''ኢትዮጵያ ከቡናው ዘርፍ ለማግኘት ያሰበችውን ገቢ ለማሳካት ጥረቷን አጠናክራ ትቀጥላለች''-ጠ/ሚ ኃይለ ማርያም


አዲስ አበባ ጥቅምት 29/2005 ኢትዮጵያ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዷ ከቡናው ዘርፍ ለማግኘት ያሰበችውን ገቢ ለማሳካት ጥረቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ አስታወቁ። ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ የመጀመሪያውን ዓለም አቀፍ የቡና ጉባዔ ሲከፍቱ እንደተናገሩት አገሪቱ ከዘርፉ እያገኘች ያለችውን ገቢ በይበልጥ በማሳደግ የኢኮኖሚዋን ዕድገት ለማስቀጠል እንቅስቃሴዋን ታጠናክራለች። ኢትዮጵያ ባለፉት አራት ዓመታት በዓይነቱ በአፍሪካ የመጀመሪያ በሆነው በኢትዮጵያ ምርት ገበያ በኩል በማገበያየት የተሻለ ገቢ እያገኘች መሆኗንና ከቡና የተገኘው ገቢ ከአጠቃላይ የአገሪቱ ገቢ 74 በመቶ መድረሱን አስታውቀዋል። በዚህም እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠርበ2010/11 የምርት ዘመን ባቀረበችው ምርት ከ235ሺህ ቶን በላይ ቡና በማቅረብ 768ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር ማግኘቷን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ተናግረዋል። ባለፉት ዘጠኝ ዓመታትም በአማካይ 200ሺህ ቶን ቡና ለዓለም ገበያ በማቅረብ 842ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገቢ ስታገኝ መቆየቷንም አስታውሰዋል። አገሪቱ ለቡና ምርት ባላት አመቺነት ከአንድ ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች በምርታማነትና ከ15ሚሊዮን በላይ በቀጥታና በተዘዋዋሪ በምርት ሂደቱ ላይ መሰማራታቸውን ገልጸው፣ከዘርፉ ልማት በይበልጥ የምትጠቀምበትን ሁኔታ ለመፍጠር ጥረቱ እንደማይቋረጥም አቶ ኃይለማርያም አረጋግጠዋል። የጉባዔው ተሳታፊዎች የአገሪቱን ቡና ምርታማነት ለማሳደግ የሚደረገውን እንቅስቃሴ በማገዝ በዘርፉ ያሉትን ችግሮች በመለየት ፍሬያማ ውጤት እንደሚያስገኙም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም እምነታቸውን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ኮፊ ኤክስፖርተርስ አሶሴሽን የቦርድ ሊቀመንበር አቶ ሁሴን አግራው በበኩላቸው ኢትዮጵያ የቡና ዘር መገኛና ጥራት ያለው ቡና በማቅረብ የያዘችውን ደረጃ ለማስቀጠል ጥራቱና ብዛቱ የተጠበቀ ቡና ለዓለም ገበያ ለማቅረብ በሚቻልበት ሁኔታ ለመነጋገር ጉባዔው መዘጋጀቱን ተናግረዋል። በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ውስጥ ከቡና ዘርፍ የተያዘውን ግብ በማሳካት በዘርፉ የተሰማሩ አካላትና አገሪቱ ተጠቃሚ እንድትሆን በማድረግም ጉባዔው ዓይነተኛ ድርሻ ይጫወታል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል። ኢትዮጵያ በምርቱ በዓለም ገበያ ተገቢውን ሚና እንድትጫወትም ሁሉም ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ጥረት እንዲያደርጉ ሊቀመንበሩ ጠይቀዋል። በኢትዮጵያ የአውሮፓ ኅብረት ልዑካን ቡድን ኃላፊ ሚስተር ዣቪዬር ማርሻልና የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት የኢትዮጵያ ተልዕኮ ዳይሬክተር ሚስተር ዴኒስ ዌለር በየበኩላቸው ኢትዮጵያ የቡና ምርቷንና በዓለም ገበያ ያላትን ድርሻ ለማሳደግ እያደረጉት ያለውን ድጋፍ እንደሚያሳድጉት አረጋግጠዋል። የጉባዔው ተሳታፊዎች በዘርፉ ያሉትን ችግሮች በመለየትና መፍትሄዎችን በመጠቆም ለአገሪቱና ለሕዝቧ ኑሮ መሻሻል የሚበጁ ሐሳቦችን በማቅረብ እንዲረዱም አሳስበዋል። ለሁለት ቀናት በሚካሄደው ጉባዔ በኢትዮጵያ የቡና ምርት፣ግብይትና አቅርቦት የሚታዩ ችግሮችንና የወደፊት አቅጣጫዎችን የሚያመለክቱ ጥናታዊ ጽሁፎች ይቀርቡበታል። በጉባዔው ከ30 አገሮች፣ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ከአገር ውስጥ የተወከሉ 250ሰዎች በመሳተፍ ላይ ናቸው። ጉባዔውን ያዘጋጁት የኢትዮጵያ ኮፊ ኤክስፖርተርስ አሶሴሽንና የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት(ዩ ኤስ ኤይድ)መሆናቸውን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በዘገባው አመልክቷል።
http://www.ena.gov.et/story.aspx?ID=3248

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር