ሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ምርትና ምርታማነት በመጨመር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችል የግብርና ቴክኖሎጂ እያስተዋወቀ ነው


አዋሳ ህዳር 18/2005 የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነትን ለመጨመርና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከ11 የሚበልጡ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሩ በማስተዋወቅ ላይ እንደሚገኝ የሀዋሳ ዩነቪርስቲ ገለጸ፡፡ 
በዩኒቨርስቲው በሲዳማና ገዴኦ ዞኖች በሙከራ ደረጃ እየተሰሩ ያሉ ቴክኖሎጅዎችን የማላመድ፣ የማስተዋወቅና የማስፋፋት ስራዎች ሰሞኑን ተጎብኝቷል፡፡ የዩኒቨርስቲ አካዳሚና ምርምር ምክትል ፕሬዜዳንት ዶክተር ፍቅሬ ደሳለኝ በጉብኝት ወቅት እንደገለጹት በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ መጨረሻ የግብርና ምርት በእጥፍ ለማሳደግ የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት ዝርያዎችን ለማላመድና ማስፋፋት ስራ ዩኒቨርስቲው ትኩረት ተሰጥቶ እየሰራ ይገኛል፡፡ ዩኒቨርስቲው በሀገሪቱ የግብርና ምርታማነትን ለማሻሻል የሚደረገውን ጥረት በእጅጉ የሚያግዙና በምርምር ጣቢያ ምርታማነታቸው የተረጋገጠ 11 ዝርያዎችን በክልሉ አራት ወረዳዎች የማባዛትና የማላመድ ስራዎችን በማከናወን ላይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በልጆች ላይ የሚከሰተውን የቫይታሚን ኤ ንጥረ ምግብ እጥረት የሚከላከሉ ሰብሎች፣ የቤተሰብ ገቢና የምግብ ዋስትናን ለማሻሻል የሚያግዙ፣ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ፣ የአንስሳት መኖ፣ ሀገር በቀል የበግና ፍየል ዝርያዎችን የማዳቀልና ማባዛት እንዲሁም መኖን በዩሪያ ማከምና ድርቆሽ ሳይበላሽ የማቆየት ዘዴዎች ይገኙበታል ብለዋል፡፡ በሄክታር እስከ 50 ኩንታል ምርት ሊሰጡ የሚችሉ የቢራና የምግብ ገብስ፣ ባቄላና ሌሎች የሰብል ዝርያዎች የሚገኙ ሲሆን በብተናና በመስመር የመዝራት ልዩነትና ከዚሁም ሊገኝ የሚችሉ ጠቀሜታዎች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡ በንጥረ ምግብ ይዘት የበለፀጉ የደጋና የወይና ደጋ የጥራጥሬ ሰብሎችን በማምረት የቤተሰብ የንጥረ ምግብ አቅርቦትን ለማሻሻል፣ ናይትሮጂን ወደ ራሳቸው በማዋሃድ የአፈር ለምነትን ለመጠበቅ የጥራጥሬ ሰብሎችና የአርሶ አደሩን ገቢ ለመጨመር ቴክኖሎጂ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን እየሰሩ እንደሚገኙም ጠቁመዋል፡፡ ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ፣በሽታ የመቋቋም አቅማቸው ከፍተኛ የሆኑና ለስነ ምህዳሩ ተስማሚነታቸው በምርምር የተረጋገጡ 971 እና 85 ሺህ 257 የተሰኙ የቡና ዝርያዎችን በተመረጡ 34 አርሶ አደሮች ማሳ ላይ የብዜት ስራዎች በመከናወን ላይ እንደሚገኝ ዶከተር ፍቅሬ ተናግረዋል፡፡ በዩኒቨርሰቲው የምርምርና ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶክተር ተስፋዬ አበበ በበኩላቸው ቴክኖሎጂዎችን የማላመድ ስራ በክልሉ በአራት ወረዳ 16 ቀበሌዎች በ646 አርሶ አደሮች ማሳ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸው ቴክኖሎጂዎቹ በሆለታና ሌሎች የግብርና ምርምር ማዕከል ውጤታማነታቸው የተረጋገጠ ነው ብለዋል፡፡ የተሻሻሉ አሰራሮችንና የግብርና ምርታማነትን ሊጨምሩ የሚችሉ ቴክኖሎጂዎችን በመለየት አርሶ አደሩ በስፋት እንዲጠቀምበትና የግብርና ምርትን በእጥፍ የማሳደግ ዓላማን ለማሳካት ዩኒቨርስቲው ከመቀሌ፣ከባህር ዳር፣ ከጅማና ከሃሮማያ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ዩኒቨርስቲው ምርታማነታቸው የተረጋገጡ ቴክኖሎጂዎችን ከማላመድ በተጨማሪ ከ190 በላይ የምርምር ሰራዎችን በማካሄድ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመው የምርምር ስራዎቹ የአምስት ዓመቱን የምርምርና ልማት ስትራቴጂን መነሻ ያደረጉ ለአርሶ አደሩ ፋይዳ ያላቸውና ችግር ፈቺ የሆኑ ናቸው ብለዋል፡፡ ዩኒቨርስቲው የማላመዱና የማባዛቱ ስራ ስኬታማ እንዲሆን ኢትዮጵያ ውስጥ የግብርና ምርታማነትን ለማሻሻል የሚደረገውን ጥረት የሚያግዙ ከኢትዮጵያና ኔዘርላንድ መንግስት የጋራ ፕሮጀክት ካሳኬፕ ጋር በመሆን እየሰራ መሆኑን የጠቆሙት ዶክተር ተስፋዬ በቀጣይ በሙከራ ጣቢያ የተሻለ ውጤት ያሳዩ ቴክኖሎጂዎችን ከክልሉ ግብርና ዕድገት ፐሮግራም ጋር በማቀናጀት በሁሉም ወረዳ ለማስፋፋት ስትራቴጂ ተነድፎ እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

 በሲዳማ ዞን ማልጋ ወረዳ ጉጉማ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ቦጋለ ግዛው ሳቢኒ የተባለ የቢራ ገብስ ዝርያ ተጠቃሚ ሲሆኑ ቀደም ሲል ማዳበሪያና ምረጥ ዘር ሳይጠቀሙ በተለምዶ በብተና እንደሚዘሩና እጅግ ዝቅተኛ ምርት እያገኙ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ሳቢኒ የተባለውን የገብስ ዘርያ በመጠቀም በመስመር በመዝራታቸው ቀደም ሲል ከሁለት እስከ ሶስት ኩንታል ምርት ከሚያገኙበት መሬት እስከ 15 ኩንታል ምርት እንደሚያገኙ ገልጸው በተለይ ለዚህ ውጤታማነት የበቁት በመስመር መዝራት፣ ምርጥ ዘር ና ማዳበሪያ መጠቀማቸው ነው፡፡ ሌላው አርሶ አደር በራሶ ደምሴ በጌዲኦ ቡሌ ወረዳ እላልቶች ቀበሌ ነዋሪ ከዚህ ቀደም የሚጠቀሙበት ማሳ ተዳፋት በመሆኑ አፈሩ ሙሉ በሙሉ በጎርፍ ስለሚጠረግ ዝቅተኛ ምርት ሲያመርቱ ቆይተዋል፡፡ በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ፣በዞንና ወረዳ የግብርና ባለሙያዎች እንዲሁም ከቀበሌው ልማት ሰራተኛ በተደረገቸው ድጋፍ የተፋሰስ ስራ በማከናወን፣ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር በመጠቀም በመስመር ዘርተው ቀደም ሲል 4 ኩንታል ምርት ከሚሰጣቸው መሬት ከ12 ኩንታል በላይ ምርት ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡ አዲስ ቴክኖሎጂ በመጠቀም በመስመር መዝራት በትንሽ መሬት ላይ ከፍተኛ ምርት ከማግኘት በተጨማሪ የዘር ብክነትን ይቀንሳል፣ ጊዜንና ጉልበትንም ይቆጥባል ብለዋል፡፡ በአንድ ለአምስት በመቀናጀት የምግብ ዋስትናን በበቤተሰብና በአከባቢ ለማረጋገጥ እንዲሁም ቴክኖሎጂውን በሁሉም አርሶ አደሮች መሬት ላይ የማስፋፋት ስራ ላይ ትኩረት ሰጥተው በመስራት የበኩላቸው እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡
http://www.ena.gov.et/Story.aspx?ID=3615&K=1

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር