ ልማት ዘርፍም በተለይም የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ሰፊ እንቅስቃሴ መደረጉንና በወላጅ፣ በመምህራንና በተማሪዎች የተደራጀ ጥረት አመርቂ ውጤት መታየቱን አረጋግጧል፡፡

የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራሙን በሰፊ የህዝብ ተሳትፎ በማስፋፋትና የእናቶችና ህጻናትን ሞት ለመቀነስና በአጠቃላይ ጤንነቱ የተጠበቀ ህብረተሰብ በመገንባት የጀመርነውን ፈጣን እድገትና የሀገሪቱን ህዳሴ ለማስቀጠል በተለይ የሴቶች አደረጃጀቶች ላይ ተመሰርቶ የተደረገው ጥረት ከፍተኛ ውጤት በማሳየቱ በሁሉም ክልሎች የተገኙትን ልምዶች በመቀመር አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥቶ መክሮበታል፡፡

ከመልካም አስተዳደር ጋር በተያያዘ በገጠሩ የተሻለ ሁኔታ መኖሩን የገመገመው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው የተገኘውን ለውጥ መሰረት በማድረግና የተጀመረውን የህዝቡን ልማታዊ እንቅስቃሴ በማጠናከር በህዝቡ በራሱ ተሳትፎ አልፎ አልፎ የሚገጥሙ ችግሮችን ማስወገድ የሚችልበት ሁኔታ መፈጠሩን በመገምገም ከስምምነት ላይ ደርሷል፡፡

የከተማ ሰራዎችን በተመለከተ በዋነኝነት የከተማውን ነዋሪ የገቢ አቅም ለማሳደግ የተካሄደው የስራ እድል ፈጠራና የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ልማት በእድገትና ትራንስፎርሜሸን እቅዱ ከተቀመጠው ግብ አንጻር አበረታች ርቀት የተኬደበት መሆኑንና ይኸው ስራ በ2005ትም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስቧል፡፡

በመልካም አስተዳደር ያሉትን ሁኔታዎችን በመፈተሽም በተለይ ባለፈው አመት ተጀምሮ የነበረው በሁሉም ክልሎች ከነዋሪው ጋር በችግሮችና መፍትሄዎች ዙሪያ በምልልስ ይደረግ የነበረው ህዝቡን ያሳተፈ የማጥራትና የመልካም አስተዳደር ማስፈን እንቅስቃሴ በያዝነው አመትም የሲቪል ሰርቪስና የፍትህ ስርዓት ማሻሻያ ፕሮግራሞችን በተጠናከረ ሁኔታ ለመተግበር ከሚደረገው ጥረት በተጨማሪ በየወቅቱ የሚያጋጥሙ ችግሮች ለማስወገድ የተጀመረውን የህዝቡን ተሳትፎ ቀጣይነት በማረጋገጥ ትርጉም ያለው መሻሻል ለማምጣት በሚቻልባቸው አቅጣጫዎች ዙሪያ አጽንኦት ሰጥቶ ተወያይቷል፡፡

የ2004 ልምዶችን በመቀመር በያዝነው አመት በሰፊ የህዝብ ንቅናቄ በገጠርና በከተማ ልማት ስራዎች በእድገትና ትራንስፎርሜሸን እቅዱ የተቀመጠውን የተለጠጠ ግብ ለማሳካት ወሳኝ የሆነውን ፈጻሚን የማዘጋጀት ስራ በተቀመጠለት አቅጣጫ መሰረት ወደ ተግባር እየተሸጋገረ መሆኑን የገመገመው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው የዝግጅት ስራዎቹ በሁሉም ክልሎች በፍጥነት ተጠናቀው የባለፈውን ክረምት ስራዎች በማጠቃለል የበጋው ስራ እንዲጀመር አሳቧል፡፡

የድርጅቱ አባላትና ህዝቡ በታላቁ መሪና እርሱም በሚመራው ኢህአዴግ የተጀመረውን የህዳሴና የብልጽግና ጉዞ በየተሰማራበት ሁሉ አጠናክሮ ለመቀጠል ያሳየው ተነሳሽነትና ቁጭት ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ግብአት በመሆኑ የዝግጅት ስራው ይህንኑ ታሳቢ አድርጎ እየተካሄደ መሆኑን በማረጋገጥ በዚሁ ግለት መቀጠል እንዳለበት ስምምነት ላይ ደርሷል፡፡

የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በሌሎች አጀንዳ ስር የአካባቢና የማሟያ ምርጫ እና የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባላት ምርጫ ዝግጅትን የገመገመ ሲሆን ምርጫው ሰላማዊ፣ ነጻና ፍትሃዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚደረግ አረጋግጧል፡፡
ፓርቲው በህግ ከተደነገገው የፓርቲዎች የስነ-ምግባር ህግ እና ሌሎች የምርጫ ህጎች በተጨማሪ አባላቱ የሚገዙበትን የስነ- ምግባር መመሪያ በማውጣት አርአያነቱን ለማረጋገጥ የተንቀሳቀሰ ሲሆን በዚህ ምርጫም ይህንኑ አጠናክሮ እንደሚቀጥል እና የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት ጋር በመመካከር ባለፉት አመታት የተጀመረውን ችግሮችን በጋራ ተወያይቶ የመፍታት እንቅስቃሴ አጠናክሮ እንደሚገፉበት በማረጋገጥ የምርጫውን ስራ በማእከልና በየደረጃው የሚያስተባብሩ ኮሚቴዎች አደረጃጀት ላይ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በያዝነው አመት የሚካሄደውን 9ኛውን የግንባሩን ድርጅታዊ ጉባኤ ዝግጅቶችንም ገምግሟል፡፡ 9ኛው ጉባኤ የአምስት አመቱ የእድገትና ትራንስፎርሜሸን እቅዱ እኩሌታ አፈጻጻም የሚፈተሽበትና የቀጣይ አመታት አቅጣጫ የሚቀመጥበት ከመሆኑም ባሻገር በታላቁ መሪ ቀያሽነት የተጀመረው የድርጅቱ የተሃድሶ እንቅስቃሴ በተቀጣጠለባቸው ባለፉት 12 አመታት የሀገራችን ህዳሴ በማፋጠን የደረሰበት ደረጃ የሚቃኝበት በመሆኑ ከወዲሁ የተጀመሩት የዝግጅት ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በማሳሰብ የዝግጅት ኮሚቴው በሰው ኃይል የሚጠናከርበትን አቅጣጫ በማስቀመጥ እና ከቤቱ በቀረቡ ሌሎችም አጀንዳዎች ዙሪያ በሰፊው በመምከር መደበኛ ስብሰባውን ጥቅምት 26/2005 ከሰዓት በኋላ አጠናቋል፡፡

ምንጭ፡የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ምክር ቤት ፅህፈት ቤት

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር